ስሁል ሽረ ና አዳማ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል
በ5ተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትግራይ ስታድየም ላይ የተካሄደው የስሁል ሽረ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ።ባለሜዳዎቹ ስሁል ሽረዎች ባሳለፍነው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ከተጋራው ቀዋሚ 11 ሥስት ቅያሬዎችን አድርገዋል።ዮናስ ግርማይ፣መድሀንየ ብርሃነ ና ወንድሜነህ አሸናፊ ወጥተው፤ዲድየር ሌብሪ፣ምንተስኖት አሎ ና በረከት ተሰማ ገብተዋል።አዳማዎች በበኩላቸው ወላይታ ድቻን ከገጠመው ቡድን ጃኮ ፔንዜን በደረጀ አለሙ፣ቡልቻ ሹራን በሱሌማን አህመድ፣ፋአድ ፈረጃን በሱሌማን ሰሚድ፣ዱላ ሙላቱን በብሩክ ቃልቦሬ ባጠቃላይ 4 ቅያሬዎች በማድረግ ጨዋታውን ጀምረዋል።
ተመጣጣኝ እና መስመር ላይ ትኩረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎች በሁለቱም ቡድኖች በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ፤ባለሜዳዎቹ ስሁል ሽረዎች ፊት ላይ ባሰለፍዎቸው ዲድየር ሌብሪ፣ብሩክ ሓዱሽ ና አብዱልለጢፍ መሀመድ አማካኝነት የአዳማ ተከላካይ ክፍልን ሲፈትሹ ታይቷል።የዚህ እንቅስቃሴ ማሳያ ማሳያ ሚሆኑት አብዱልለጢፍ መሀመድ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ ሰብሮ በመግባት መሬት ለመሬት ያሻማው ኳስ ብሩክ ሓዱሽ ለመድረስ ጥረት ቢያደርግም ጃኮ ፔንዜ በፍጥነት ኳሱን ሊይዘው ችሏል።በተጨማሪ ቀኝ መስመር ላይ ብሩክ ሓዱሽ በግሉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከነበረው ዲድየር ሌብሪ የተቀበለውን ኳስ በቀጥታ ወደ ፍጹም ቅጣት ሳጥን አሻግሮት ለግቡ ቅርብ የነበረው አብዱልለጢፍ መሀመድ ቢያገኘውም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።በ3-5-2 የጨዋታ ስልት ወደ ሜዳ የገቡት አዳማዎች ግራ መስመር ላይ ትኩረት አድርገው እድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ነበር።በተለይ ግራ መስመር የተሰለፈው ሱሌማን ሰሚድ ከመሀል ሜዳ ሚጣሉለትን ሰንጣቂ ኳሶችን በመጠቀም ያሻገራቸው ኳሶች በበረከት ተሰማ ና በኣዳሙ ማሳላቺ ጥረት ሊከሽፋ ችለዋል።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ 10 ደቂቃዎች ላይ መስመር ላይ ትኩረት አድርገው ጫና መፍጠር የቻሉት ስሁል ሽረዎች የእንቅስቃሴያቸውን ውጤት በ51ኛው ደቂቃ ማግኘት ችለዋል።ግራ መስመር ላይ አብዱልለጢፍ መሀመድ ከብሩክ ሓዱሽ ጋር አንድ ሁለት ተጫውተው ያገኘውን ኳስ በመጠቀም ወደ ፍፁም ቅጣት ሳጥን በሚገባበት ጊዜ በአዳማ ተከላካዮች በመጠለፋ ምክንያት የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ሀብታሙ ሸዋለም ወደ ግብነት ቀይሮ የሳምሶን አየለ ቡድንን መሪ ማድረግ ችሏል።ከግቡ መቆጠር በኃላ አዳማዎች የአቻነትን ግብ ለማግኘት ጨዋታው ላይ ጥሩ ያልነበረውን ከንአን ማርክነህን በቡልቻ ሹራ፣መናፍ አወልን በሚካኤል ጆርጅ ቀይረው በሁለት አጥቂዎች መጫወትን መርጠዋል።ስሁል ሽረዎች በበኩላቸው ያገቡትን ግብ ለማስጠበቅ ወደ ኃላ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት እድሎችን መፍጠር ቢሞክሩም አጨዋወታቸው የአዳማ ተከላካይ ክፍልን ሚፈትን አልነበረም።ከመሀል ሚላኩ ቀጥተኛ ኳሶችን ወደ ፊት መጣላቸውን የቀጠሉት አዳማዎች ተቀይሮ በገባው ቡልቻ ሹራ እና በረከት ደስታ አማካኝነት ያገኝዋቸውን ግልፅ የግብ እድሎች ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል።ጨዋታው ሊጠናቀቅ ትንሽ ደቂቃዎች ሲቀሩት ብሩክ ቃልቦሬን ቀይሮ የገባው ዱላ ሙላቱ የግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ ስህተትን በመጠቀም ማራኪ ግብ አስቆጥሮ የአሸናፊ በቀለ ቡድንን ጣፋጭ አንድ ነጥብ እንዲያገኝ አድርጎታል።
ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማዎች በሊጉ ያለመሸነፍ ግስጋሴያቸውን ሲያስቀጥሉ ስሁል ሽረዎች ደረጃ ሰንጠርዡ አጋማሽ ላይ ሚያስቀምጣቸው እድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።