“ፋሲል ማንኛውም አሰልጣኝ የሚመኘው ክለብ በመሆኑ ኩራት ይሰማኛል”
የፋሲል ከተማ እግር ኳስ ቡድን ሲነሳ
የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት መሆኑ፣ ሊጉን
በተቀላቀለበት ዓመት ጠንካራ ተፋላሚ
ከመሆን ያለፈ ሃያላን ክለቦችን ድል የነሳ
የሚለው ከሌሎች ነገሮች ቀድሞ ከፊታችን
ድቅን ይላል፡፡ ያም ቢሆን ታዲያ የክለቡ
አሰልጣኝ ዘ/ማሪያም ወ/ጊዮርጊስ “ጥቂት
ናቸው” በሚላቸው ደጋፊዎች ጫና ራሱን
ከአሰልጣኝነት አንስቷል ወይም ተሰናብቷል
የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ሰንብተዋል፡፡
አሰልጣኝ ዘማሪያም 250ሺህ ብር አካባቢ
ከግሉ ወጪ አድርጎ ለመታከም ወደ ታይላንድ
ባንኮክ ከመጓዙ ጥቂት ሰዓታት በፊት በእሱና
በክለቡ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ከጋዜጠኛ
ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ያደረገው ቆይታ ይህን
ይመስላል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ፡- አሁን ጤናህ እንዴት
ነው…?… ታይላንድስ የምትቆየው ለስንት
ቀን ነው?
ዘማሪያም፡- ከመጀመሪያው ህክምና
በኋላ 3 ወር ቆይቼ እንድመለስ በሀኪሙ
ቢነገረኝም ፋሲል ከነበረበት ወሳኝ ሰአት
አንፃር በተሰጠኝ የጊዜ ቀጠሮ መሰረት
መሄድአ ልቻልኩም፤ አንድ ወር ያህል
አሳልፌያለሁ፡፡ ዶ/ሩም ቶሎ መምጣት
አለብህ ብሉ ስለነገረኝና ከዚህ በላይ መዘግየት
የራሱ የሆነ ችግር ስለሚያስከትል ዛሬ
ምሽት መጓዝንመርጫለሁ። /ቃለ-ምልልሱን
የሰራነው ሀሙስ ምሽት ነው/
ሀትሪክ፡- አንድ ወር መቆየትህ ጤናህ
ላይ የፈረድክስ አልመሰለህም?
ዘማሪያም፡- ለፋሲል ማህበረሰብ ያለኝ
ፍቅር ከዚህ በላይ እንዳደርግ ያስገድደኛል፤
በነገራችን ላይ አንድ ወር መቆየቴ የተወሰነ
ችግር ጤናዩ ላይ ሊያመጣ እንደሚችል ግልፅ
ነው፡፡ አንደኛው ኦፕራሲዮን አድርጌ ሰመጣኮ
በመጣሁ በ5ኛው ቀን ጅማ ላይ ፋሲልን
እየመራሁ ሄጄ ጅማ አባቡናን 3ለ1 በረታንበት
ጨዋታ ከእነ ህመሜ ነው የገባሁት፤ ማረፍ
እያለብኝ ነው ወደ አሰልጣኘነቴ የተመለስኩት፡
፡ቡድኑ ጨዋታ እያለው አላስቻለኝም፤ አሁን
ወደ ባንኮክ የምጓዘው የ15 ቀን ቪዛ ይዤ ነው
፤ቀኑ እንደ ዶክተሮቹ ሊያጥርም ሆነ ሊረዝም
ይችላል፡፡ ከ15 ቀን በላይ ከሆነ ሆስፒታሉ
ቪዛውን ማደስ ይችላል፡፡
ሀትሪክ፡- በዚህ መልኩ ከምታስብለት
ክለብህ ጋር በዚህ መልኩ መለያየትህ ምን
ስሜት ፈጠረብህ?ውለታህ ያልተቆጠረ
የተገፋህ ያህል አልተሰማህም?
ዘማሪያም፡- የሆነ የህመም ስሜት
አለው፤ ከደጋፊው፣ከቦርዱና ከደጋፊ ማህበሩ
ጋር ያለኝ ግንኙነት የፍቅር ያህል ነው፤
በመከባበር በመፈቃቀር ላይ ያጠነጠነ በመሆኑ
ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ጥቂት ደጋፊዎች ናቸው
አላሰራ ያሉኝ፡፡ ስድቡ ወደ ግላዊ ጥቃት
የማተኮር አዝማሚያ እንዳለው ስረዳ ነው
ይሄን ውሳኔ የወሰንኩት፡፡
ሀትሪክ፡– የአንተን ከክለቡ መለያየት
ተከትሎ ብዙ እተባለ ነው …ለመሆኑ ከቦታው
ተባረርክ?… ወይስ… ሃላፊነትህን በፈቃድህ
ለቀክ…?… የትኛው ነው ትክክል…?
