የ22ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪሚዬር ሊግ አዲስ አበባ ላይ ኢትዮ ኢለክትሪክ በሜዳው ወልዲያ ከተማን ባስተናገደበት ጨዋታ ታፈሰ ተስፋዬ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ወልዲያ ከተማን 1-0 በማሸነፍ ለጊዜውም ቢሆን ከወራጂ ቀጠናው ወጥተዋል፡፡
15 ደቂቃ ዘግይቶ 10:15 ሲል በጀመረው የኢትዮ ኢለክትሪክና ወልዲያ ከተማ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ባለፈው ሳምንት ከሜዳቸው ውጭ ጅማ ላይ በጅማ አባጅፋር ሽንፈትን ካስተናገዱበት የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ግርማ በቀለ ፡ጫላ ድሪባ ፡ዲዲዬ ለብሪ እና በሀይሉ ተሻገርን በማሳረፍ ፡ሲሴ ሀሰን ፡ስንታየሁ ዋለጬ ፡ስንታየሁ
ሰለሞን እና ጥላሁን ወልዴ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡በእንግዳዎቹ ወልዲያ ከተማዎች በኩል ሰበታ ላይ በሲዳማ ቡና ሲሸነፍ በመጀመሪያ አሰላለፍ ከተጠቀሙባቸው ተጨዋቾች አማረ በቀለ፡ብርሃኔ አንለይ እና ዳንኤል ደምሴን በማሳረፍ በምትካቸው አዳሙ መሀመድ ፡ያሬድ ሀሰንና ምንያህል ተሾመን አስገብተዋል፡፡
በሊጉ ግርጌ የተቀመጡት ባለሜዳዎቹ በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ ከሰፈሩት ወልዲያ ከተማዎች ጋር ያደረጉት ጨዋታ ሲጀምር ተመጣጣኝና ፈጣን የኳስ ሽግግር ፍሰት በነበረውና ሁለቱም ክለቦች ጨዋታውን በአሸናፊነት ውጤት ይዞ ለመውጣት ከነበራቸው ፍላጎት አንፃር ጨዋታው መሃል ላይ ያመዘነና ማራኪ ቢሆንም በበርካታ ኢላማቸውን ባልጠበቁ የግብ ሙከራዎች የታጀበ ነበር፡፡በጨዋታው እንቅስቃሴ ወልዲያ ከተማዎች በ11ኛው ደቂቃ መስፍን ኪዳኔ በግራ መስመር ሰብሮ በመግባት የኢለክትሪክ ሳጥን ውስጥ በግራ እግሩ በግቡ ትይዩ ለነበረው አንዷለም ንጉሴ (አቤጋ )አመቻቶ አቀብሎት ሳይጠቀምበት ሲቀር በቀኝ መስመር አጥቦ የገባው በላይ አባይነህ ኳሷን ለማግኘት ተንሸራቶ ቢሞክርም ኳሷ የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችበት እንቅስቃሴ አልተጠቀሙበትም እንጂ ወልዲያዎች ቀዳሚ መሆን የሚችሉበትን አጋጣሚ መክኗል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ባለሜዳዎቹ ኢለክትሪኮች የሚሰነዘርባቸውን ኢላማውን ያልጠበቀ የግብ ሙከራም ቢሆን አጠፋውን ለመመለስ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ የቻሉበት አጋጣሚ በ28ኛው ደቂቃ ሲሆን በዚህ አጋጣሚ አምበሉ አዲስ ነጋሽ ከመሃል ሜዳ በረጅሙ በግራ መስመር በኩል ለነበረው ለስንታየሁ ሰለሞን አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ስንታየሁ ከግራ መስመር ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ አንጋፋው አጥቂ ታፈሰ ተስፈዬ በድንቅ አጨራረስ ኳስን ከመረብ ጋር በማገናኘት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ከግቧ መቆጠር በሇላ የአቻነት ግብ ለማግኘት ወደ ፊት ተጠግተው ለመጫዎት የሞከሩት ወልዲያዎች አንድም ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ተጋጣሚያቸው ኢትዬ ኢለክትሪክ ሁለተኛ ግብ ለማግኘት ባደረጉት እንቅስቃሴ 45ኛውና በ45+1 ደቂቃ ለግብ የቀረቡ አድርገው ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ግብ ለማግኘት ጥረት በማድረግ የተሻሉ የነበሩት ወልዲያዎች በ55ኛው ደቂቃ በግራ መስመር መስፍን ኪዳኔ ያሻገረውን ኳስ በላይ አባይነህ በጭንቅላቱ ገጭቶ ኢላማውን ሳይጠብቅ በግቡ አግዳሚ ሲወጣ በ60ኛው ደቂቃ አንዷለም ንጉሴ ከምንያህል ተሾመ የተቀበለውን ኳስ ለኤዶም አመቻችቶ አቀብሎት አገባው ሲባል የመከነው ኳስ የሚያስቆጭ ነበር፡፡ባለሜዳዎቹ ግብ ላለማስተናገድ ወደ ሇላ ተመልሰው በተጫዎቱበት የዚህኛው የጨዋታ አጋማሽ በመስመር በኩል የሚሰነዝሯቸው ጥካቶች አስፈሪ ነበሩ፡፡ለዚህም በ68ኛው ደቂቃ ስንታየሁ ዋለጩ ከሳጥን ውጭ አክሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ ተገጭቶ ሲመለስ በሌላ በኩል በ75ኛው ደቂቃ አዲስ ነጋሽ ሞክሮት የወልዲያው ቤሌንጌ ያወጣበት ይጠቀሳል፡፡
የጨዋታው ደቂቃ ማገባደጃ ላይ የአቻነት ግብ ለማግኘት በሙሉ ሃይላቸው አጥቅተው የተጫወቱት ወልዲያዎች በ80:90እና 92ኛው ደቂቃ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርጉም፡ኳስና መረብን ሳያገናኙ ጨዋታው በኢትዬ ኢለክትሪክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
የጨዋታውን ውጤት ተከትሎ ኢትዮ ኢለክትሪኮች ከነበሩበት 16ኛ ደረጃ ነጥባቸውን 21 በማድረስ ወራጂ ቀጠናውን ለቀው ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ ወልዲያ ከተማ በ20 ነጥብ ወራጂ ቀጠናውን ተቀላቅሎ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
☞ም/አሰልጣኝ ቦጋለ ዘውዴ – ኢትዮ ኤለክትሪክ
የዛሬው ውጤት ካለንበት የደረጃ ሰንጠረዥ አንፃር ለሁለታችንም አስፈላጊ ነበር፡፡በተጨዋቾቻችን ከፍተኛ ጥረትና ፍላጎት ሶስት ነጥብ ማግኘት መቻላችን ለቀጣዩ ጨዋታ ትልቅ የስነ ልቦና ጥንካሬ ይሰጠናል፡፡በተለይም ግብ ሳይቆጠረብን ማሸነፍ መቻላችን የነበሩብንን ድክመቶች እያሻሻልን መሆናችን የሚያሳይ ነው ፡፡በቀጣይም ጥሩ ውጤት አስመዝግበን ከወራጂ ስጋት በጊዜ ለመዳን ጠንክረን እንሰራለን፡፡
☞አሰልጣኝ ኃይማኖት ግርማ – ወልዲያ ከተማ
ተጋጣሚያችን ጥሩ በነበሩበት የመጀመሪያው አጋማሽ ግብ አስቆጠሩብን በሁለተኛው አጋማሽ እኛ የተሻልን ነበርን ግብ ማስቆጠር ግን አልቻልንም።ውጤቱ ለሁለታችንም አስፈላጊ ነበር፡፡የተጨዋቾች እጥረት አለብን በቀጣይም የምናደርጋቸው ጨዋታዎች ትልቅ ፈተና ይጠብቀናል፡፡