በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ተስተካካይ 1ጨዋታ ዛሬ ተደርጎ የሊጉን መሪ ደደቢትን ከአምናው የሊጉ አሸናፊ ቅ/ጊዮርጊስ ያገናኘው ይህ ጨዋታ ያለግብ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቀቀ።
እንደ ወትሮው ሁሉ እጅግ ባማረ እና በደመቀ የደጋፊዎች ዝማሬ እና ድጋፍ ታጅቦ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በጨዋታው ጅማሬ መጣል የጀመረው ዝናብ በጨዋታው ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ በግልፅ ተስተውሏል።
በጨዋታው ቅ/ጊዮርጊስ በ4-2-3-1 የጨዋታ ዘይቤ ወደሜዳ የገባ ሲሆን ከአራቱ ተከላካዮች ፊት ሙሉዓለም ጥላሁን እና ምንተስኖት አዳነ ሲጫወቱ ከእነሱ ፊት ኢብራሂም ፎፋና በግራ ክንፍ ጋዲሳ መብራቴ በቀኝ እንዲሁም አብዱልከሪም ኒኪማ ደግሞ ብቸኛ አጥቂ ከነበረው አቡበከር ሳኒ ጀርባ በመሆን ነበር ጨዋታውን የጀመሩት። ደደቢት በአንፃሩ በ4-3-3 የጨዋታ ዘይቤ የገባ ሲሆን አስራት መገርሳ፣ የአብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለ የመሀል 3ቱን ቦታ ሲይዙት ከነሱ ፊት ሽመክት ጉግሳ አቤል ያለው እና ኤፍሬም አሻሞ ይጫወቱ ነበር።
ይህ ጨዋታ የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ ለማስተናገድ የወሰደበት 4ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 4ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ ኤፍሬም አሻሞ ከግብ ጠባቂው ጋር 1-1 ተገናኝቶ የሞከረውን ኳስ የቅ/ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ በድንቅ ሁኔታ አውጥቶታል። 15ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አብዱልከሪም ኒኪማ ከ አቡበከር ሳኒ የተቀበለውን ኳስ ከግቡ 35ሜ ርቀት ላይ ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት ኳሱ ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥቶበታል። በተደጋጋሚ ወደ ደደቢት የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረጉት ቅ/ጊዮርጊሶች 18ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን አጋጣሚ ኢብራሂም ፎፋና ከሳጥን ውጪ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ቢመታውም የደደቢት ግብ ጠባቂ ክሌመንት አዞንቶ በቀላሉ ይዞታል። ከዚህ ሙከራ 3ደቂቃዎች በኋላ 21ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ የሰራውን ስህተት ተከትሎ የደደቢቱ ሽመክት ጉግሳ ቀጥታ ወደ ግቡ ሞክሮት ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞታል።
በጨዋታው የመሀል ሜዳ ክፍል ላይ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ቅ/ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ ወደ ደደቢት የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ለዚህ ብልጫ እንደ ዋና ምክንያት ሊቆጠር የሚችለው የአማካዮቹ ሙሉዓለም ጥላሁን እና ምንተስኖት አዳነ በጨዋታው ምርጥ አቋም ላይ ከመገኘታቸው በተጨማሪ የአብዱልከሪም ኒኪማ ወደ ኋላ እየተመለሰ እንዲሁም ከተከላካዮቹ ደግሞ ሳላዲን ሰዒድ ወደፊት እየመጣ ማገዛቸው የደደቢት የመሀል ሜዳ ክፍል ተጫዋቾች ላይ ብልጫ መውሰድ አስችሏቸዋል። ይህን የጨዋታ ብልጫ ተከትሎ የደደቢት ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ጥፋት እንዲሰሩ አስገድዷቸዋል።
31ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አበባው ቡጣቆ ያሻገረለትን ኳስ ምንተስኖት በግሩም ሁኔታ ሞክሮት የደደቢቱ ግብ ጠባቂ በቀላሉ ይዞታል። 38ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አብዱልከሪም ኒኪማ ከግራ ክንፍ በኩል ያሻገረለትን ኳስ አቡበከር ሳኒ በግንባሩ ገጭቶት ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቷል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ይሄ ነው የሚባል ሙከራ ሳይደረግበት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በወረደ ጨዋታ እና ሽኩቻ በበዛበት ጨዋታ የተካሄደ ነበር። ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ 48ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊስን ተከላካዮች ስህተት ተከትሎ ያገኘውን ኳስ የደደቢቱ አጥቂ አቤል ያለው ሞክሮት ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥቶበታል።
53ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አብዱልከሪም መሀመድ ከቀኝ ክንፍ በኩል ያሻገረለትን ኳስ ምንተስኖት አዳነ በግንባሩ ገጭቶት ግብ ጠባቂው በግሩም ሁኔታ አውጥቶታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የደደቢቱ አቤል ያለው ከግራ ክንፍ በኩል ከሽመክት ጉግሳ የተሻገረለትን ኳስ ሞክሮት ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቷል። ከዚህ በኋላም ዝናቡ በድጋሚ በመጀመሩ እና መጫወቻ ሜዳው ውሀ በመያዙ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ኳሱን እንደልብ ማንሸራሸር አልቻሉም። ይህንንም ተከትሎ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ረጃጅም ኳሶችን ሲጠቀሙ ተስተውለዋል። 62ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አቡበከር ሳኒ በግል ጥረቱ ይዞ ገብቶ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ኳስ በቅ/ጊዮርጊስ በኩል የሚያስቆጭ ነበር። ከ3 ደቂቃዎች በኋላ አቡበከር ሳኒ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ክሌመንት አዞንቶ በድንቅ ሁኔታ አውጥቶታል። 67ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን ድባብ የቀየረ አጋጣሚ ተከስቶ ነበር። የቅ/ጊዮርጊሱ በሃይሉ አሰፋ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው ጠልፎት ሲወድቅ የጨዋታው የመሃል ዳኛ የነበሩት ኢንተርናሽናል አርቢትር ለሚ ንጉሴ የፍፁም ቅጣት ምት ከሰጡ በኃላ በድጋሚ የመስመር ዳኛውን ሃሳብ በመቀበል ጨዋታው በመዓዘን ምት እንዲቀጥል አድርገዋል። ይህንንም ውሳኔያቸውን ተከትሎ በተጫዋቾችና በደጋፊው ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸዋል። ከዚህ አጋጣሚ በኋላ ጨዋታውን መቆጣጠር ተስኗቸው ተስተውለዋል። 75ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ አማካይ አስራት መገርሳ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ በቀይ ከሜዳ ተሰናብቷል።
ከዚህ በኋላ ቅ/ጊዮርጊስ ግብ አስቆጥሮ ለማሸነፍ ረጃጅም ኳስን ሲጠቀም ደደቢት በአንፃሩ ሰአት ለማባከን በተደጋጋሚ ሜዳ ላይ ሲወድቁ ተስተውለዋል። በዚህም ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን ሊያሰሙ ችለዋል። በዚሁም ጨዋታው ያለግብ 0-0 ሊጠናቀቅ ችሏል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ም/አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቅ/ጊዮርጊስ
“ወደ ሜዳ የመጣነው ጨዋታውን ለማሸነፍ ነው፤ 1ነጥብ ለማግኘት ወደ ሜዳ አልመጣንም፤ ሜዳ ላይ ልጆቻችን የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥረናል፤ የእነሱ አጥቂዎች ፍጥነታቸውን እንዳይጠቀሙ እና እነሱ ሜዳ ላይ ተጭነን ግብ ለማግባት ሞክረናል፤ አልተሳካልንም፤ በውጤቱ ደስተኞች አይደለንም።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ስለ ዕለቱ ዳኛ የተጠየቁት አሰልጣኙ ሲመልሱ ” ብዙ ጊዜ ስለ ዳኛ መናገር አይመቸኝም፤ ግን ስለ እንቅስቃሴው ከጠየቃችሁኝ ግልፅ ፍፁም ቅጣት ምት ነበር፤ ዳኛው ነፍቷል፤ ከነፋ በኋላ ለምን ወደ ማዕዘን ምት እንዳደረገ መገመት አልችልም። ግን በኔ እሳቤ ግልፅ ፍፁም ቅጣት ምትነው። ዳኛውም ደግሞ ትክክል መሆኑን ነፍቶ አሳይቶናል፤ ግን በኋላ ውሳኔው ለምን እንደተቀየረ አላውቅም።” በማለት አስተያየታቸውን አጠናቀዋል።
ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ ደደቢት
“ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ በዝናቡ ምክንያት እንዳሰብነው መጫወት አልቻልንም፤ አንድ ተጫዋች በቀይ ባይወጣብን ኖሮ ለማሸነፍ ፈልገን ነበር የገባነው። ከዚህ ቀደም እንደነበርነው ወደ ግብ መድረስ አልቻልንም። የጌታነህ ከበደ አለመኖር በቡድናችን ውስጥ ክፍተት ፈጥሯል።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ስለ ቀይ ካርዱ የተጠየቁት ም/አሰልጣኙ ሲመልሱ”ቀይ ካርዱን በፀጋ እንቀበላለን።” ብለዋል።