በ6ተኛው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት የደረሰባቸው መቐለ 70 እንደርታዎች በትግራይ ስታድየም አዳማ ከተማን አስተናግደው ሱሌማን ሰሚድ በራሱ ግብ ላይ እንዲሁም በአማኑኤል ገብረሚካኤል አማካኝነት ባስቆጠርዋቸው ግቦች ሙሉ ሥስት ነጥብ ይዘው ወጥተዋል።አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይለ በፈረሰኞቹ ከተሸነፈው ስብስብ አንተነህ ገብረክርስቶስን በሄኖክ ኢሳያስ፣ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን በአሸናፊ ሀፍቱ ሲቀይሩ አዳማዎች በበኩላቸው ብሩክ ቃልቦሬ፣ደረጄ አለሙ፣መናፍ አወል ወጥተው ጃኮ ፔንዜ፣ቴዎድሮስ በቀለ ና የኃላሸት ፍቃዱ ገብተዋል።
ባሳለፍነው አሁድ ዕለት በድንገተኛ አደጋ ህይወቱ ላለፈው የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊ የህሊና ጸሎት በማድረግ በተጀመረው የመጀመርያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድን ቀጥተኛ አጨዋወትን መርጠው የተመለከትንበት ነበር።መቐለ 70 እንደርታዎች መስመር ላይ ና ከመሀል በረጅሙ በሚላኩ ኳሶች ላይ መሰርት አድርገው ብዙ ማይባሉ እድሎችን መፍጠር ችለዋል።በተለይ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከኦኪኪ ኦፎላቢ ጋር በጥሩ ቅብብል ሄደው መሬት ለመሬት ያሻማውን ኳስ አሸናፊ ሀፍቱ ሲጨርፈው ቅርብ የነበረው ጃኮ ፔንዜ መልሶበታል።በተመሳሳይ አሁንም ኦኪኪ ኦፎላቢ ከመሀል የተላከለትን ኳስ በመጠቀም ፍፁም ቅጣት ሳጥን ውስጥ በግራ በኩል የነበረው አማኑኤል መትቶት ከግቡ አናት ወደ ላይ ሊወጣ ችልዋል።
- ማሰታውቂያ -
በ4-2-3-1 የተጨዋቾች አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው በመጀመርያው አጋማሽ 30 ደቂቃዎች ውስጥ የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም የኃላሸት
ፍቃዱ ካገኘው እድል ውጪ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድርግ ሳይችሉ ቀርተዋል።የመጀመርያው አጋማሽ መጨረሻ ላይ መቐለዎች በአማኑኤል ገብረሚካኤል እና አሸናፊ ሀፍቱ አማካይነት ያገኙዋቸውን ጥሩ እድሎች ሳይጠቀሙ ቀርታዋል።በተለይ ከመሀል ሄኖክ ኢሳያስ በረጅሙ የተላከው ኳስ አማኑኤል ከጃኮ ጋር ቢያገናኘውም ፈጣኑ አጥቂ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ተደጋጋሚ ጉሽሚያዎች እና የዳኛ ፊሽካዎች ፣ተመልካችን ያላዝናና ጥቂት ሙከራዎችን ያስተናገደው ሁለተኛው አጋማሽ መቐለዎች በመጀመርያ 5 ደቂቃዎች ላይ በፈጠሩት ጫና ግብ አስቆጥረው የጨዋታውን መንፈስ ቀይረውታል።ከቀኝ መስመር ስዩም ተስፋዬ ያሻገረው ኳስ ሱሌማን ሰሚድ ለመግጨት ሲሞክር በፈጠረው ስህተት ራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ባለ ሜዳዎቹ መሪ መሆን ችለዋል።ከግቡ መቆጠር በኃላ አዳማዎች የተሻለ መነቃቃት ያሳያሉ ተብሎ ቢጠበቅም ከመስመር እና ከመሀል ከሚመትዋቸውና ከሚያሻግርዋቸው ኢላማቸውን ያልጠበቁ ኳሶች ውጪ ይህ ሚባል እንቅስቃሴ ማሳየት አልቻሉም።ምዐም አናብስቶቹ በበኩላቸው በመልሶ ማጥቃት በኦኪኪ እና አማኑኤል አማካኝነት ዕድሎችን ቢያገኙም የሜዳው መጨረሻ ክፍል ላይ በነበራቸው የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ተጨማሪ ግቦችን ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።
ሆኖም የዕለቱ ዳኛ የጨዋታውን መጠናቀቅ ለማሳወቅ ፊሽካቸውን ባዘጋጁበት ቅፅበት አማኑኤል ገብረሚካኤል ከያሬድ ከበደ የተላከለትን ኳስ በመጠቀም የጃኮ ፔንዜን መውጣት ተመልክቶ በጥሩ አጨራረስ የመቐለን ግብ ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።ጨዋታውም በመቐለ አሸናፊነት ፍፃሜውን ሊያገኝ ችሏል።
ውጤቱን ተከትሎ መቐለ 70 እንደርታዎች ነጥባቸውን 13 በማድረስ ሁለተኛ ደረጃቸውን ሲይዙ አዳማዎች የዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈታቸውን ተጎንጭተዋል።