የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን በዚህ ዙርም በውድድር አመቱ ወጣ ገባ የሚል አቋም እያሳየ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም በሊጉ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነውን ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ ያለግብ አቻ ተለያይቷል። በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከሜዳው ውጪ ማሸነፍ የተሳነው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም ድል ማድረግ ተስኖታል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ6ኛው ሳምንት የአምናውን ሻምፒዮን መቐለ 70 እ. አስተናግዶ 2-1 ማሸነፉ ሲታወስ እና የቡድኑን ወሳኝ አጥቂ ሰልሀዲን ሰዒድ ከጉዳት ማግኘቱ እና ከአቤል ያለውን እና ጌታነህ ከበደ ጋር የፈጠረው ጥምረት ሲታይ የሀዋሳውን ጨዋታ በቀላሉ ያሸንፋል የሚል ግምት ነበር። ሆኖም ግን በተቃራኒው ሆኖ ከሜዳው ውጪ ግብ ሳያስቆጥር ተመልሷል። ከቦታው ባገኘነው መረጃ መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ተደጋጋሚ እድሎችን መፍጠር ቢችልም ሳይጠቀምበት ቀርቶ በአቻ ውጤት ተመልሷል።
ውጤቱንም ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ መሪዎቹ ጎራ በደምብ መጠጋት የሚችልበትን አጋጣሚ ሲያመክን ሀዋሳ ከተማም በተመሳሳይ እድሉን አምክኗል። በ7ሳምንታት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሪው ወልዋሎ አ.ዩ. በ4ነጥቦች ርቆ በ10 ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሀዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በ1ነጥብ ዝቅ ብሎ በ9ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ሊጉን ወልዋሎ አ.ዩ. በ14 ነጥቦች ሲመራ መቐለ 70 እ. እና ፋሲል ከተማ በቅደም ተከተል በ13 እና በ12 ነጥቦች 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የኮከብ ግብ አግቢነቱን ደግሞ የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በ7 ግቦች ቀዳሚ ሲሆን የባህርዳር ከነማው ፍፁም ዓለሙ በ6 እንዲሁም የመቐለ 70 እ. አማኑኤል ገ/ሚካኤል በ5ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።