በመሸሻ ወልዴ
መቐለ 70 እንደርታ በፕሪበመቐለ ሊጉ
የ28ኛው ሳምንት ጨዋታው በወራጅ ቀጠና
ላይ የሚገኘውን ደቡብ ፖሊስን 4ለ0 በማሸነፍ
ከሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ጋር ያለውን የሁለት
ነጥብ ልዩነት በማስተካከል አሁን ላይ በእኩል
ነጥብ ሊጉን በጋራ እየመሩት ሲገኝ ፋሲል
ከነማ የቅድሚያ ስፍራ ላይ ሊቀመጥ የቻለው
በግብ ክፍያ በመብለጥ ብቻ ነው፡፡
የመቐለ 70 እንደርታ እግር ኳስ ክለብ
የፕሪምየር ሊጉን በግብ ክፍያ እየመራ
ከሚገኘው ፋሲል ከነማ ጋር ዋንጫውን
ለማንሳት እየተፎካከረ ባለበት የአሁን ሰዓት
ላይ የቡድኑ የግራ መስመር የአማካይ
ስፍራ ተጨዋች ሄኖክ ኢሳያስ ቡድናቸው
የዘንድሮውን የሊግ ዋንጫ የሚያነሱበት
ዕድል እንደተመቻቸላቸውም ይናገራል፡፡
የመቐለ 70 እንደርታው ሄኖክ በዚህ
ዙሪያም አስተያየቱን ሲሰጥ “መቐለ የፕሪምየር
ሊጉን ዋንጫ የማንሳት እድሉ የሚወሰነው
ከመከላከያ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ነው፤
ግጥሚያውን ማሸነፍ ይኖርበታል፤ ስለዚህም
ከእነሱ ጋር የሚኖረን ጨዋታ የዋንጫ ነው
ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል፤ የመቐለ 70
እንደርታው ሄኖክ ጋር በክለባቸው የፕሪምየር
ሊግ የውድድር ዙሪያና በራሱም የኳስ
ህይወት ቆይታው ላይ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ
/G.BOYS/ አናግሮት ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ጅማሬህ ምን
ይመስላል?
ሄኖክ፡- የእግር ኳስን መጫወት
የጀመርኩት ተወልጄ ባደግኩበት የሐረር
ከተማ ጀጎል አካባቢ ነው፡፡
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ፡- በቤተሰብ ውስጥ የእግር
ኳስን የምትጫወተው አንተ ብቻ ነህ? ስንት
ወንድምና አህት አለ?
ሄኖክ፡- በቤተሰባችን ከሚገኙት መካከል
የአሁን ሰዓት ላይ የእግር ኳስን የምጫወተው
እኔ ብቻ ነኝ፤ አክስቴ ቀድሞ እንደነገረችኝ
ከሆነ ደግሞ አሁን ላይ በህይወት የሌለው
ወላጅ አባቴም ኳስን ይጫወት ነበር፤ እኛ
ቤት ውስጥ አሁን ያሉኝ እህቶች ሶስት ሲሆኑ
አንድ ወንድምም አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን ስትጫወት
ቤተሰብ አካባቢ የነበረው አመለካከት እንዴት
ነበር?
ሄኖክ፡- ቤተሰቦቼ ትምህርት ላይ
እንዳተኩር የሚፈልጉ ቢሆንም ያኔ ኳስ
መጫወቱም ላይ አይጫኑኝም ነበር፤
ስለዚህም የምወደውን እና የማፈቅረውን ኳስ
በመጫወት እና ጠንክሬም በመስራት ነው
የዛሬው ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻልኩት፡፡
ሀትሪክ፡- ወደ ክለብ ተጨዋችነት እንዴት
ገባህ?
ሄኖክ፡- የእግር ኳስን ስጫወት ወደ ክለብ
ደረጃ የገባሁት ባህርዳር ላይ በተካሄደው
ውድድር ሐረርን ወክዬ በፕሮጀክት ደረጃ
ስጫወት ነው፤ ያኔም ደደቢቶች አይተውኝ
ነው ለወጣት ቡድናቸው ሊያስፈርሙኝ
የቻሉት፡፡
ሀትሪክ፡- ደደቢት የመጀመሪያው ክለብህ
ነው፤ ቆይታህን እንዴት ትገልፀዋለህ?
