በ11ኛ ሳምንት የኢትዮጽያ ፕሪሚየር ሊግ ሐዋሳ ከተማ ከኢትዮ ኤሌትሪክ አገናኝቶ 0ለ0 ተለያይተዋል፡፡
ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ ዮሐንስ ሴጌቦ ከግራ መስመር ያሻገረውን ግሩም ኳስ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ ተመጣጣኝ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የኳስ እንቅስቃሴ ወደ ግብ በመድረሱ እና ጫና በመፍጠሩ ረገድ ባለሜዳዎቹ የተሻሉ ነበሩ። በተለይም ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ጫና መፍጠር ችለዋል። በ14ተኛው ደቂቃ ደስታ ዮሐንስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ በ35ተኛው ደቂቃ ታፈሰ ሰለሞን ከዮሐንስ ሴጌቦ ከሳጥን ውጪ የተቀበለውን ኳስ መቷት በግቡ አናት ወጥታለች፡፡ በ40ኛው ደቂቃ ሙላለም ረጋሳ ከርቀት ለዳዊት ፍቃዱ ያሻገረለትን ኳስ የቀድሞ ቡድኑ የገጠመው የኢትዮ ኤሌትሪክ ግብ ጠባቂ ዮሐንስ በዛብህ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ተንሸራቶ በእግሩ አውጥቶታል፡፡ በዚሁ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ሐዋሳ ከተማዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በ51ኛው ደቂቃ ባልተለመደ ሁኔታ የመስመር ተከላካይ ቦታ የተሰለፈው ሔኖክ ዲልቢ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ሞክሯት ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡ ከሶስት ደቂቃ በሗላ ደስታ ዮሐንስ ከግራ መስመር ሰብሮ በመግባት ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ተፍቶት ሻይቡ ጅብሪል አጊንቶ መቶት ግብ ጠባቂው በቀላሉ አድኖበታል፡፡በ55ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ አስመስለህ ወድቀሀል በማለት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡
ሐዋሳ ከተማዎች ምንም እንኳን የቁጥር ብልጫ ቢኖርባቸውም ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ ነበሩ፡፡ በ65ኛው ደቂቃ ላይ ዊሊየም ያቡኒ በጉዳት ከሜዳ ሲወጣ በጉዳት ከሜዳ ርቆ የነበረው እስራኤል እሸቱ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ በ70ኛው ደቂቃ ደስታ ዮሐንስ በግራ መስመር በኩል ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ ለመግባት ሲሞክር ግርማ በቀለ ተንሸራቶ አውጥቶታል፡፡ ከሁለት ደቂቃ በሗላ ሔኖክ ዲልቢ ከቀኝ መስመር በኩል የመታት ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትማ ወጥታለች ይቺን ኳስ ለመመለስ የተወረወረው ዮሐንስ በዛብህ የግቡ ቋሚ ጋር ተጋጭቶ ጉዳት አስተናግዶ ጨዋታው ለጥቂት ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር፡፡ በ78ተኛው ደቂቃ ሔኖክ ዲልቢ ተከላካዮችን በማታለል ለመሐመድ ሲላ አቀብሎት የመታት ኳስ ተከላዮች ተደርበውበት የጨግቡን ቋሚ መታ ወታነለች፡፡በ86ኛው ደቂቃ እስራኤል እሸቱ ከሳጥን ውጪ አጊንቶ የመታት ኳስ በግቡ አናት ወታለች፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት ሀይሉ እሸቱ ከዲዲየር ሊብሬ የተቀበለውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ወደ ውጪ የመታት ኳስ ለ እንግዳዎቹ የምታስቆጭ ነበረች፡፡ ጨዋታው በዚህ ወጤት ተጠናቋል፡፡ ሐዋሳ ከተማዎች የፍሬው ሰለሞን ቀይ ካርድ ተገቢ አይደለም በማለት ክስ አስመዝግበዋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
- ማሰታውቂያ -
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ
“ማሸነፍ ካለመቻላችን ውጪ በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ ነበርን በጎዶሎ እየተጫወትንም ብልጫ ወስደን ነበር፡፡ ከጨዋታ ጨዋታ በልጆቼ ላይ ጥሩ መሻሻል አለ፡፡ ችግራችን ግብ የማግባት ነው። የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች ጉዳት አለብን፡፡ ባሉን ልጆች ያለብንን ችግር ለመቅረፍ እንሞክራለን፡፡”
ም/አሰልጣኝ ቅጣው ሙሉ – ኢትዮ-ኤሌክትሪክ
“ጨዋታው ጥሩ ነበር ያገኘናቸውን እድሎች አልተጠቀምንም፡፡በቅጣት እና በጉዳት ከቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ያጣናቸው ልጆች አሉ፡፡ባሉን ልጆች ጠንካራ ስራ ሰርተን እስከ 10ኛ ባለው ደረጃ እንጨርሳለን፡፡”