“አሁን ያለው እግር ኳስ ጦር
ያማዝዛል ብዬ አላምንም”
ከውድድር ንግስናው ወደ አመራርነቱ
ከመጣ ከ1 አመት በላይ ሆኖታል፡
- ማሰታውቂያ -
፡ እነኚያ በመላው አለም የአትሌቲክስ
ትራኮች ላይ ይፈረጥጡ የነበሩት እግሮች
አሁን ለውሳኔ ሰጪነት ወደ ቢሮ የሚገቡ
ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን
ፕሬዝዳንት ሆኖ በተመረጠ ማግስት ለሃትሪክ
የመጀመሪያውን ቃለ ምልልስ የሰጠው
ሃይሌ ገ/ስላሴ በድጋሚ ከዝግጅት ክፍላችን
ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ስለሩጫ
ህይወቱና አመራርነቱ፣ ስለኢትዮጵያ እግር
ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫና ውዝግብ፣ ስላለው
ሀብትና በአገር ደረጃ ስላለው ምኞት፣
ቼልሲን ለምን እንደደገፈ፣ የአትሌቲክስ
ብሄራዊ ቡድኑ ፈረሰ ወይስ አልፈረሰም
በሚሉት ሌሎች ጉዳዮች ግልፅ የሆነ ምላሽ
የሰጠው ሃይሌ ገ/ስላሴ ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር
የነበረው ቆይታ ይህንን ይመስላል፡፡
ሃትሪክ፡- ሃይሌ ገ/ስላሴ በህይወቱ
ማድረግ ፈልጎ ያቃተው ነገር አለ?
ሃይሌ፡- (ሳቅ) አዎ በጣም አለ እንጂ
በማራቶን የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ
ፈልጌ መሳተፍ ባለመቻሌና ባለመሳካቱ ቅር
ይለኛል፡፡
ሃትሪክ፡- አሁንስ እድል የለም እንዴ?
ሃይሌ፡- (ሳቅ በሳቅ) ልሞክረው እንዴ?
ተው አትቀልድብኝ በቀስት ካልሆነ በሌላ
መንገድ አይሆንም በተነገረን መሰረት
እድሜያችንም 45 ገብቷል፡፡ በተነገረን ማለቴ
ደግሞ አባቴና እናቴ አንተ የተወለድከው
በዚህ ቀን ነው አሉኝ፤ ያቺ አህያ አንተ
በተወለድክበት ቀን ጠፍታብን ነበር ያው
በጅብ ተበልታለች… መቼ ነው የተበላችው
ሲባሉ ግን ቀኑ አይታወቅም (ሳቅ)
ሃትሪክ፡- ኢትዮጵያ ላይ ማየት
የምትፈልገው ምንድነው?
ሃይሌ፡- ኢኮኖሚዋ አድጎ ማየት! እንደ
አውሮፓዊያን ከድህነት ወጥታ ሌላውን
አለም ስትረዳ ማየት እመኛለሁ፡፡
ሃትሪክ፡- ሃይሌ ከስራው ውጪ በምን
ዘና ይላል?
ሃይሌ፡- ጋዜጣና መፅሔት ማንበብ፣
የታሪክ ፊልሞችን ማየት እወዳለሁ፡፡ ቤቴ
በጊዜ ገብቼ ከቤተሰቤ ጋር መጫወትን
እወዳለሁ፡፡
ሃትሪክ፡- ሃይሌ ከሰር አሌክስ ፈርጉሰንና
ከነፈርዲናንድ ጋር የተነሳኸውን ፎቶ አየሁ
አገኙህ ወይስ አገኘሃቸው?
ሃይሌ፡- (ሳቅ) ምንድነው ያልከው?