ሄኖክ፡- ደደቢት ከወጣት ቡድኑ
አንስቶ እስከዋናው ድረስ የተጫወትኩበት
እና ለዛሬም ጥሩ የኳስ ህይወቴ መንገዱን
የከፈተልኝ ቡድኔ ነው፤ በዚህ ቡድን ውስጥም
ለስምንት ዓመታት ያህልም ተጫውቻለው፤
በዚህ ቡድን ቆይታዬም የፕሪምየር ሊጉን
ዋንጫ ያነሳው ስለሆንኩም በዚህ በጣም
ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
ዋንጫን ከደደቢት ክለብ ቆይታህ በኋላም
ዓምናም ከጅማ አባጅፋር ጋር ለማንሳት
ችለሃል…
ሄኖክ፡- አዎን፤ ይህን የሊግ ዋንጫ
ከአንዴም ሁለት ጊዜ በወጣትነት እድሜ ላይ
ማግኘት መቻል መታደል ነውና የእኔ ደስታ
ልዩ ሊሆንልኝ ችሏል፤ ዘንድሮ ደግሞ ፈጣሪ
አሳክቶት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ዋንጫ
ማግኘት ከቻልኩ የዋንጫ ቁጥሬ ሀትሪክ
ይሆንና ደስታዬ የበለጠ የሚጨምርልኝም
ይሆናል፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን ልጅ ሆነህ
መጫወት ስትጀምር ተምሳሌትህ ማን ነበር?
ሄኖክ፡- የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ
ነበርኩና ሪያን ጊግስ ነበር ሞዴሌ፤ ለእሱ
ችሎታ ልዩ አድናቆት ነው ያለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታን
በፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎ እንዴት
አገኘኸው? ጠንካራ እና ደካማ ጎናችሁ ምን
ነበር?
ሄኖክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
ላይ ያለንን የዘንድሮ ተሳትፎአችንን በሁለት
መልኩ ነው የምገልፀው፤ ውድድሩ ሲጀመር
እኔ የቡድኑ ተጨዋች ያልነበርኩ ቢሆንም
በጥሩ የውጤታማነት ጉዞ ላይ ነበር ይሄድ
የነበረው፤ በሁለተኛው ዙር ላይ ክለቡን
ስቀላቀል ደግሞ ከሜዳ ውጪ ባደረግናቸው
ጨዋታዎች ተደጋጋሚ የውጤት ማጣት
ስላጋጠመን እና በሜዳችንም ነጥብ የጣልንበት
ሁኔታ ስለነበር በዚህ የሊጉን ውድድር በሰፊ
ነጥብ ልንመራ የምንችልበትን ውጤት
አሳጥቶን በፋሲል ከነማ እንዲደረስብን
አድርጓል፤ አሁን ላይ ደግሞ በድጋሚ ወደ
ውጤታማነት ልንመለስ ችለናል፡፡
የመቐለ 70 እንደርታ ጠንካራው ጎን
አንድነታችን እና ህብረታችን ነው፤ ከዛ
ውጪም አሰልጣኛችን ገብረ መድህን ኃይሌ
የሚሰጠንን ጥሩ እና ወጣ ያለ ስልጠናን
በሜዳ ላይ ተግባራዊ ማድረግ መቻላችን
ነው፤ ክፍተት ጎናችን ደግሞ የሜዳ ውጪ
ግጥሚያዎቻችንን አለማሸነፍ መቻላችን ነው፡
፡
ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታ፣ ፋሲል
ከነማ እና ሲዳማ ቡና የፕሪምየር ሊጉን
ዋንጫ ለማንሳት ተፋጠዋል፤ በውድድሩ
መጨረሻ ማን ባለድል ይሆናል? ለእናንተስ
ከሁለቱ ስጋት የሚሆንባችሁ ክለብ ማን
ነው?
ሄኖክ፡- የዘንድሮውን የፕሪምየር
ሊጉን ዋንጫ የምናነሳውማ እኛ ነን፤
ይህም ድል ከመከላከያ ጋር በምናደርገው
ጨዋታ ይወሰናል፤ ለዋንጫው ለእኛ ስጋት
የሚሆንብንም ክለብ ሲዳማ ቡና ነው፡፡
ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታ ደቡብ
ፖሊስን ያሸነፈበት ጨዋታ የፋሲል ከነማን
አቻ መውጣት ተከትሎ በነጥብ እንዲጋራ
አድርጎታል፤ ግጥሚያው ምን መልክ ነበረው?
