ዛሬ ከተደረጉት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በብቸኝነት አ/አ ስታዲየም ላይ የተካሄደው የቅ/ጊዮርጊስ እና የፋሲል ከተማ ጨዋታ በፈረሰኞቹ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጨዋታው ጅማሬ እንግዳዎቹ ፋሲል ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደፊት ተጭኖ በመጫወቱ በኩል የተሳካላቸው ነበሩ። ሆኖም ይህንን ብልጫቸውን ወደግብነት በመቀየሩ ረገድ ደካማ ነበሩ። ከ25ደቂቃ በኋላ መነቃቃት ያሳዩት ቅ/ጊዮርጊሶች በታደለ መንገሻ፣ በአብዱልከሪም ኒኪማ እና በበኃይሉ አሰፋ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ይህንንም ተከትሎ አብዱልከሪም ኒኪማ ከርቀት ግሩም ኳስ በቀጥታ መትቶ ኳሱ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የወጣበት፣ በሃይሉ አሰፋ ከግራ መስመር ወደ ጎል አጥብቦ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ጥረት ወደ ውጭ የወጣበት ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ቅ/ጊዮርጊሶች ሁለት አስገዳጅ ቅያሪዎችን ያደረጉ ሲሆን፣ አጥቂው አማራ ማሌ እና አማካዩ ታደለ መንገሻ በመጎዳታቸው አሜ መሀመድ እና አዳነ ግርማ ተክተዋቸው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ይህንንም ተከትሎ ፈረሰኞቹ የፋሲል ከተማን የተከላካይ መስመር ክፍል ሲያስጨንቁ አምሽተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩ 45+3ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አብዱልከሪም ኒኪማ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲመልሰው በአካባቢው የመበረው እና ኳሷን ያገኘው አሜ መሃመድ ወደ ጎልነት ቀይሯት የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ሆኗል።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በደማቅ ድጋፍ እና ዝማሬ የተጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ ፈረሰኞቹ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ያደረጉ ሲሆን በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች ወደ ጎል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ደካማ ነበር። በጨዋታው 79ኛ ደቂቃ ላይ የጨዋታውን ይዘት ሊቀይር የሚችል ክስተት ተፈጠረ። ፋሲል ከነማዎች በመልሶ ማጥቃት ይዘውት የገቡትን ኳስ ደጉ ደበበ ለመመለስ በሚሞክርበት ወቅት ጥፋት በመስራቱ የጨዋታው የመሃል ዳኛ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ከዚህ ጥፋት ሁለት ደቂቃዎች በኋላ 81ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት የፋሲል ከተማው አምሳሉ ጥላሁን በቀጥታ ወደግብ በመምታት ግሩም ግብ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር። ከዚህች ግብ መቆጠር 5ደቂቃዎች በኋላ 86ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አቡበከር ሳኒ ላይ የተፈፀመውን ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አዳነ ግርማ ወደግብነት ቀይሮት በድጋሚ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት ላይ 90+3ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አሜ መሃመድ ተከላካዮችን አልፎ ይዞ ገብቶ ለራሱ ሁለተኛውን ለቡድኑ ደግሞ ሶስተኛውን ግብ በማስቆጠር ቅ/ጊዮርጊስን ከ8 ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ 3ነጥቦች እንዲያገኝ አስችሎታል።