እነሱን አገኘው ነው የሚባለው እኩልማ
አይደለሁም፡፡ የነርሱና የኔ ዝና አይገናኝም
የሰው መለኪያ ገንዘብ ሆኗልኮ የገንዘብ
ጨዋታ አለማችን ላይ ተንሰራፍቷል እኛ
ከፍለን እነርሱን ትልቅ አደረግናቸው፡፡
ሰዎቹ የመላው አለም አይን አርፎባቸዋል፡
፡ ከዚህ በፊትም ከፈርጊ ጋር አንዴ
ተገናኝተናል በድጋሚ ደግሞ በማንቸስተር
ሩጫ ላይ ተከፍዬ አሸነፍኩና በነጋታው
ሄደን አየናቸው፤ ምናልባት ሃይሌ የሚባል
ከኢትዮጵያ የመጣ አትሌት ነው ብለው
የተነሳነው ፎቶ ይመስላል፡፡ ፎቶውን
ሰዎች አንስተው ነው የለቀቁት፤ ራሴኮ
አልተነሳሁም እነርሱ ሃይሌ ጀግና ነው
ብለው አይነሱም እኔም በተመሳሳይ ጀግኖቼ
ናችሁ ብዬ አልነሳም፡፡ እንደ አትሌቲክስ የኔ
ጀግኖችን ባገኝ ነው ፈልጌ ፎቶ የምነሳው፡
፡ እነ ሜሲና ሮናልዶ ቢመጡም ፎቶ ብነሳ
ብዬ አልመኝም፡፡ የኔ መስመር ይለያል
በመስመራቸው ከማክበር ውጪ የተለየ ቦታ
የለኝም፡፡
ሃትሪክ፡- ሃይሌና ቼልሲ ለምን
ተዋደዱ?
ሃይሌ፡- አዎ ቼልሲን የምደግፈው
በሞውሪንሆ ጊዜ ነው፡፡ ቼልሲ ንዴቴን ያበረደ
ክለብ ነው እዚህ ሃገር የማንቼና የአርሴ
ደጋፊ ነን ብለው ሲጣሉ ጩቤ ሲማዘዙ ሳይ
እበሳጭ ነበር፡፡ ያኔ ነው ታድያ ሞውሪንሆ
መጥቶ የደጋፊዎቹን ረብሻና ፀብ ሲያበርድ
ዋንጫ ሲወስድ ሳይ ይሄ ለመቀጣጫ አሪፍ
ነው ብዬ መደገፍ ጀመርኩ፡፡
ሃትሪክ፡- ሃይሌ ስለማንቼና አርሴ ካነሳህ
በተደጋጋሚ በኛ አገር ኳስ ረብሻ ሲነሳ ሰው
ሲሞትም አየን ይሄንንስ እንዴት አየኸው?
ሃይሌ፡- አሳፋሪ ነው ስፖርት ሜዳ
ላይ ኳስ ልታይ መጥተህ በዚህ ደካማ
ኳስ አባበህ መደባደብ ያሳፍራል፡፡ እንደው
የእኛ አትሌቲክስ በተደጋጋሚ ቢወቀጥ ሰው
እንዲህ ይሆናል? በአትሌቲክሱ ደረጃችን
ከ100 በላይ ቢሆን ምን ይፈጠራል? የኛ
ኳስ ፀብ የሚገባው ነው ብዬ አላምንም
አትሌቲክሳችንን ልንጠብቅ ይገባል በእጅ
የተያዘ ወርቅ እንዳይሆንብን እሰጋለሁ፡
፡ በእግር ኳሱ በርትተን ከሰራን ውጤት
ይመጣል፡፡ አሁን ያለው የኛ አገር ኳስ ግን
ጦር ያማዝዛል ብዬ አላምንም ደጋግሜ
መናገርም የምፈልገው ይሄን ነው፡፡ እንደኔ
ሃይ ባይ የጠፋ ይመስለኛል፡፡ ከኳስ ሜዳ
ውጭ በአመራር ደረጃ በምረጡኝ ዘመቻ ሌላ
ችግር ነው ያየሁት ምናለበት እኔም ትቻለሁ
እኔም ትቻለሁ ቢሉ? ክለቦችና ደጋፊዎችም
ውድድሩ የኳስ እንጂ የቦክስ የድንጋይ
ውድድር አይደለም፡፡ የኳሱም ሆነ የቦክሱ
የራሱ ውድድር አለው እዚያ ላይ መሳተፍ
ይቻላል፡፡ በኳሱ ሽንፈት ሲገጥም በድብድብ
መሸፈን 2ኛ ሽንፈት ይመስለኛል፡፡
ሃትሪክ፡- አትሌቲክሳችን በመላው አለም
አለው የሚባለው ዝና አሁንም የተጠበቀ ነው
ማለት ይቻላል?