ሄኖክ፡- ደቡብ ፖሊስን በሰፊ የግብ
ልዩነት ያሸነፍንበት ጨዋታ ለእኛ ጣፋጭ
የሆነልን ድል ነው፤ ጨዋታውን ለመርታት
የአሰልጣኛችንን ምክር በሚገባ መስማት
መቻላችን ጠቅሞናል፤ ደቡብ ፖሊስ
ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን ነው፤ ያን
ስለምናውቅም አሰልጣኛችን ለእነሱ ጊዜ
መስጠት እንደሌለብን እና ጎልም ቶሎ
ማስቆጠር እንዳለብንም ስለነገረን ያንን ጎል
ማስቆጠር ከ16ኛው ደቂቃ አንስቶ ተግባራዊ
ስላደረግን እና እነሱም ጎል ሲቆጠርባቸው
በእንቅስቃሴ እንዲወርዱ ስላደረግን በዚህ ባለ
ድል ልንሆን ችለናል፡፡
ሀትሪክ፡- በህይወት ዘመንህ በጣም የተደ
ሰትክበት እና የተከፋክበት አጋጣሚ የቱ ነው?
ሄኖክ፡- በጣም የተደሰትኩት የፕሪምየር
ሊጉን ዋንጫ ዓምና ከጅማ አባጅፋር ክለብ
ጋር ስናገኝ ነው፤ የተከፋሁትና ያዘንኩት
ደግሞ ወላጅ እናት እና አባቴን በሞት ያጣው
ጊዜ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የመቐለ 70 እንደርታን
አሰልጣኝ እንደዚሁም ደግሞ ደጋፊዎቻችሁን
በምን መልኩ ነው የምትገልፃቸው?
ሄኖክ፡- የመቐለ 70 እንደርታው
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን ከወቅኩበት
ጊዜ ጀምሮ ለእሱ የማሰልጠን ችሎታ ከፍተኛ
ክብር እና አድናቆትም ነው ያለኝ፤ በደደቢት
ክለብ የተጨዋችነት ዘመኔ እኔን ከወጣት
ቡድኑ ችሎታዬን አይቶ ያሳደገኝ እሱ ነው፤
ወደ ጅማ አባቡናም ባመራሁበት ጊዜ ወደ
ክለቡ ያመጣኝ እሱ ነው፤ አሁንም ከወላይታ
ድቻ ወደ መቐለ 70 እንድራታ በሁለተኛው
ዙር ቡድኑን እንድጠቅም በድጋሚ ጠርቶኝ
በክለቡ ጥሩ ጊዜን እያሳለፍኩ ስለሆነ ይሄ
ያስደሰተኛል፡፡
የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎችን
በተመለከተ እነሱ እስከ 60 እና 70 ሺህ
ደጋፊዎች በመሆን የሚሰጡን ድጋፍ ልዩ
ነው፤ ለውጤታማነታችንም ማማር የእነሱ
ከፍተኛ አስተዋፅኦም አለበትና ሊመሰገኑ
ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት
የወደፊት ምኞትህ?
ሄኖክ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን
በመመረጥ ሀገሬን ማገልገል እፈልጋለው፤
ይሄን እድል ከዚህ በፊት ዕድሜያቸው
ከ23 ዓመት በታች ለሆነው የባሬቶ ቡድን
ውስጥ ተመርጬ ተጫውቼ ነበርና ሀገርን
ማገልገል የሚሰጠው እርካታ ከፍ ያለ ስለሆነ
በድጋሚ መመረጥን እፈልጋለው፤ ከዛ
ውጪም በፕሮፌሽናል ተጨዋችነትም ከሀገር
በመውጣት የመጫወት ፍላጎቴ ከፍተኛ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…..?
ሄኖክ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት
ህይወቴ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የረዱኝን
ማመስገን እፈልጋለው፤ መጀመሪያ ለፈጣሪዬ
ነው ምስጋናዬን የማቀርበው በመቀጠል
ለቤተሰቦቼ ማለትም ላሳደገችኝ አያቴ፣
ለአክስቴ፤ ለአክስቴ ባል እንደዚሁም እኔን
ከታዳጊነት እድሜ አንስቶ ላሰለጠኑኝ ነፍሱን
ፈጣሪ ይማረው ለፋሲል ተወልደ ለዳንኤል
ፀሐዬ ለገብረመድህን ኃይሌ እና ብዙ ነገር
ላደረገችልኝ ለታናሽ እህቴ ዮርዲ ከፍተኛ
ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው፡፡