በ20ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪሚዬር ሊግ በአዲስአበባ ስታዲዬም አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው መከላከያ በፍፁም ገ/ማርያም የጭማሪ ደቂቃ ግብ 1-0 አሸንፏል፡፡
ልክ 9:05 ሲል በተጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ባለሜዳዎቹ መከላከያዎች በአዳማ ከተማ ሽንፈት ካስተናገዱበት የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች የ3ተጨዋቾችን ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ ሲገቡ አብነት ተክቶ ምንተስኖት ሲገባ ፍፁም በመጀመሪያ ጨዋታው በማራኪ ምትክ እንዲሁም በሀይሉን አማኑኤል ተክቶት ወደ ሜዳ ሲገቡ ፡እንግዳዎች ኢትዬጵያ ቡናን በሜዳቸው ከረታው የመጀመሪያ 11ስብስብ በረከትን አስቀምጠው ዘካሪያስን በማስገባት ጨዋታውን ጀምረዋል
ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ በተስተናገደበት የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች ወደ ፊት ተጠግተው ግብ ለማስቆጠር ከመጫዎት ይልቅ የመጀመሪያ ምርጫቸውን ግብ ላለማስተናገድ ጥንቃቄ በመረጡበት በዚሁ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሁለቱም ክለቦች በመስመር በኩል የሃይል ሚዛናቸውን አጋድለው የተጫዎቱ ሲሆን ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ በማድረግ በኩል ባለሜዳዎቹ ቀዳሚዎች ነበሩ፡፡በ6ኛው ደቂቃ ዳዊት ለሳሙኤል ያሻገረለትን ኳስ ሳሙኤል ወደ ግብ ሞክሮት በአዞዎቹ ተከላካዮች ተጨርፎ ወደ ውጭ በመውጣቱ ጦረኞቹ ያገኙትን የመጀመሪያ የማዕዘን ምት እዛው ተቀባብለው በግራ መስመር በኩል ከሳጥኑ ውጭ ዳዊት ወደ ግብ ሞክሮት በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው የእንግዳዎቹ ግብ ጠባቂ ፅዬን ኳሱን በግቡ አግዳሚ አውጥቶበት ሌላ የማዕዘን ምት ቢያገኙም ባለሜዳዎቹ አልተጠቀሙበትም፡፡
እንግዳዎቹ አርባምንጭ ከተማዎች መከላከልን ላይ አመዝነው በመልሶ ማጥቃት ሲጫዎቱ ወደ መከላከያ የግብ ክልል መግባት ቢችሉም በሚወሰድባቸው የቁጥር ብልጫ ኳሱን በቀላሉ በእነ ምንተስኖትና ታፈሰ በተደጋጋሚ ይነጠቁ ነበር፡፡አዞዎቹ የጠራ የግብ ሙከራ ለማድረግ 36 ደቂቃ ለመጠበቅ ተገደው ነበር፡፡በዚሁ ደቂቃ በቀኝ መስመር በኩል የተሻገረውን ኳስ በግራ መስመር አጥቦ የገባው ዘካሪያስ የመከላከያውን ግብ ጠባቂን ይድነቃቸው አቋቋም በማየት በግንባሩ ወደ ግብ ሞክሮት ከግብ ጠባቂው ኳሷ አልፋ ከመረብ ጋር ተገናኘች ሲባል ድንቅ ሲንቀሳቀስ የዋለው የመከላከያው ምንተስኖት ኳሷን እንደምንም ማውጣት ችሏል፡፡
- ማሰታውቂያ -
በባለሜዳዎቹ መከላከያዎች በኩል ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ በማድረግ የተሻሉ ሲሆኑ ኢላማቸውን የጠበቁት ሙከራዎች ቁጥር ግን ጥቂት ነበሩ፡፡በ24ኛው ደቂቃ የአዞዎቹ ግብ ጠባቂ ፅዬንና ምንተስኖት የሰሩትን ስህተት የመከላከያው አጥቂ ሌላኛው ምንተስኖት ሳይጠቀምበት ኳስ ወደ ውጭ ኢላማውን ሳይጠብቅ የወጣበት የሚያስቆጭ ጥሩ አጋጣሚ ሲሆን በእንግዳዎቹ በኩል ሌላኛው የግብ ሙከራ በ43ኛው ደቂቃ አማኑኤል ከሳጥን ውጭ አክሮ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ የወጣበት ተጠቃሺ በመሆን የመጀመሪያ አጋማሽ ያለ ግብ ሳይቆጠር ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
በሁለቱም ክለቦች በኩል ከመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተሻለ ፉክክር በተካሄደበት የሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ግልፅ የግብ ሙከራ በማድረግ አሁንም ጦረኞቹ ቀዳሚ መሆን ሲችሉ፡በ56ኛው ደቂቃ ቴዎድሮስ ከሳጥን ውጭ በግምት ከግቡ 20 ሜትር አካባቢ አክሮ ወደ ግብ የመታት ኳስ በአዞዎቹ ግብ ጠባቂ ስትመክን፡በ62ኛው ደቂቃ የአዞዎቹ የተከላካይ ቦታ ተጫዋች አለልኝ ፡ ዳዊት ላይ በሰራው ጥፋት ከግቡ 26ሜትር ርቀት ያገኙትን ቅጣት ምት ምንይሉ ወጀ ግብ ሞክሮት በግቡ አግዳሚ ወደ ላይ ሳወጣ ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም፡፡አዞዎቹ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ እንቅስቃሴ ወደ ግብ መድረስ በቻሉበት የሁለተኛው አጋማሽ በብርሃኑ እና በእንዳለ አማካኝነት የሚያደርጓቸው የማጥቃት እንቅስቃሴዎች አስፈሪ ቢሆኑም ቡድኑ በተቃራኒ የግብ ክልል ሲገባ ምን ማድረግ እንዳለበት የቤት ስራውን ጨርሶ የመጣ አልነበረም፡፡ኳሶች በተደጋጋሚ ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ከመባከናቸው ባሻገር በቀላሉ በተጋጣማያቸው ተከላካዮች ተነጥቀው በራሳቸው ላይ አደጋ ይፈጥሩ ነበር፡፡
ባለሜዳዎቹ በጨዋታው ማጠናቀቂያ የባከነ ጨማሪ ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ አዲሱ ፈራሚያቸው ፍፁም ገ/ማርያም ለክለቡ በተጫዎተበት በመጀመሪያ ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ በማስቆጠር የጨዋታውን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝተዋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
☞የመከላከያ አሰልጣኝ-ስዩም ከበደ
የዛሬው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያችን ጥሩ አልነበረም፡፡ነገር ግን ጥሩ ሳንሆንም ወሳኝ ሶስት ነጥብ ማስመዝገባችን መልካም፡፡ማሸነፋችን ለቀጣዩ ጨዋታ ትልቅ የስነ ልቦና ጥንካሬ ይሆነናል፡፡
☞የአርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ-እዬብ ማለ
በጨዋታው ጥሩ ተጫውተናል፡፡በዳኝነት ስህተት 1ነጥብ አጥተናል፡፡የዛሬው ዳኝነት ስህተት ነበረው ፡፡መደበኛውና ጭማሪው ደቂቃ ተጠናቆ ነው ግብ የተቆጠረብን ፡ብዙ እናገር ነበር የሚጣብኝን ቅጣት ሳስብ ቤተሰቦቸ አሉ፡፡እናም ከዚህ ሁሉ ዝምታ ይሻለኛል በማለት አስገራሚ አሰተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