ሃይሌ፡- በተባበሩት መንግስታት
ድርጅት ቪቶ ፓወር /ድምፅን በድምፅ
የመሻር መብት/ ያላቸው 5 አገራት አሉ፡፡
በአትሌቲክሱም 5 አገራት የገነነ እና ክብር
የሚሰጠው ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ፣
ኬኒያ፣ጃማይካ፣አሜሪካና ሩሲያ የአትሌቲክሱ
ሃይላን መሆናቸው የታወቀና የታመነ ነው፡፡
ሃትሪክ፡- አትሌቲክሱ መምራትና
መወዳደርን እንዴት ትገልፀዋለህ?
ሃይሌ፡- ማራቶን ስትሮጥ ቢደክምህም
ተደስተህ ትወጣለህ፤አትሌቲክስ በሁሉም
ስፖርት ውስጥ አለ፡፡ እግር ኳስ፣ ቦክስ፣
ቴኒስ፣ ቅርጫት ኳስ ሁሉም ስፖርት ውስጥ
ሩጫ አለ፡፡ ይህ ሁሉም ስፖርትን ያካትታል፡
፡ እግር ኳስን ብታይ አትሌቲክስ ውስጥ
የለም በኳስ ውስጥ ግን አትሌቲክስ አለ፡፡
ይህንን ስፖርት መሮጥም ሆነ መምራትም
ደስ ይላል፡፡ በሩጫ ዘመኔ ስለማገኘው ድል
ነው የምለፋው፤አሁን ግን ስለአትሌቶችና
አሌቲክስ ነው የማስበው ለራስ ማሰብና
ለጋራ መጨነቅን አይቻለሁ፡፡
ሃትሪክ፡- እየተመዘገቡ ባሉ ውጤቶች
ዙሪያ የኛ እጅ አለበት ማለት ትችላላችሁ?
ሃይሌ፡- እኛ ሰራን ብለን የምንፎክረው
ነገር የለም፡፡ ያደረግነው አቀናጅተን
ለአትሌቶቹ ሞራል መስጠት ብቻ ነው፡
፡ እኔ ፈጠርኩ ሰራሁ የሚል ካለ ግብዝ
ነው ማለት ነው ይሄ የአመታት በርካታ
አመራሮች ልፋት ውጤት ነው ለቀድሞዎቹ
ክብር መስጠት የግድ ይላል፡፡ ውጤቱ
የነርሱ ነውና የኛ ትልቁ ችግር ስልጣን
ሲያዝ የባለፈውን ጉድፍ ማውጣት በሁሉም
ቦታ ላይ ይታያል፡፡ በሁሉም ቦታ ላይ
የሚታይ ችግር ይመስለኛል፡፡ አንድ መስሪያ
ቤት ስትገባ አዲሱ ተሿሚ የመጀመሪያ ስራ
ያለፈውን አመራር ስራ መተቸት ነው ይሄ
አይዋጣም፡፡ እንደ አገር ማስተካከል ያለብን
ይህን ባህሪ ነው በርግጥ የተሻለ ወስዶ
ደካማውን መተው የቻለ አመራር ሊሞገስ
ይገባል፡፡ ስፖርቱ አካባቢም ይህን ማረም
የግድ ነው ለመመረጥ የባለፈውን አመራር
ችግር መጥቀስና ለማሻሻል እሰራለሁ ማለት
የግድ ነው፡፡ ቦታው ከተያዘ በኋላ ግን ሲታይ
የቀድሞዎቹ አመራሮች የየራሳቸውን አሻራ
ትተው ማለፋቸውን ማመን አለብን፡፡
ሃትሪክ፡- ብሄራዊ ቡድን በተመለከተ
ፈርሷል ወይስ አልፈረሰም?
