በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት 1ተስተካካይ ጨዋታ ዛሬ(ሀሙስ) ተከናውኖ ቅ/ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
11:00 ሲል የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል።
6ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው ከነዓን ማርክነህ ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ተመልሷል። 10ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ ጋዲሳ መብራቴ ከአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ጃኮ ፔንዜ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የሞከረው ኳስ ግብ ጠባቂው በድንቅ ሁኔታ አድኖበታል። 14ኛው ቅ/ጊዮርጊስ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ ያገኙትን ቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ በቀጥታ መትቶት ኳሱ ወደ ውጭ ወጥቷል። በጨዋታው በአንፃራዊ መልኩ አዳማ ከተማዎች ብልጫ መውሰድ የቻሉ ሲሆን 24ኛው ደቂቃ ላይ የቀድሞው የቅ/ጊዮርጊስ አጥቂ ዳዋ ሁቴሳ ከርቀት ጥሩ ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ ኳሱ በቅ/ጊዮርጊስ ተከላካዮች ተደርቦ ወደ ውጭ ወጥቷል።
- ማሰታውቂያ -
ከዚህች ሙከራ 3ደቂቃዎች በኋላ 27ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር ይዘው የገቡትን ኳስ ድንቁ ተጫዋች ከነዓን ማርክነህ በማስቆጠር እንግዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ ነበር። 31ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አዳነ ግርማ ከመሃል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ በጭንቅላቱ የሞከረው ኳስ ወደ ውጭ ወጥቷል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ መነቃቃት ያሳዩት አዳማ ከተማዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ብልጫ መውሰድ የቻሉ ሲሆን 37ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ይዘው የገቡትን ድንቅ ኳስ በረከት ደስታ አግኝቶ ሞክሮት ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አልፎ አልፎ ወደ አዳማ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደረጉ የተስተዋሉት ፈረሰኞቹ ጥረታቸው ግን የተደራጀ ባለመሆኑ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። 42ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ ከቀኝ መስመር እያጠበበ ገብቶ የመታው ኳስ ለጥቂት በግቡ ጎን ወደ ውጭ ወጥቷል። ከ3ደቂቃዎች በኋላ 45ኛው ደቂቃ ላይ ሌላው የቅ/ጊዮርጊስ ተጫዋች አቡበከር ሳኒ ከመዓዘን ምት የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ቢሞክረውም ኳሱ ወደ ውጭ ወጥቷል። በዚህም ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ተቀዛቅዞ እና ተዳክሞ የታየው ሁለተኛው አጋማሽ ሙከራ ለማስተናገድ ረዘም ያለ ሰዓት ወስዶበታል። 65ኛው ደቂቃ ላይ ቅ/ጊዮርጊሶች ከሜዳው በስተቀኝ በኩል የመዓዘን መምቻ አካባቢ ያገኙትን የቅጣት ምት ኳስ አበባው ቡጣቆ ወደ ጎል ቢያሻማውም የአዳማ ከነማ ግብ ጠባቂ ጃኮ ፔንዜ በቀላሉ ይዞታል።
ከዚህም በኋላ ይሄ ነው የማይባል ሙከራ ሳይደረግበት እንዲሁም በሁለቱም ቡድኖች በኩል የሚቆራረጡ ኳሶች የተስተዋለበት አጋማሽ ሆኖ ነው ያመሸው።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ 4ደቂቃዎች ሲቀሩት 86ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ የመስመር አጥቂ አቡበከር ሳኒ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ አግኝቶ ወደ ጎልነት ቀይሮት ቡድኑ አቻ እንዲሆን አስችሎታል።
የጨዋታው መጠናቀቅ በሚጠበቅበት ሰዓት በደጋፊዎች መካከል በተነሳ ፀብ እና ግጭት ጨዋታው ለተወሰነ ጊዜ የተቋረጠ ሲሆን በረብሻው በርከት ያሉ ደጋፊዎች ጉዳት ደርሶባቸው እርዳታ ሲደረግላቸው ተስተውሏል። የተነሳው ፀብ መረጋጋቱን ተከትሎ ጨዋታው ከቆመበት የቀጠለ ሲሆን በዚሁ ውጤት 1-1 ተጠናቋል።