አዳማ ከተማ ከነዓን ማርክነህ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ወላይታ ድቻን 1-0 በመርታት ከሊጉ መሪ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 3 ሲያጠብ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ 3ኛነት ከፍ ብሏል፡፡
እንደሁልጊዜው በርካታ ተመልካች በስራ ምክንያት ሳይታደምበት 9:00 ሲል የጀመረው ይሄው ጨዋታ ከጨዋታው አስቀድሞ ባለሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች የስፖርታዊ ጨዋነትን በተመለከተ “ቅድሚያ ለስፖርታዊ ጨዋነት” የሚል የተፃበት ባነር ወደ ሜዳ ይዘው በመግባት አሳሳቢ እየሆነ ለመጣው የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ጨዋታው በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ የተደረገበት ቢሆንም ያን ያህል በግብ ሙከራዎች የታጀበ አልነበረም፡፡ምናልባትም ገና በጨዋታው መጀመሪያ 4ኛው ደቂቃ ባልተጠበቀ ሰዓት ባለሜዳዎቹ በከነዓን ማርክነህ ድንቅ የጭንቅላት ግብ መሪ የሆኑበትን አጋጣሚ በጊዜ ማግኘታቸው ድቻዎች ላይ መደናገጥን ፈጥሯል፡፡
ያም ሁኖ ከግቧ መቆጠር በሇላ የጦና ንቦቹ የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው ሲጫዎቱ በረጅሙ ወደ ፊት በሚጣሉ ኳሶች ግብ ለማግኘት ተንቀሳቅሰዋል፡፡በዚህ በዳግም በቀለና ያሬድ ዳዊት አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ባለሜዳዎቹ አዳማዎች የተሰነዘረባቸውን ጥቃት ከመመከት ባለፈም የአጠፋ ምላሽ ለመስጠት በ30ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ በጭንቅላቱ ገጭቶ ወደ ግብ ሞክሮት ለትንሽ ኳሷ በግቡ ቋሚ ታካ ወጥታለች፡፡
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በመውሰድ ፡በትልቅ ተነሳሽነት ግብ ለማስቆጠር የተጫዎቱት ወላይታ ድቻዎች በ51ኛው ደቂቃ በበዛብህ መለዮ አማካኝነት የአቻነቷን ግብ ቢያስቆጥሩም፡ በዛብህ ኳሷን ከማግኘቱ አስቀድሞ ከጨዋታ ውጭ (Offside )አቋቋም ላይ ስለነበር ግቧ በመስመር ዳኛው ተሽራለች፡፡ባለሜዳዎቹ አዳማዎች ግብ ላለማስተናገድ ወደ ሇላ ተመልሰው በረጅሙ ለዳዋ በሚጣሉ ኳሶች ሌላ ግብ ለማግኘት የተጫዎቱ ቢሆኑም ሌላ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው በዚሁ ተጠናቋል፡፡
አዳማ ከተማ ማሸነፍን ተከትሎ ነጥቡን ወደ 36 በማድረስ በደረጃ ሰንጠሰዡ ወደ 3ኛነት ከፍ ሲል ወላይታ ድቻ በነበረበት 10ኛ ደረጃ በ27ነጥብ ተቀምጧል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
☞አዳማ ከተማ -አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ
በዛሬው ጨዋታ 3 ነጥብ ማስመዝገባችን ጥሩ ነው፡፡የጨዋታ ብልጫ በወሰድንበት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ግብ አስቆጥረን ግብ አለማስተናገዳችን መልካም ነበር፡፡
☞ወላይታ ድቻ -ዘነበ ፍስሀ
በጨዋታው ጥሩ ባልነበርንበት የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ግብ አስተናግደናል፡፡ነገር ግን እኛ ጥሩ በነበርንበት የሁለተኛው አጋማሽ ግብ ማስቆጠር አለመቻላችን ውጤት እንድናጣ አድርጎናል፡፡ቢሆንም ግን በውጤቱ አንከፋም፡፡
ኤሌክትሪክ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ፈረሰኞቹ ዳግም ወደ ለመዱት የሻምፒዮንነት ጉዞ የተሳፈሩበትን ወሳኝ ድል ኢትዬ ኤለክትሪክን 2-1 በማሸነፍ ሲያስመዘግቡ ከመሪው ጅማ አባጅፋር ያለቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ 3 በማጥበብ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ 2ኛነት ከፍ ብለዋል፡፡
በቅዱስ ጊዬርጊስ የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ በይደር ተይዞ ዛሬ በተስተካካይ መርሃ ግብር የተካሄደው ይሄው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ኢሊክትሪኮች ወልዲያ ከተማን 1-0 በማሸነፍ ለጊዜውም ቢሆን ከወራጂ ቀጠና ወተው አፋፉ ላይ የተቀመጡበትን ውጤት ካስመዘገቡበት ቋሚ 11 ስብስብ የ3 ተጨዋቾችን ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን ሲሴ ሀሰን፡ጥላሁን ወልዴ እና ሀይሌ እሸቱን በማሳረፍ ግርማ በቀለ፡በሀይሉ ተሻገርና ዲዲዬ ለብሪን ተክተው ገብተዋል፡፡
