በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ተስተካካይ 1ጨዋታ ዛሬ (ሰኞ) ተደርጎ ኢትዮ-ኤሌክትሪክን ከድሬዳዋ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በኃይሌ እሸቱ ብቸኛ ግብ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ጣፋጭ 3ነጥቦችን ማግኘት ችሏል።
ብዙም ማራኪ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኤሌክትሪክ ከተጋጣሚው በተሻለ ወደ ግብ መድረስ ችለዋል። 18ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ግርማ በቀለ ከቅጣት ምት በቀጥታ የመታው ኳስ ወደ ውጭ ወጥቷል። ከ5 ደቂቃዎች በኋላ 23ኛው ደቂቃ ላይ ዲዲዬር ሊብሬ የሞከረውን ኳስ የድሬዳዋ ከተማ ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው በሚያስደንቅ ሁኔታ አውጥቶታል። 27ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው ኩዋሜ አትራም በግሩም ሁኔታ የመታውን ኳስ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ሱሊማን አቡ አውጥቶበታል።
ከዚህ በኋላም ይሄ ነው የሚባል የረባ የጨዋታ እንቅስቃሴም ሆነ የግብ ሙከራ ሳይስተዋልበት የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ ሊጠናቀቅ ችሏል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ነበር ግብ ያስተናገደው። 47ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ዲዲዬር ሊብሬ ያሻገረለትን ኳስ ኃይሌ እሸቱ በድንቅ መረጋጋት እና ብቃት ያስቆጠራት ግብ የጨዋታው ውጤት ቀያሪ መሆን ችላለች። ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ውጤቱን ለማስጠበቅ አፈግፍጎ ከዛም አጋጣሚ ሲገኝ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ሲያደርግ ድሬዳዋ በአንፃሩ ውጤቱን ቀልብሶ ከአ/አ ስታዲየም ነጥብ ይዞ ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። ይህንንም ተከትሎ 50ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው ተከላካይ ያሬድ ዘውድነህ በረዥሙ ያሻገረለትን ኳስ ሙየዲን ሙሳ ከቅርብ ርቀት ሞክሮት ያልተጠቀመበት ኳስ የሚጠቀስ ነበር።
በዚህ መልኩ ጨዋታው እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ 70ኛው ደቂቃ ላይ በአ/አ ስታዲየም የተለመደው አንድ ኩነት ተከሰተ፤ ይኸውም የሜዳው መብራት(ፓውዛ) መጥፋት ነበር። ለ20 ደቂቃዎችም በመጥፋቱ ተጫዋቾቹ እና ሜዳው ውስጥ የተገኙት ደጋፊዎች ሲሰላቹ ተስተውሏል። መብራቱ ከ20 ደቂቃዎች ቆይታ በኋላ የመጣ ሲሆን ጨዋታው ከቆመበት ቀጥሏል።
- ማሰታውቂያ -
75ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ኃይሌ እሸቱ በግራ መስመር በፍጥነት በመግባት ጀማል ጣሰውን አልፎ የሳተው ኳስ ቡድኑን ኢትዮ-ኤሌክትሪክን ወደ አስተማማኝ ውጤት ማድረስ የሚያስችል እና እጅግ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በዚሁም ጨዋታው በኢትዮ-ኤሌክትሪክ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቅ ችሏል።
ውጤቱንም ተከትሎ 1ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው(ከወልድያ ስፖርት ክለብ) ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በ13 ነጥቦች የሰነበተበትን የመጨረሻ ደረጃ ለወልድያ ስፖርት ክለብ በማስረከብ 14ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ተሸናፊው ድሬዳዋ ከተማ በአንፃሩ በእኩል 13ነጥቦች በ3 የግብ ክፍያ በመብለጥ 13ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።