በ5ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተጠበቀው እና ሀዋሳ ላይ የተካሄደው የወንድማማቾች ደርቢ በሲዳማ ቡና 3-1 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
ብዙም ማራኪ እንቅስቃሴ ባልታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ የመጀመሪያው ሙከራ በሲዳማ ቡና በኩል ሲደረግ ሀብታሙ ገዛኸኝ የሞከራት ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥታለች። ጨዋታው ቀጥሎ ሲዳማ ቡና መሪ መሆን የቻለበትን ግብ የመጀመሪያ የመሰለፍ ዕድል የተሰጠው የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ አማኑኤል እንዳለ ወደግብ የላካት ኳስ የግብ ጠባቂውን መዘናጋት ተከትሎ ግብ ልትሆን ችላለች። ከዚህ ግብ መቆጠር በኋላ ብዙም የረባ እንቅስቃሴ ሳይታይ የመጀመሪያው አጋማሽ በሲዳማ ቡና 1-0 መሪነት ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ፈጠን ያለ እንቅሰቃሴ ታይቶበት የጀመረ ሲሆን ይሄን ያሳየች ኳስ 55ኛው ደቂቃ ላይ በሲዳማ ቡናዎች በኩል በመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ኳስ አዲስ ግደይ መሀል ለመሀል ሲያሻግራት ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ ይዞ በመግባት ወደ ግብነት ቀይሯት የሲዳማን መሪነት ወደ 2-0 ማሳደግ ችሏል። ከዚህ ግብ በኋላ ጫና ፈጥረው ለመጫወት የሞከሩት ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ ጥረት ያደረጉ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ 65ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው ሰንደይ ሙቱኩ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት የሀዋሳ ከተማው አጥቂ ብሩክ በየነ ወደ ግብነት ቀይሮት ውጤቱን ማጥበብ ችሎ ነበር።
ሆኖም ግን ሀዋሳ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት በሚሞክሩበት ሰዓት በተከላካዮች መዘናጋት የተገኘውን ኳስ የሲዳማ ቡናው ይገዙ ቦጋለ ወደ ግብነት ቀይሮት ጨዋታው በሲዳማ ቡና 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱንም ተከትሎ ሲዳማ ቡና ከመሪው ወልዋሎ አ.ዩ. በ1ነጥብ ዝቅ ብሎ በ9ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ሀዋሳ ከተማ በአንፃሩ በ7ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
- ማሰታውቂያ -
ሊጉን አንድ ጨዋታ የሚቀረው ወልዋሎ አ.ዩ. በ10 ነጥቦች ሲመራ ሲዳማ ቡና በ9 እንዲሁም ባህርዳር ከተማ በ8ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃ ይዘዋል። የኮከብ ጎል አግቢነቱን ደግሞ የፋሲል ከተማው ሙጂብ ቃሲም፣ የኢትዮጵያ ቡናው እንዳለ ደባልቄ፣ የባህርዳር ከተማዎቹ ማማዱ ሲዲቤ እና ፍፁም ዓለሙ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማው ብሩክ በየነ በእኩል 4 ግቦች ሲመሩ አዲስ ግደይ፣ ዳዋ ሁቴሳ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ይገዙ ቦጋለ እና ሰመረ ሀፍተይ በእኩል 3ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።