በፈረሰኞቹ በኩል ከሜዳቸው ውጭ በአርባምንጭ ከተማ ከደረሰባቸው የ3-0 አስደንጋጭ ሽንፈት ከተጠቀሙባቸው ቋሚ 11 ስብስብ የ4 ተጨዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ አስቻለው ታመነ፡ናትናኤል ዘለቀ፡አዳነ ግርማና ሪቻርድ አፒያን በማስገባት ምንተስኖት አዳነ፡ ሙሏለም መስፍን፡ጋዲሳ መብራቴና አሜ መሀመድን በማሳረፍ ገብተዋል፡፡በዚህም የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ አፒያ በፈረሰኞቹ ማለያ በቋሚ አሰላለፍ የመጀመሪያ ተመራጭ ሁኖ ሲጀምር የመጀመሪያው ሁኖ ተመዝግቧል፡፡
በርካታ ደጋፊዎች ታድመውበት 10:00 ሲል በጀመረው የኢሊክትሪክና የቅዱስ ጊዬርጊስ ጨዋታ ገና ከጨዋታው መጀመሪያ ደቂቃ የግብ ሙከራ የተደረገበት ሲሆን በ2ኛው ደቂቃ ኢሊክትሪኮች በመስመር በኩል ለግብ የተቃረበ ሙከራ በስንታየሁ ሰለሞን አማካኝነት ሲያደርጉ የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ኳሷን ወደ ውጭ አውጥቶ የማዕዘን ምት ቢያገኙም ኢለክትሪኮች አልተጠቀሙበትም፡፡በፈጣን የኳስ ቅብብሎሽ ወደ ግብ ለመድረስ በሚደረግ ፍክክር የቀጠለው ይሄው ጨዋታ በፈረሰኞቹ መለያ በመጀመሪያ አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገባው ስቴቨን አፒያ በ6ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ከመረብ ጋር በማገናኘት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡
ከጎሏ መቆጠር በሇላ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ለማግኘት ወደ ፊት ተጠግተው የግብ ሙከራ ቢያደርጉም ኢላማቸውን የጠበቁ አልነበሩም፡፡በ19ኛው ደቂቃ ፈረሰኞቹ በመስመር በኩል ይዘውት የገቡትን ኳስ በሀይሉ አሰፋ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ ክልል የሰነጠቀውን ኳስ አፒያ ኳሱን ሳይደርስበት የኢለክትሪኩ ግብ ጠባቂ ሱሌማን አቡ ኳሷን በያዘበት እንቅሰስቃሴ ከአፒያ ጋር ተጋጭተው ግብ ጠባቂው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ጨዋታው ለ6ደቂቃዎች ያህል ቆሞ ኤሌክትሪኮች በሱሌማን አቡ ቦታ፡ ዮሃንስ በዛብህን ቀይረው በማስገባት ጨዋታው ቀጥሏል፡፡
ፈረሰኞቹ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በማጥቃት እንቀቅስቃሴ ትተዋቸው የሚሄዷቸውን ክፍተቶች በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ሲጫዎቱ በ37ኛው ደቂቃ በመሀሪ መና እና በበሀይሉ አማካኝነት ያደረጓቸው ለግብ የተቃረቡ ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በኢለክትሪክ በኩል በ38ኛው እና 49ኛው ደቂቃ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ በ51ኛው ደቂቃ ዲዲዬ ለብሪ በጥሩ አጨራረስ ኳስና መረብን አገናኝቶ ቡድኑን ወደ አቻነት መልሷል፡፡በ60ኛው ደቂቃ ካሉሿ አልሀሰን ጣጣውን የጨረሰ ኳስ ለታፈሰ ተስፋዬ አመቻችቶ አቀብሎት አገባው ሲባል ሮበርት ኦዶንካራ የመለሰበት ኢሊክትሪክን ወደ መሪነት የሚመልስ ወርቃማ አጋጣሚ መክኗል፡፡
ፈረሰኞቹ በ70ኛው ደቂቃ ያገኙትን የማዕዘን ምት በአፒያ ተቀይሮ የገባው አማራ ማሌ በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠረው ግብ በድጋሚ መሪ መሆን ችለዋል፡፡ኢሊክትሪኮች በድጋሚ የአቻነቷን ግብ ለማግኘት በጨዋታው ማገባደጃ በቀኝ መስመር በኩል ዲዲዬ ለብሪ ሰብሮ ለመግባት ሲሞክር
አቡበከር ሳኒ ጥፋት በመስራቱ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ጨዋታው በዚሁ ሲጠናቀቅ ኢለክትሪክ በነበረበት በ21 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ሲረጉ፡ ፈረሰኞቹ በ36 ነጥብ ወደ 2ኛነት ከፍ ብለዋለል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
☞ኢትዮ ኤሌክትሪክ – ም/አሰልጣኝ ቦጋለ ዘውዴ
በጥቃቅን ስህተቶች ተሸንፈናል፡፡የአጨራረስ ችግራችን ዋጋ አስከፍሎናል፡፡በቀጣይ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረን እንሰራለን፡፡
☞ቅ/ጊዮርጊስ – ቫስ ፒንቶ
ዛሬ ማሸነፋችን ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ወደ ዋንጫው በምናደርገው ጉዞ የማሸነፍ ስነ ልቦና ጥንካሪያችን ለማጎልበት ውጤቱ ትልቅ ሚና አለው፡፡