በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት 8 ጨዋታዎች ዛሬ በተደረገ 1 ጨዋታ ጅማሬአቸውን አድርገዋል።
አ/አ ላይ በተደረገው በዚህ ጨዋታ 11፡00 ሲል ቅ/ጊዮርጊስ ጅማ አባጅፋር አስተናግዶ 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ይህ ድሉም ቅ/ጊዮርጊስ በሜዳው 3ግቦችን በማስቆጠር ያሸነፈበት 3ኛ ጨዋታው ሆኖ ተመዝግቧል። ለቅ/ጊዮርጊስ ግቦቹን ተከላካዩ አበባው ቡጣቆ ሁለቱን ሲያስቆጥር አዳነ ግርማ ቀሪዋን 1ግብ ማስቆጠር ችሏል።
በጨዋታው ይሄ ነው የሚባል የጨዋታ ብልጫ ያላሳዩት ቅ/ጊዮርጊሶች ከቆሙ ኳሶች ያገኟቸውን አጋጣሚዎች በአግባቡ በመጠቀማቸው ጨዋታውን አሸንፈው መውጣት ችለዋል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ ለማስተናገድ 3ደቂቃዎች ብቻ ፈጅተውበታል። አበባው ቡጣቆ ከግቡ 35 ሜትር ርቀት ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ ወደግብ በመምታት በግሩም ሁኔታ ከመረብ ጋር አገናኝቶት ቅ/ጊዮርጊስን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። በጊዜ ግብ ማስተናገዳቸውን ተከትሎ መደናገጥ የተስተዋለባቸው እንግዳዎቹ ጅማ አባጅፋሮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከብዷቸው ተስተውለዋል። በመሀል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ያሳዩት ቅ/ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ ወደግብ ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም ይሄ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ ጅማ አባጅፋሮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በመጨረሻዎቹ 15ደቂቃዎች ላይ ጥሩ ሆነው ሲቀርቡ በጨዋታው ጥሩ ሆኖ ያመሸው ተከላካዩ ሄኖክ አዱኛ በተደጋጋሚ የቅ/ጊዮርጊስን ተከላካዮች በማስጨነቅ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት የሚያሻግራቸው ኳሶች አደገኛ ቢሆኑም አጥቂዎቹ ሊጠቀሙባቸው ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ በቅ/ጊዮርጊስ 1-0 መሪነት ተጠናቋል።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ለየት ባለ የድጋፍ ድባብ የተጀመረው ሁለተኛው ግማሽ ብዙ ግጭቶች እና ቶሎ ቶሎ የሚቋረጡ የኳስ ቅብብሎች የተስተዋለበት ነበር። 66ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አጥቂ ኪዬታ ሲዴ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ በድጋሚ አስቆጥሮ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ከዚህም ግብ መቆጠር በኋላ ውጤቱን ለማጥበብ ጥረት ያደረጉት ጅማ አባጅፋሮች ያደረጉት ጥረት በብዙ ደጋፊዎች አድናቆትን አትርፏል። ሁለተኛው ግብ ከተቆጠረ 12ደቂቃዎች በኋላ 78ኛው ደቂቃ ላይ በኀይሉ አሰፋ(ቱሳ) ከማዕዘን ምት ያሻገረለትን ኳስ አዳነ ግርማ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ቡድኑ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠበትን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ውጤቱን ተከትሎ 2ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ቅ/ጊዮርጊስ ከመሪው ደደቢት 3ነጥቦችን ዝቅ ብሎ በ16 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ተሸናፊው ጅማ አባጅፋር ከተጋጣሚው ቅ/ጊዮርጊስ በ2 ነጥቦች አንሶ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
በጨዋታው 2ግቦችን ያስቆጠረው አበባው ቡጣቆ ከድረ-ገፃችን Hatricksport.com ጋር ባደረገው አጠር ያለ ቆይታ ስለጨዋታው አስተያየቱን ሰጥቷል። “ጨዋታውን በማሸነፋችን ደስተኛ ነኝ። በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ እስካሁን ከገጠምናቸው ቡድኖች ጅማ አባጅፋር ከባዱ ነበር። ሌሎች ቡድኖች ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ሲጫወቱ መከላከልን ምርጫቸው ያደርጋሉ። ጅማ አባጅፋር ግን ለማጥቃት ያሳዩት ተነሳሽነት ጨዋታውን ከባድ አድርጎብናል።” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
የቅ/ጊዮርጊሱ ም/አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ
“ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ ወጥተን ነበር፤ እነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ነጥብ መጣላችን ክለባችንን ወደተሻለ ደረጃ እንዳይጓዝ አድርጎት ነበር። ይህ በመሆኑም የዛሬውን ጨዋታ ድል ማድረግ እንዳለብን አስበን ነበር ወደሜዳ የገባነው፤ ያሰብነውንም አሳክተን ድል ማድረግ ችለናል። ጨዋታውን በመጀመሪያው አጋማሽ ጨርሰን መውጣት እንችል ነበር፤ በአጠቃላይ ግን የዛሬው ድል ይገባናል።” በማለት አስተያየቱን አጠቃሏል።
የጅማ አባጅፋሩ አሰልጣኝ ገ/መድህን ሀይሌ
“እንዳያችሁት ጨዋታው በቅ/ጊዮርጊስ የበላይነት ተወስዶብን ነው የተሸነፍነው። እኛ ቡድን ላይ ታክቲክ ላይ ችግር ነበረብን። ቅ/ጊዮርጊስ ይህንን ጨዋታ ማሸነፉ አይበዛበትም። የሚገባው ውጤት ነበር።” በማለት አስተያየቱን አጠቃሏል።