ትግራይ ስታድየም ላይ የተካሄደው የወልዋሎና የጅማ አባጅፋር ጨዋታ ምንም ግብ ሳያስተናግድ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።ከሥስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥቦችን መሰብሰብ የቻሉት የዮውሀንስ ሳህሌ ልጆች ባሳላፍነው ሳምንት ስሑል ሽሬ ላይ ድል ከተቀዳጀው ስብስብ ሥስት ተጨዋቾችን በጉዳት ምክንያት ቀይረዋል።አሞስ አቼምፖንግ፣ካርሎስ ዳምጠው፣ፍቃዱ ደነቀ በሄኖክ መርሹ፣ሚኪኤሌ ለማና ሰመረ ሀፍታይ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።በጳውሎስ ጌታቸው ሚመሩት ጅማዎች በበኩላቸው ከሲዳማው ሽንፈት አንድ ቅያሪ እሱም አምረላ ደልታታን በጀሚል ያቆብ ቀይረዋል።
በአንጻራዊነት የባለሜዳዎቹ በላይነት በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የታዩበት ነበር።በ4-3-1-2 የጨዋታ አቀራረብ ወደ ሜዳ የገቡት ወልዋሎዎች ከሁለቱም መስመር በሚነሱ ኳሶች እድሎችን መፍጠር ችለዋል።የጨዋታው የወልዋሎ የመጀመርያ ሙከራ መሀል ላይ ወደ ቀኝ መስመር አድልቶ ሲጫወት የነበረው ሚኪኤል ለማ በረጅሙ ያሻገረው ኳስ ነጻ አቋቋም ላይ የነበረው ጁንያንስ በቀጥታ ሲመታው ከግቡ አናት ለትንሽ ወጥቷል።ከመስመር በሚነሱ ኳሶች የጅማ ተከላካይ ክፍልን የመረበሽ እንቅስቃሴያቸውን ያስቀጠሉት ጅማዎች አሁንም ከቀኝ መስመር ምስጋናው ዮውሀንስ ያሻማውን ኳስ ወጣቱ አጥቂ ሰመረ ሀፍታይ በግምባሩ ገጭቶት ለጥቂት ወደ ውጭ ሊወጣ ችሏል።ጅማ አባጅፋር አብዛኛውን የመጀመርያ አጋማሽ በራሳቸው ሜዳ ያሳለፋ ሲሆን አልፎ አልፎ ከቀኝ መስመር በኤርሚያስ ሃይሉ አማካኝነት ለማጥቃት ሙከራዎችን አድርገዋል።በተለይ የመጀመርያ አጋማሽ ማጠናቀቂያ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ ጀሚል ያቆብ በግምባሩ ገጭቶት አብዱላዚዝ ኬይታ መልሶበታል።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው አጋማሽ ስምኦን ማሩን በሚኪኤለ ለማ ቀይረው የገቡት ወልዋሎዎች እንደ መጀመርያው አጋማሽ በተመሳሳይ መልኩ መስመር ላይ ትኩረት አድርገው ቢንቀሳቀሱም አሸናፊ ሚያደርጋቸው ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።በሁለተኛው አጋማሽ ቀኝ መስመር ተከላካይነት ወደ መስመር አጥቂነት የተሸጋገረው ምስጋናው ዮውሀንስ ከቀኝ መስመር ወደ መሀል ሰብሮ በመግባት የመታው ኳስ የጨዋታው ኮከብ ሰኢድ ሀብታሙ ሲመልስበት፤ሰኢድ የተፋውን ኳስ ከግቡ በቅርብ ርቀት የነበረው ሰመረ ለመምታት ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል።ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ወልዋሎዎች ጁንያስ ናንጂቡ ሳሙኤል ዮውሃንስ ከግራ መስመር ያሻማለትን ኳስ በግምባሩ በመግጨት የሞከረው ኳስ አሁንም ሰኢድ ሀብታሙ ሊመልስለት ችሏል።የጅማዎችን መከላከል ለማለፍ የተቸገሩት ወልዋሎዎች በጨዋታው በተከላካይ አማካይነት የተሰለፈውን ሄኖክ መርሹን በአጥቂው ብሩክ ሰሙ በመቀየር የአጥቂነት ባህሪ ያላቸውን ተጨዋቾቻቸውን ቁጥር በመጨመር የግብ እድሎችን መፍጠር ቢችሉም የጅማን መርበብ መድፈር ሳይችሉ ቀርተዋል።በተለይ ተቀይሮ የገባው ብሩክ ሰሙ ከግራ መስመር ራምኬል ሎክ አሻምቶለት ያገኘውን ኳስ በግምባሩ ቢገጨውም ከግቡ ጎን ሊወጣ ችልዋል።በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ መከላከልን ምርጫጨው ያደረጉት ጅማዎች የጨዋታው መጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በጀሚል ያቆብ እና ተቀይሮ በገባው ሀብታሙ ንጉሴ አማካኝነት ከርቀት በመምታት ያደረጉዋቸው ሙከራዎች በአብዱላዚዝ ኬይታ ተመልሰዋል።በዚህም መሰረት ጨዋታው ያለግብ አቻ ሊጠናቀቅ ችሏል።
ውጤቱን ተከትሎ ወልዋሎ የዓመቱ የመጀመርያ ነጥቡን ሲጥል ጅማዎች ነጥባቸውን ወደ 3 ከፍ አድርገው 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።