በ6ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ(ቅዳሜ) 6ጨዋታዎች ተደርገዋል። ከነዚህ ጨዋታዎች አንዱ የነበረው እና ወልቂጤ ላይ በወልቂጤ ከተማ እና ስሑል ሽረ መካከል የተደረገው ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል።
በፌደራል አርቢትር አሸብር ሰቦቃ የተመራው እና 9:00 ሲል ጅማሮውን ያደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል። ቀዝቀዝ ብሎ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የረባ እንቅስቃሴ ሳይስተዋልበት ተካሂዷል። በጨዋታው ወልቂጤ ከተማ የስሑል ሽረን የተደራጀ የተከላካይ ክፍል ለማስከፈት ረጃጅም ኳሶች ሲጠቀሙ ታይተዋል። ስሑል ሽረዎች በአንፃሩ በጥልቅ በመከላከል በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ምርጫቸው አድርገው ታይተዋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በወልቂጤ ከተማ በኩል ጃኮ አረፋት ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን የስሑልጨሽረ ተከላካዮች የሚሰሩትን ስህተት ለመጠቀም ጥረት ሲያደርግ ውሏል። የስሑል ሽረ ተጫዋቾችም አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ ወደኋላ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት የወልቂጤ ከተማን የኋላ ክፍል ለማስከፈት እና ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ይህንንም ተከትሎ ጨዋታው ያለግብ ሊጠናቀቅ ተገዷል። ውጤቱንም ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ በ8ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ስሑል ሽረ ደግሞ በ6ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ሊጉን ፋሲል ከተማ እና ወልዋሎ አ.ዩ. 11 ነጥቦች በግብ ክፍያ ተለያይተው አንደኛ እና ሁለተኛ ሲሆኑ መቐለ 70 እንደርታ በ10 ነጥቦች ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል። የኮከብ ጎል አግቢነቱን ደግሞ የፋሲል ከተማው ሙጂብ ቃሲም በ6 ግቦች ሲመራ የኢትዮጵያ ቡናው እንዳለ ደባልቄ፣ የባህርዳር ከተማዎቹ ማማዱ ሲዲቤ እና ፍፁም ዓለሙ፣ የፋሲል ከተማው ኦሴይ ማውሊ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማው ብሩክ በየነ በእኩል 4 ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።