በ21ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪሚዬር ሰበታ ላይ ፋሲል ከተማን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ በእዮብ አለማየሁ የሐት-ትሪክ ጎሎች ፋሲልን 3-0 አሸንፏል፡፡
ጨዋታው ሶዶ ላይ መካሄድ የነበረበት ቢሆንም የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በወላይታ ድቻ ላይ 2 ጨዋታ ከሶዶ ስታዲዬም 150 ኪሜ ወጥቶ በፌዴሬሽኑ በተመዘገበ ሜዳ እንዲጫዎት በጣለበት ቅጣት ምክንያት ጨዋታው ወደ ሰበታ መጥቷል፡፡
በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ወላይታ ድቻዎች ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ያንጋን ከረቱበት የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች የ2 ተጨዋቾችን ለውጥ በማድረግ ያሬድና ዘላለም ምትክ አምረላና ፀጋዬ ሲገቡ ፡በፋሲል ከተማ በኩል የ1ተጨዋች ለውጥ ሲያደርጉ ፍፁምን በማሳረፍ ከቅጣት የተመለሰውን አምሳሉን ተክተው ገብተዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
25 ደቂቃዎችን ዘገይቶ በበርካታ ደጋፊዎች ታጂቦ ሰበታ ላይ በተካሄደው የወላይታ ድቻና ፋሲል ከተማ ጨዋታ ተመጣጣኝና ፈጣን የኳስ ፍሰት የሚባል ፉክክር የተስተናገደበት ቢሆንም በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች አፄዎቹ የተሻሉ ነበሩ፡፡ለዚህ ማሳያነት ገና ጨዋታው በጀመረ በመጀመሪያ ደቂቃ ፋሲሎች በፍሊፕ ዳውዝ አማካኝነት የግብ ሙከራ ሲያደርጉ የመጀመሪያውን የማዕዘን ምት አግኝተዋል፡፡በ8ኛው ደቂቃ በያሳር አማካኝነት ሌላ የግብ ሙከራ ሲያደርጉ በ14ኛው ደቂቃ ሰንደይ በግራ መስመር ሳጥኑ ውጭ ጠርዝ ላይ አክሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ ለትንሽ በግቡ ቋሚ ወጥቷል፡፡በወላይታ ድቻዎች በኩል በ19ኛው ደቂቃ በዛብህ ወደ ፋሲል የግብ ክልል ከመሀል ሜዳ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ የፋሲል ተከላካዮችና ግብ ጠባቂው ሳማኪ የሰሩትን ጥፋት ተጠቅሞ እዮብ አለማየሁ ግብ አስቆጥሮ ንቦቹ ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡
ከግቧ መቆጠር በሇላም የግብ ሙከራ በተደጋጋሚ በታጀበበት ጨዋታ በ24ኛው ደቂቃ ፋሲሎች አምሳሉና ያሳር አንድ ሁለት ተቀባብለው ያሳር ወደ ግብ ያሻማውን ፍሊኘ በጭንቅላቱ ገጭቶ የሞከረው ኳስ በግቡ ቋሚ ስትወጣ በድጋሚ ኤርሚያስ ከያሳር የተሻገረለትን ኳስ ሞክሮት የዲቻው ግብ ጠባቂ ወንደሰን ኳሷን ባወጣበት ቅፅበት ወደ ግቡ ሳይመለስ በድጋሚ ኤርሚያስ ወደ ግብ የመታት ኳስ በዲቻ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውታል፡፡የጦና ንቦቹ በ32ኛው ደቂቃ በረጅሙ ያሻገሩትን ኳስ ከሳማኬ ጋር የተገናኘው ጃኮ ኳሷን ሙሉ ለሙሉ ሳያገኛት ተሸራቶ ጨርፏት ወደ ውጭ ለትንሽ በግቡ ቋሚ ታካ ስትወጣ በ40ኛው ደቂቃ ፋሲሎች የአቻነት ግብ ፍለጋ እንደወጡ ድቻዎች በአብዱልሰመድ በረጅሙ ያሻገሩትን ኳስ የፋሲል ከተማው ግብ ጠባቂ ኳሷን ለመያዝ ግቡን ለቆ በወጣበት እዬብ ከበዛብህ ጣጣውን ጨርሶ የደረሰውን ኳስ ወጋ አድርጎ ከመረብ ጋር በማገናኘት ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሮ የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አመርተዋል፡፡
በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ በሙሉ ሃይላቸው አጥቅተው መጫወት የጀመሩት ፋሲሎች በ49ኛውና በ53ኛው ደቂቃ በያስር አማካኝነት ያለቀላቸው የግብ ሙከራዎችን ተቀይሮ በገባው ራምኬል አማካኝነት በ59ኛው ደቂቃ በተጨማሪም በአምበሉ ሄኖክ አማካኝነት ከመሃል ሜዳ በረጅሙ አክሮ የመታት ኳስ ሌላ የግብ ሙከራ ሲያደርጉ ግብ በማስቆጠር ባይችሉም በ77ኛው ደቂቃ ድቻዎች በግብ ክልላቸው ኳስ በእጅ በመንካታቸው ፋሲሎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ከድር መትቶት የድቻው ወንደሰን ፍፁም ቅጣት ምቱን አምክኖበታል፡፡ፋሲሎች ከዚህ በሇላ ተነሳሽነታቸውም ተቀዛቅዞ የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ድቻዎች በ90ኛው ደቂቃ እዮብ ለራሱም ለቡድኑም 3ኛ ግብ በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሰርቶ ጨዋታው በወላይታ ድቻ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
የጨዋታውን ውጤት ተከትሎ ድቻዎች ነጥባቸውን 27በማድረስ 2 ተስተካካይ ጨዋታው እያለቸው በሰንጠረዡ 9ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ፋሲሎች በ32 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