በተስተካካይ መርሃ ግብር ዛሬ ትግራይ ላይ በተካሄደ ጨዋታ በዋንጫ ፍክክሩ ቀጥተኛ ተፎካካሪ የሆኑት መቐለ ከተማና ቅ/ጊዮርጊስ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ነጥብ ሲጋሩ፡የሊጉ መሪ ጅማ አባጅፋር 2 ነጥቦችን ሳይጫዎት እንዲያተርፍ አስችሎታል፡፡
በግዙፍ ትግራይ ስታዲዮም በርካታ ደጋፊዎች በታደሙበት የመቐለ ከተማና ቅ/ጊዮርጊስ ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ የመቐለ ከተማ ለቀድሞ ተጨዋቾች ዕውቅና ለመስጠት ባዘጋጀው ጨዋታ የቀድሞ የጉና ንግድ ተጨዋቾች ከ ትራንስ ኢትዮጵያ ተጨዋቾች ባደረጉት ጨዋታ ጉና ንግድ አሸንፈው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
የመቐለ ከተማና ቅ/ጊዮርጊስ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር ተዘምሮ ነበር ጨዋታው የተጀመረው፡፡በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች 4-2-3-1 አሰላለፍ ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡በጨዋታው መጀመሪያ ደቂቃ የግብ ማግባት ሙከራ ሲስተናገድበት ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ቀዳሚውን ሙከራ ማድረግ ችለዋል፡፡ተጋጣሚያቸው ቅ/ጊዮርጊስ ምላሽ የሰጠበትን የግብ ሙከራ በ4ኛው ደቂቃ በጨዋታው ቡድኑን በአምበልነት እየመራ በገባው ናትናኤል ዘለቀ አማካኝነት ከግብ ክልል ውጭ ጠርዝ ላይ አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ ወደ ላይ ሲወጣ፡ በ7ኛው ደቂቃ መሃሪ መና ከመስመር ወደ መቀለ የግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ በሃይሉ አሰፋ ፍፁም ቅጣት ምት ውስጥ ተጨርፎ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት ለትንሽ ወደ ውጭ ወጥቷል፡፡
ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ይሄው ጨዋታ በሚሰሩ ጥፋቶችና በሚቆራረጡ የኳስ ሽግግር ሲቀጥል ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ ነበር፡፡በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ኳስን መስርተው ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት በመጠኑም ቢሆን በፈረሰኞቹ አማካኞች ሲከሽፍ የማጥቃት አማራጫቸው ወደ ተሻጋሪና አግድሞሽ ኳሶች ቀይረዋል፡፡ፈረሰኞቹም ቢሆን ከዚህ የተለየ የማጥቃት መንገድን አልተከተሉም፡፡በረጂሙ ከመሃል ሜዳ ወደ ግራና ቀኝ እንዲሁም ቀጥተኛ ኳሶችን በማሻገር ግብ ለማግኘት ሞክረዋል፡፡መቀለዎች በ30ኛው ደቂቃ ከመሃል ሜዳ የተሻገረውን ኳስ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ወደ ግብ ሞክሮት ለትንሽ በግቡ ቋሚ ሲወጣ የጨዋታው አጋማሽ ተጠናቆ ተጨዋቾች ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
እንግዳዎቹ ፈረሰኞቹ የተሻሉ በነበሩበት የሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ፡በተደጋጋሚ የሚያደርጓቸው ቅብብሎሽና ግብ ለማግኘት የነበራቸው ፍላጎት የላቀ የነበረ ቢሆንም ፈረሰኞቹ አሁን የአጥቂ ክፍሉ ከሜዳቸው ሲዎጡ ግብ ማስቆጠር እንደሚቸገር አመላካች ነበር፡፡በዚህኛው አጋማሽ ፈረሰኞቹ የተጨዋቾች ለውጥ ባያደርጉም ኦስናልዶ ታቫሬዝን ወደ ፊት አጥቂነት በማምጣት አሜ መሀመድን የመስመር አማካኝ ሚና በመስጠት ግብ ለማግኘት የሚና ለውጥ በማድረግ ገብተዋል፡፡በ49ኛው ደቂቃ ፈረሰኞቹ በግራ መስመር ይዘውት የገቡትን ኳስ ሳይጠቀሙበት መባከኑ እንጁ ምናልባትም ቀዳሚ ሊሆኑበት የሚችል ኳስ የነበረ ሲሆን በ57ኛው ደቂቃ በሀይሉ አሰፋ ከግራ መስመር ይዞት የገባው ኳስ በግብ ጠባቂው ፊሊኘ ኦቮኖ መክኖበታል፡፡
ባለሜዳዎቹ መቐለዎች በኩል በዚህኛው የጨዋታ አጋማሽ ኢላማውንና ለግብ የተቃረበ ሙከራ በ63ኛው ደቂቃ በአማኑኤል ገ/ሚካኤል አማካኝነት ሲያደርጉ አማኑኤል የፈረሰኞቹን ተከላካዮች አልፎ ይዞት የገባውን ኳስ ሮበርት ኦዶንካራ ሲያድንበት በ75ኛው ደቂቃ አማኑኤል ከመሀል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ በአግባቡ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡
ከግቧ መቆጠር በሇላ ፈረሰኞቹ የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ባደረጉት ጥረት በ82ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም መሀመድ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ከርቀት ያስቆጠራት ድንቅ ጎል ብርቱካናማዎቹን ከሽንፈት ታድጋለች፡፡ጨዋታው ሲቀጥል ያለቀለት የግብ ሙከራ ሳይደረግበት ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ መቀለ ከተማና ቅ/ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርተው ጅማአባጅፋር ሳይጫዎት 2 ነጥብ አትርፏል፡፡በዚህም የጨዋታውን ውጤት ተከትሎ መቀለ ከተማዎች ነጥባቸውን 36 በማድረስ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ 3ኛነት ከፍ ሲሉ ፈረሰኞቹ በ37 ነጥብ በነበሩበት 2ኛ ደረጃ ረግተዋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ~መቐለ ከተማ
“ከውድድር መራቃችን ትንሽ ጎድቶናል። በአካል ብቃት ደረጃ ከሀያ ቀን በላይ ከጨዋታ መራቃችን ይበልጥ ጎድቶናል። ጨዋታው ተመጣጣኝ ነበር። ወደ ጎል በመድረስ እኛ የተሻልን ነበርን።መሀል ሜዳ ላይ ኳስ በመቆጣጠር እነሱ የተሻሉ ነበሩ።”
ም/አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ~ ቅዱስ ጊዮርጊስ
“ጨዋታው ከመጀመሪያው ጠንካራ እንደሚሆን ጠብቀን ነበር ምክኒያቱም መቐለ ከተማ ከመሪዎች ጎራ የተሰለፈ ነው። ጨዋታውን ተቆጣጥረን ለመጫወት ሞክረናል አንዳንድ የአጨራረስ። ሜዳው ላይ የተሻልን ቡድን ነበርን። እግርኳስ ነውና ውጤቱትን በፀጋ ተቀብለናል።”