ዘማሪያም፡- አረ ያባረረኝም
የለም…! እነኚህ ጥቂት የሚባሉ ደጋፊዎች
ናቸው መግቢያና መውጪያ ያሳጡኝ፤
ሆቴል መጥተው ይሳደባሉ፣ መንገድ ላይ
ይተናኮሉናል፣ ወደ ጨዋታ ስንሄድ ይሸነፋሉ
ብለው ለመሳደብ ተዘጋጅተው ይመጡና
ስናሸንፍ የበለጠ ንዴታቸው ጨምሮ በይበልጥ
ሲሰድቡን ሳይ እያዘንኩ መጣሁ፤ ተሸንፈንም
አሸንፈንም ይሳደባሉ ጤናዬን የሰዋሁት
ለክለቡ ስል ነበር፤ አሁን ግን የቡድኑ
ውጤትና ጤናዩን ከማጣት ይልቅ ጤናዬን
ለመጠበቅ ራሴን አግልያለሁ፡፡ ከፋሲል ጋር
ያለኝ ታሪክ የማይረሳ የማይደበዝዝ በመሆኑ
የግንቦትና ሰኔ ወር ደምወዜን ጭምር ትቼ
ራሴን ከቦታው ዞር አድርጌያለሁ፡፡ የቦርዱ
አመራሮች ከህክምና መልስ ተረጋጋና ደገመን
ማድረግ ያለብንን ተወያይተን ወደ ቦታህ
ትመለሳለህ ቢሉኝም እኔ ግን በቃኝ ብዬ ራሴን
ከሃላፊነት አንስቻለሁ፤ዕውነታው ይሄ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ክለቡ በአሁን ሰዓት በ38
ነጥብ በ6ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው፤ይሄ
ደግሞ የሊጉ እንግዳ ለሆነ ቡድን መጥፎ
የሚባል ውጤት አይደለም፤ ክለቡን ለቀህ
እስክትወጣ የሚያደርስ ተቃውሞ የገጠመህ
የዘንድሮ የውድድር ዓመት ሲጀመር የፋሲል
ዕቅድ ምን ቢሆን ነው?
ዘማሪያም፡- እኔንም የገረመኝ ይሄው
ነው፤ በመጀመሪያው ዓመት በሊጉ መቆየት፣
በሁለተኛው ዓመት ጥሩ ቡድን መገንባት፣
በሶስተኛው ዓመት ደግሞ ለዋንጫ የሚፎካከር
ቡድን የመገንባት እቅድ ይዘን ነው የተነሳነው፡፡
በ2009 የፕርምየር ሊግ ጨዋታ ግን ካሰብነው
በላይ መጓዛችንና ዕቅዳችንን ማሳካታችን
በመጀመሪያው ዓመታችን ዋንጫ ካልመጣ
የሚሉ ሠዎች እንዲፈጠሩ አድርጓል፤
የተወሰኑ ሰዎች ዋንጫ መውሰድ አለብን
እያሉ ቡድኑን እንዲበጠብጡ አጋጣሚው
ዕድል ፈጠረላቸው፤ በተለይ ከኢት.ንግድ ባንክ
ጋር ተጫውተን 3ለ1 ከተሸነፍንበት የ25ኛው
ሳምንት ጨዋታ በኋላ እነዚህ ያልኩህ ጥቂት
የሚባሉ ደጋፊዎች ስለተሸነፍን ብቻ ቡድኑ
ሊወርድ ይችላል ብለው እስከሟሟረት ደረሱ፤
ፋሲል ግን በቀሪ 5 ጨዋታዎች 1 ነጥብ
ባያገኝ እንኳን እንደማይወርድ መረጋገጡ
አኩርቶኛል፡፡ በግሌ ካቀድኩት በላይ ስለተጓዝን
የምፀፀትበት ሳይሆን የምደሰትበት ዓመትን
አሳልፌያለሁ ባይ ነኝ፡፡ አሁን የተገኘውን
ውጤት ማንም አልጠበቀውም፤ በደቡብ
ሲቲ ካፕ ላይ 3 ጊዜ ስንሸነፍ እኮ የቦርዱ
አባላት በሊጉ መቆየታችንን ሲጠራጠሩ ነበር፡
፡ በኋላ ላይ ግን ውጤት ከጠበቁት በላይ ሆኖ
አግኝተውታል፡፡
ሀትሪክ፡– ፋሲል ከተማ ለፕሪምየር
ሊጉ እንግዳ ከመሆኑ አንፃር ከዚህ በላይ
መጠበቅ ይቻላል?ዋንጫን መመኘት በራሱ
ክፋት ባይኖረውም “ችኩል” የሚል ስያሜ
አያሰጥም?
