በካፍ ኮንፌደሬሺን ካፕ ምድብ ድልድል ለመግባት የመጀመሪያውን ጨዋታ ለማድረግ ወደ ታንዛኒያ ያቀናው ወላይታ ድቻ ዳሬ ሰላም ላይ በተጋጣሚው ያንግ አፍሪካንስ 2ለ0 ተረቶ የመልሱን የሜዳውን ጨዋታ ከባድ አድርጓል፡፡
በትልቅ መነሳሳት ላይ የነበሩት የጦና ንቦች ከሜዳቸው ውጭ ዛሬ ያስመዘገቡት ውጤት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፉበትና አዲስ ታሪክ በፃፉበት የካፍ ኮንፌደሬሺን ካፕ ወደ ምድብ ድልድል ለመግባት በሚደረገው የመጨረሻ የደርሶ መልስ ጨዋታ ታንዛኒያ ላይ ያስመዘገቡት ውጤት የመልሱን ጨዋታ ተጠባቂም፡ከባድም አድርጓል፡፡ድቻዎች በትልቅ መነሳሳት ላይ እንደመሆናቸው ጨዋታውን ከሜዳቸው ውጭ ወደ ታንዛኒያ ዳሬሰላም አቅንተው ቢያደርጉም ጥሩ ውጤት ያስመዘግባሉ በሚል የስፖርት ቤተሰቡ ተስፋ ቢያደርግም የተመዘገበው ውጤት የስፖርት ቤተሰቡ በመልሱ ጨዋታ ፊቱን ወደ ሶዶ በማዞር በትንሽ ተስፋ የድቻን ወደ ምድብ ድልድል ለማለፍ እንዲጠብቅ ያደረገ ሁኗል፡፡
በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ 1 ደቂቃ ባልሞላ ሽርፍራፊ ሰከንድ ከመስመር በተሻገረ ኳስ ግብ ያስተናገዱት የጦና ንቦች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የነበራቸው የስነ ልቦና ጥንካሬ ድንቅ ነበር፡፡ከሜዳ ውጭ በሚደረግ ጨዋታ በዚህ ሰዓት ግብ ሲቆጠር የሚፈጥረው የስነ ልቦና ችግር ከባድ ቢሆንም ድቻዎች ከዚህ ጫና ወጥተው ኳስን መስርተው በመጫዎት በኩል የተሻሉ ቢሆኑም ግብ ለማስቆጠር ወደ ተጋጣሚያቸው ያንግ አፍሪካንስ የግብ ክልል በመግባት የጠራ የግብ ሙከራ ለማድረግ ግን 40 ደቂቃዎችን ጠብቀዋል፡፡በዚሁ ደቂቃ በተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ጠርዝ ላይ በዛብህ መለዬ ወደ ግብ አክሮ የመታት ኳስ በያንጋው ግብ ጠባቂ ሮስታንድ የዳነበት ብቸኛ የጠራ ተጠቃሺ ሙከራ ነበር፡፡
- ማሰታውቂያ -
በባለሜዳዎቹ ያንግ አፍሪካንስ በኩል ከግቧ መቆጠር በሇላም ቢሆን በተጋጣሚያቸው ድቻ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቢወሰድባቸውም ኳስን በሚያገኙ ጊዜ ግብ ለማስቆጠር የነበራቸው ተነሳሽነት ጨዋታውን በሜዳቸው መጨረስ እንዳሰቡ የሚያመላክት ነበር፡፡በዚህም በ14ኛው እና፡16ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የተቃረቡ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቀሪ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል መሃል ሜዳው ላይ በሚደረጉ ፍትጊያዎች ሲባክኑ የመጀመሪያው አጋማሽ በዚሁ ውጤት ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ድቻዎች የአቻነት ግብ ያስቆጥራሉ ወይስ ባለሜዳዎቹ ያንጋዎች ሌላ ያልተጠበቀ ነገር ያሳያሉ የሚለው የሚጠበቅ የነበረ ሲሆን በጨዋታው መጀመሪያ ንቦቹ የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በገቡበት ቅፅበት ሌላ ግብ በ54ኛው ደቂቃ አስተናግደው ጨዋታው በባለሜዳዎቹ 2ለምንም መሪነት ሲቀጥል፡እንግዳዎቹ ድቻዎች የግብ ዕድል ለማግኘት ቢሞክሩም ያን ያህል የጠራ አልነበረም ፡፡ባለሜዳዎቹ የሜዳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ የዲቻን የግብ ክልል በተደደጋጋሚ ጥሰው ይገቡ ነበር፡፡
ድቻዎች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፉበት በዚሁ የካፍ ኮንፌደሬሺን ካኘ ካደረጓቸው 5 ጨዋታዎች ግብ ባላስቆጠሩበት ያንጋ 2ለ0 ተሸንፈው ጨዋታው ሲጠናቀቅ፡በርካቶች ድቻ ዛማሌክን ያሸነፈበትን ጥንካሬ በማሰብ የመልሱን የሀዋሳውን ጨዋታ ተስፋ አድርገዋል፡፡
የመልሱ ጨዋታ ከ11 ቀናት በሇላ ሀዋሳ ላይ በሀዋሳ ኢንተርናሺናል ስታዲዬም የሚካሄድ ይሆናል፡፡