ሃይሌ፡- አልፈረሰም መንገዱን ነው
የቀየርነው፡፡ በፊት በፊት በብሄራዊ ቡድን
ደረጃ ታቀፍኩ ብሎ አንድ ውድድር
ከተካፈለ በኋላ ሲመለስ ይኮፈሳል ከርሱ
ውጪ ሌላው የማይችል ወይም የማይጠቅም
አድርጎ ያያል ለአሰልጣኞችም ያስቸግራል፡
፡ ይሄን ለማስተካከል በመላው አገሪቱ ያሉ
አትሌቶች የብሄራዊ ቡድን አባላት እንደሆኑ
እንዲሰማቸው አድርገናል፡፡ ይሄ ነው
ለአገራችን የሚጠቅመው፡፡
ሃትሪክ፡- ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን
ሼቦ እና አሰልጣኝ ቶሌራ ዲንቃ ብሄራዊ
ቡድኑ ፈርሷል እያሉኮ ነው?
ሃይሌ፡- የብሄራዊ ቡድን ምስረታን
አቅጣጫ ስናስተካክል ምርጥ ውሳኔ ነው
ያለው አንደኛው አሰልጣኝ ቶሌራ ዲንቃ ነው
(ሳቅ በሳቅ)፡፡ ሚዲያ ላይ ወጥተው ከተቹት
መሃል ደግሞ አንዱ ይሄ ባለሙያ ነው
ለመናገር ፈልገው ካልሆነ በቀር የቀድሞው
አካሄድ ልክ አይደለም የዘንድሮው አካሄድ
ይሻላል የሚሉ በርካታ አትሌቶች አሉ፡፡
አሁንኮ በርካታ አትሌቶች ካሰብነው ፈጥነው
እየመጡ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
በቀጣይ ደግሞ የስራችንን ውጤቱን አብረን
እናየዋለን፡፡
ሃትሪክ፡- ወደ እግር ኳሱ እንምጣና
ከምርጫው ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ
ውዝግቦችን ለማብረድ እነ ሃይሌ እየሞከሩ
ነው የሚል ነገር ሰማሁ እዉነት ነው?
ሃይሌ፡- የማስታረቅ ስራ ሳይሆን
የምናየው ነገር ደስ የማይል ነው፣ ያዙኝ
ልቀቁኝ አለበት በ2000 ዓ.ም ከነፕሮፌሰር
ኤፍሬም ይስሃቅ ጋር ሆነን የተፈጠረውን
ችግር ለማስወገድ አሸማግለን ነበር፡፡ አሁንም
አለመግባባቱ ደስ አይልም ጥቅምን ማሰብ
ችግር የለውም ሌሎች እስኪታዘቡ ድረስ
የአገርን ጥቅም አሳልፎ መስጠት ግን በጣም
አሳፋሪና የወረደ ተግባር ነው፡፡ ማንም
ይስራው ማንም ተገቢ አይደለም የሚል
አቋም ነው ያለኝ፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን ባለማድረጓ ይህን
ፃፉበት እንዲህ አድርጉባት እያሉ የሚልኩ
ሰዎች ተገቢ ስራ አልሰሩም ከቻልኩና
ከበረታሁ በግሌ እታገላለሁ እንጂ ኢትዮጵያ
እንዲህ አድርጋለች ብዬ አልፅፍም፡
፡ በአትሌቲክሱ ምርጫ ያሰብኩት ሳይሆን
ባልመረጥ ራሴን አገላለሁ እንጂ አገሬን
አሳልፌ አልሰጥም፡፡ ለዘመናት የተሞተላት
አገር ናትኮ፡፡ ምናልባት ተሳስቼ ይሆናል
ለፊፋ በፃፉት ሰዎች አዝናለሁ፡፡ እኛኮ
የአፍሪካ መሪ ነን፡፡ ፊፋኮ እንደ ይድነቃቸው
አገርነታችን ተሰሚነት አላት ከሚላቸው
አገሮች አንዷ ነን፡፡ ዛሬ ለሌላው አልተመቸም
ሲባል ያስፈራል፡፡ ነገ ሃይሌ ለምን እንዲህ
አለ ብዬ እተች ይሆናል ነገር ግን በአገሬ
ጉዳይ ያለኝ አቋም ይሄ ነው፡፡ ብዙ አገር ዞሬ
የኛ ደረጃ ትልቅ እንደሆነ አይቻለሁ፡፡ ይህን
ሁሉ ትተን ያዙኝ ልቀቁኝ እያልን መቀጠል
አለብን እንዴ? ከዚህ በኋላስ ያሸነፈው
አመራር ፊፋና ካፍ ጋር ሲሄድ ምን አይነት
ሞራል ይዞ ነው?
