በመሸሻ ወልዴ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሶስተኛው
ሳምንት የጨዋታ መርሃ ግብር እሁድ
እለት በአዲስ አበባ ስቴድየም ላይ በዓምናው
የሊጉ ሻምፒዮና ቅዱስ ጊዮርጊስና ከከፍተኛ
ሊጉ ባደገው መቀሌ ከተማ መካከል ተካሂዶ
ግጥሚያው 1-1 በሆነ የአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ
ችሏል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስና የመቀሌ ከተማ ክለቦች
የእሁድ እለቱ ጨዋታቸው ለሻምፒዮናው
ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያው እና ለመቀሌ
ከተማ ደግሞ ሶስተኛው ጨዋታ የነበረ ሲሆን
ግጥሚያው በሁለቱ ክለቦች መካከል ደጋፊዎች
በመታጀብ የተደረገና እልህ አስጨራሽም
ስለነበር ትኩረትን ስቧል፤ በዕለቱ የጨዋታ
ፍልሚያም የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቡድን
የሆነው መቀሌ ከተማ በአጥቂው አማኑኤል
አማካይነት ባስቆጠሩት ግብ ጨዋታውን
ሲመሩ ቢቆዩም ግጥሚያው እየተካሄደ
በሄደበት የመጨረሻው ሰአት ላይ የቅዱስ
ጊዮርጊሱ ተከላካዩ ምንተስኖት አዳነ ከማዕዘን
ምት የተሻገረውን ኳስ በግምባሩ በመግጨት
ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን ከመሸነፍ ሊያድነው
ችሏል፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችንም
ከገቡበት የሃዘንና የትካዜ ስሜትም እንዲወጡ
በማድረግም ሊያስደታቸውም ችሏል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የመቀሌ ከተማ
ጋር ባደረገው ጨዋታ ግጥሚያውን በአቻ
ውጤት ሲያጠናቅቅ ግቧን ለቡድኑ ያስቆጠራት
ምንተስኖት አዳነን ስለጨዋታው፣ በመጨረሻ
ሰዓት ላይ እሱ ባስቆጠረው ግብ ቡድኑ አቻ
ስለመለያየቱና ሌላም አጠር ያለ ጥያቄዎችን
ጠይቀነው ተጨዋቹ ምላሹን እንደሚከተለው
ሰጥቶናል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስና የመቀሌ ከተማ ክለቦች
አቻ ስለተለያዩበት ጨዋታ
- ማሰታውቂያ -
‘‘የእሁድ ዕለት ጨዋታችንን ከመቀሌ
ከተማ ጋር ስናደርግ ፍልሚያው ከፕሪ
ሲዝን እንደመምጣታችንና እነሱም ገና ከታች
የመጡና በአዲስ ጉልበትም የሚጫወቱ
ከመሆናቸው አኳያ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
የመክፈቸው ጨዋታ ለእኛ በጣም ሊከብደን
እንደሚችል ጠብቀንና ገምተን ነበር፤
ለእዚያም ነው ያንን ጨምሮና በእለቱም
ጨዋታ ላይ ጥሩ ካለመሆናችን ጋር ተደምሮ
ግጥሚያውን ሳናሸንፍ የቀረነው”፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ አንተ በግምባርህ
ገጭተህ ባስቆጠርካት የመጨረሻው ሰአት ግብ
ነው አቻ የተለያየው፤ ግቧን ስታስቆጥር ምን
ስሜት ነው የተሰማህ….?
“የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ
ወደ ዋናው ቡድን በማደግ መጫወት
ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ ብዙ ጊዜ እንዲህ
ባሉ ወሳኝ ሰአታቶች ላይ ክለቤን ከሸንፈት
የምታደግባቸውንና ብሎም ቡድኔን ለድል
የማበቃበትን ግቦች የማስቆጠር ልምዱ ስላለኝ
የእሁድ እለትም ጨዋታ ላይ ከታችኛው
ሊግ በመጣው የመቀሌ ከተማ ቡድን ጋር
ስንጫወት ልንሸነፍ ጫፍ በደረስንበት ሰዓት
ላይ ለቡድናችን ከመሸነፍ የምንድንበትን
እጅግ በጣም የምታስፈልግና ደጋፊዎቻችንም
ብዙ እንዳያዝኑብንም ያደረገችንን የአቻነት
ግብ በግምባሬ በመግጨት ላስቆጥር ስችል
በጣም ነው የተደሰትኩት፤ ያን ዕለት
ለእዚያም ነው ጎሏን ካገባው በኋላም ደስታዬ
ከፍ ያለም ስለነበር ወደ ካታንጋ አካባቢ
በመሄድና አክሮባት በመስራትም ጭምር
ከደጋፊዎቻችንም ጋር ልደሰት የቻልኩት”፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስና የመቀሌ ከተማ ክለቦች
ግጥሚያቸውን ሲያጠናቅቁ 1-1 የሚል
ውጤት ተመዝግቧል፤ ውጤቱ ለእናንተ በቂ
ነበር ወይስ አይደለም….?
‘‘የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ መቀሌ ከተማን
በተፋለመበት ጨዋታ ማሸነፍን ፈልጎ ነው
አቻ የተለያየው፤ የእለቱ ጨዋታ ላይ እኛ
ግጥሚያውን በድል አለመወጣታችን በጣም
ነው ያስቆጨን፤ ያም ሆኖ ግን በእለቱ በሜዳ
ላይ ከነበረን አቋም አኳያ እኔ ባስቆጠርኩት
ብቸኛ ግብ ጨዋታችንን በአቻ ውጤት
ማጠናቀቃችን ለእኛ በቂ የሚያስብለን ውጤት
ነበርና ያንን አምነንም ነው የተቀበልነው”፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስና የመቀሌ ከተማ ክለቦች
በጨዋታው ወቅት የነበራቸው አቋም ምን
መልክ ያለው እንደነበር…
“የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ መቀሌን
በተፋለመበት ጨዋታ የነበረውን አቋም
በተመለከተ ሁላችንም እንደጠበቅነው
አይደለም ልንንቀሳቀስ የቻልነው፤ በጨዋታው
ጎል ጋር በተደጋጋሚ በመድረስና አስፈሪ
የሚባሉ ሙከራዎችን እንደሌላው ጊዜ ማድረግ
አልቻለንም ነበር፤ ብዙ ነገሮች ከብደውን
ነበር፤ የመቀሌ ከተማ ቡድንን በተመለከተ
ጥሩ ቡድን ነው ያላቸው፤ ብዙዎችም በሊጉ
ላይ የተካበተ ልምድ ያላቸውም ናቸው፤
አዳዲስ የሆኑና ጥሩ ችሎታ ያላቸው ወጣት
ተጨዋቾችንም ክለቡ ይዟል፤ ያም ሆኖ ግን
የእዚያን እለት የእነሱ አጨዋወት ለእኛ
ብዙም የሚያመች አልነበረምና የአቻነትን
ውጤት ከመፈለግ አኳያ ከኳስ ጀርባ በመሆን
የሚጫወቱበትንም አይነት እንቅሰቃሴንም
ይከተሉ ስለነበር የእኛ ጥሩ አለመሆንና
ለቡድናችንም የማጥቃት አማራጭ ላይ
ያሉት ልጆቻችንም በጉዳት ላይ ስለነበሩም
በሁለታችን መካከል የተደረገው ግጥሚያ
በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል”፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ
የተከላካይ ቦታ ላይ ስለመጫወቱ፤ በእዚያው
የምትቀጥልስ ይመስልሃል….?
“የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ ባለኝ
ቆይታዬ ያለ እረፍት ረጅሙን ጊዜዬን የመሃል
ተጨዋች በመሆን ቡድኑን አገልግያለሁ፤ ጎል
በማስቆጠርና ቡድኔንም ለስኬት እንዲበቃ
በመርዳትም ጭምር ጥሩ ወቅትን ከክለቡ
ጋር ላሳልፍም ችያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ
የአዲስ የጨዋታ ሚናን አጥብቄ የፈለግኩ
ተጨዋች ስለሆንኩኝ የተከላካይ ስፍራው ላይ
ለመጫወት በመፈለግ እዚያ ላይ ተደጋጋሚ
ሙከራን እያደረግኩኝ ነው፤ እዚያ ቦታ ላይ
በእርግጥ ከዓመት በፊትም የተጫወትኩበት
አጋጣሚ ነበር፡፡ አሁን ግን የእኔ ውሳኔ
በመሆኑ ከክለቡ ጋር በእዚያ ስፍራ ላይ
ለመጫወት መፈለጌን ጠቅሼና ተነጋግሬበት
በቦታው ላይ በመጫወት ጥሩና አበረታች
ጅማሬን እያሳየው ነው ያለው፤ በእዚያ ቦታ
ላይ የምትቀጥል ይመስልሃል ለሚለው ጥያቄ
ወደፊት የሚፈጠረው ነገር ባይታወቅም እኔ
ግን አዎን የተከላካይ ቦታው ላይ ካሉት
ተጨዋቾች ጋር በመፎካከር መጫወትን
እፈልጋለው ነው የምለው”፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ የሊግ አጀማመር
በአቻ ውጤት ከመሆኑ አንፃር፤ ስለቀጣይ
ግጥሚያችሁስ ምን ትላለህ…?
‘‘የቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ፕሪምየር
ሊግ አጀማመርን በአቻ ውጤት መሆኑን
ተንተርሶ ነጥብ በመጣላችን ዙሪያ ብዙ
ቢባልም ያ እኛን ፈፅሞ ስጋት ውስጥ የሚከተን
አይደለም፤ እንዲህ ያሉ አጀማመሮች ከዚህ
ቀደምም ገጥመውን ያውቃሉ፤ በቀድሞ
ጊዜም እንዲህ ያሉ አጀማመሮች ቡድኑን
አጋጥመውትም ያውቃሉ፤ አሁን ግን ሊጉ ገና
መጀመሩ ነው፤ ገና ደግሞ 29 ጨዋታዎች
በሊጉ አሉን፤ ቡድናችን ለእንደነዚህ አይነት
ጅማሬዎችም አዲስ አይደለምና የቀጣዩ
ጨዋታዎቻችን ላይ ያሉብንን ከፍተቶች
በመድፈን የሊጉ የመሪነት ዙፋንን በአጭር
ጊዜ ውስጥ እንደምንረከብ በጣም እርግጠኞች
ነን፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን
በሚመለከትና ስለሚያስተላልፈው መልዕክት
“የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ለቡድናችን
ውጤታማነት ሁሌም ቢሆን እኛን
በማበረታታት በኩል ከጎናችን ሆነው ልዩና
ከፍተኛ ድጋፍን የሚያደርጉልን ናቸው፤
ያማረ የስቴድየም ድጋፍን በመስጠት እኛን
ያነቃቁናል ለእዚያ እነሱ ሊመሰገኑ ይገባል፡
፡ ያም ሆኖ ግን የእሁድ እለት ጨዋታ ላይ
የእኛ ክለብ ውስጥ በደጋፊዎቻችንም ሆነ
በተጨዋቾች ዘንድ መሸነፍንና አቻ መውጣትን
ፈፅሞ የማንፈልገው በመሆኑ ለደጋፊዎቻችን
እንደሚሰጡን ድጋፍ የአቻ ውጤት
አይገባቸውም፤ ለእዚያም ነው ቡድኑ ውስጥ
እንደዚያ ያሉ ውጤቶች ሲመዘገቡ ውጤቱ
እምብዛም ስላልተለመደም መከፋታቸውን
ያወቅነው፤ ስለዚህም የእነሱን ደስታ እኛ
በሚገባ ስለምናውቅ የቀጣይ ጨዋታዎች ላይ
ወደ ስኬታማነት በመመለስ በተለያዩ የድል
ውጤቶች እነሱን እንክሳቸዋለን”፡፡