ዘማሪያም፡- ኳስ የሚያውቅ ካለ
ከፋሲል ጋር ከዕቅድ በላይ መስራቴን ይረዳል፤
አብዛኛው ደጋፊ ይሄንን ጠንቅቆ ያውቃል፤
እየረበሹ ያሉት ሰዎች ናቸው የዋንጫ ዕቅድ
ያወጡት እንጂ ብዙሃኑ ደጋፊ አይደለም፡፡
በርካታ የፋሲል ማህበረሰብ ግን በዘንድሮው
የሊግ ውድድር ውጤት ደስተኞች ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- በዘንድሮው የሊግ ውድድር
ወደ 9 አሰልጣኞች የመሰናበታቸው ምክንያት
ምን ይመስልሃል?
ዘማሪያም፡- እኔንም ሲያስገርመኝ
የነበረው ይኸው ነው፤ ከእኔ ውጪ ሌሎች
በመሰናበትና በብሄራዊ ቡድን ሹመት
የተፈጠሩ ለውጦች ናቸው፡፡ በእኔ ግምት ይሄ
ቬንገር አውት / WENGER OUT/ የሚለው
ነገር ብዙ ችግር ያመጣ ይመስለኛል፤
በየክልል ለጨዋታ ስንጓዝ የአሰልጣኙን ስም
እየጠሩ /OUT/ ውጣ ማለት የተለመደ ወይም
አዲስ ፋሽን የሆነ ይመስለኛል፤ ከዚህ ይልቅ
ሌሎች መልካም ነገሮችን ብንኮርጅ የተሻለ
ይመስለኛል፡፡ እኔ በግሌ ግን ስለ ክለቦቹ
ውሳኔ ባልናገር እመርጣለሁ፤ለመልካም
ነገር ታስቦ ከሆነ እሰየው ነው፤እንደ ክለቦቹ
ሃሳብና ራዕይ እንደ ኮሚቴ አባላቱ አስተሳሰብ
የሚወሰን ይመስለኛል ብል ይቀለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- የክለባችሁ አመራሮች በአንተ
ላይ የተፈጠረውን ችግር ለማስወገድ ምን
ያህል ሞክረዋል?
ዘማሪያም፡- በደንብ ሞክረዋል፤ግን
ከአቅም በላይ ሆኖባቸው ሙከራው
አልተሳካም፡፡ ደጋፊዎቹኮ ከህግና ሥርዓት
ውጪ ስራ አስኪያጅ ቢሮ ድረስ ገብተው
ተሳድበው ዝተው እስከመውጣት ሁሉ
የደረሱ ናቸው፡፡ መስመር ያለፈ ተቃውሞ
ሲበዛ ጤናዬንም ደጋፊውንም ከማጣ ጤናዬን
ባቆይ ብዬ መራቅን መርጫለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ከህክምናህ መልስ የያዝከው
አዲስ ዕቅድ አለ?
ዘማሪያም፡- ለጊዜው ቅድሚያ ለጤናዬ
መስጠትን መርጫለሁ፤ ስለ ቀጣይ ዕቅዴ
ከባንኮክ መልስ የምወስንበት ጉዳይ ነው
የሚሆነው፤ ከተወሰኑ ከለቦች ጋር በቀጣይ
የአሰልጣኝነት ህይወቴ ዙሪያ ያናገሩኝ
እንዳሉ መደበቅ አልፈልግም፤ በእርግጠኝነት
የምናገረው ግን ስመለስ ሌላ ክለብ እንደማገኝ
ብቻ ነው፡፡ አሁን ግን ሁሉ ነገሬ ጤናዬ ላይ
ብቻ አተኩሯል፡፡
ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ቃል ካለህ?
ዘማሪያም፡- ፋሲል ሁልጊዜም
በቋሚነት በሊጉ እንዲቆይ የሚያስችለው
አቅም ተገንብቷል፤እንኳን አሁን እስከ 2010
ዓ.ም ድረስ በፍፁም አያሰጋውም፡፡ በግሌ
ፋሲል በሊጉ እስከቆየ ድረስ ደግሞ ታሪኬ
ሳይረሳ እየታወሰ እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነኝ፡
፡ ለክለቡ መልካም የውደድር ዘመን ፍፃሜ
የሚያገኝበት እንዲሆንም እመኛለሁ፡፡ የክለቡ
ቦርድ፣ የደጋፊዎች ማህበርና መላው የክለቡ
ደጋፊዎችን ከልብ ማመሰገንም እፈልጋለሁ፡
፡ ነገር ግን ለደጋፊው የምለው ይሄን ድንቅ
ክለብ ነቅቶ እንዲጠብቅ ነው፤ በተረፈ ፋሲል
የትኛውም አሰልጣኝ የሚመኘው አይነት ክለብ
በመሆኑ ኩራት ይሰመኛል፡፡