ሃትሪክ፡- ሃይሌ የአትሌቲክስ ሰው ነው
ኳስ ውስጥ ምን ጥልቅ አደረገው ቢባል
ምላሽህ ምን ይሆናል?
ሃይሌ፡- እኔስ የኳሱ ሰዎችን ለምን
አትሌቲክስ ውስጥ ገባችሁ እላለሁ እንዴ?
ስፖርትኮ ነው ጋሽ ይድነቃቸው እግር ኳሱን
ብቻ ሳይሆን አትሌቲክስንም መርተዋልኮ፡
፡ ምንም ይሁን ምን ስለኢትዮጵያ እከሌ
ያገባዋል እከሌ ደግሞ አያገባውም ማለት
አይቻልም፡፡ እንኳን እኔ ገና ኢትዮጵያ ሆኖ
ሊወለድ የተፀነሰም ልጅ ያገባዋል፡፡ እኔ
የማየውና የምረዳው በአገሩ ማንም ሰው
አያገባውም ሊባል አይገባም ለውዝግቡ መነሻ
የሆኑ ሰዎች ለኢትዮጵያም ሲሉ ከምርጫው
ወጥተናል ቢሉ ይከበራሉ እንጂ አይዋረዱም
ግን ግን ውስጡ ምን እንዳለ ታውቃለህ?
ይህን ያህል የሚያጨቃጭቀው ፌዴሬሽን
ውስጥ ምን ቢኖር ነው?
ሃትሪክ፡- የፎርብስ መፅሔት በየወሩ
የአለማችን ሃብታም ሰዎች ዝርዝር ያወጣል
ሃይሌስ የቱ ጋር ነው?
ሃይሌ፡- ማን መዘገበንና (ሳቅ በሳቅ)
ብዙ ለማድረግ እየጣርኩ ነው፡፡ ፎርብስ
ውስጥ ሳንገባም አንሞትም (ሳቅ) ካልገባንማ
ሞተናላ!
ሃትሪክ፡- 2018 የፈረንጆች አዲስ አመት
ተጀምሯል ሃይሌ ለኢትዮጵያ ምን ይመኛል
የሚለውን የመጨረሻችን ብናደርገውስ?
ሃይሌ፡- ለኢትዮጵያ በዚያ ጊዜ
የምመኘው ሰላምና ፍቅርን ነው፡፡ ሰዎች
በሰላም የሚኖሩባት አንቺ ትብሽ አንተ
ትብስ የሚባባሉበት አገር እንድትሆን ነው
የምመኘው፡፡ ሁላችንም የአዳም ዘር አንድ
ነን የሁሉም ክለብ ደጋፊዎች የጊዮርጊስ
ይሁን የቡና፣የሲዳማ ይሁን የመቀሌ
እንደዚሁም የሌሎች ክለቦች ደጋፊዎች
ፈልገውና መርጠው ሊደግፉ ይችላሉ ነገር
ግን ያሉበት ዘር መርጠውና ፈልገው የመጣ
ሳይሆን አባቶቻችን እናቶቻችን የመጡበት
በመሆኑ ልንጣላበት አይገባም፤ እናም ይሄ
ሁሉ ልዩነት ወደ አንድ መስመር መጥቶልን
ኢትዮጵያችንና ኢትዮጵያዊነት አብቦ
ድሮ እንደምንፋቀረውና እንደምንናፍቀው
በውጭም ይሁን በአገር ውስጥ ያለን
ኢትዮጵያዊያን በ2018 በጋራና በፍቅር
የምንኖርበት አመት እንዲሆንልን እመኛለሁ።