በ15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ(ሰኞ) ሲካሄድ በአ/አ ደርቢ ደደቢት ከ መከላከያ ተጫውተው የሊጉ መሪ ደደቢት በመጀመሪያዎቹ እና በመጨረሻዎቹ 10ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው 4 ግቦች 4-0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ መሪነቱን ያጠናከረበትን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።
በጨዋታው አጥቂዎቹን ጌታነህ ከበደን እና አቤል ያለውን ሳይይዝ ወደሜዳ የገባው ደደቢት በጨዋታው ከተጋጣሚው መከላከያ ተሽሎ የቀረበ ነበር። ከሁለቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ደደቢት ከጅማ አባጅፋር ጋር ከተደረገው ጨዋታ በኋላ በነበረው ቃለመጠየቅ በዳኞች ላይ የማይገባ ንግግር ተናግረዋል በሚል የ3 ወራት ቅጣት ተጥሎባቸዋል። ይህንንም ተከትሎ የዛሬውን ጨዋታ መምራት አልቻሉም።
ይህ ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ ለማስተናገድ 2ደቂቃዎች ብቻ ነበረ ያስፈለጉት። 2ኛው ደቂቃ ላይ አኩዌር ቻሞ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ደደቢትን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። በዚህች ግብ መቆጠር ምክንያት መረጋጋት የተሳናቸው መከላከያዎች ቶሎ ቶሎ ኳስ ሲበላሽባቸው ተስተውሏል። ከግቧ መቆጠር 8ደቂቃዎች በኋላ 10ኛው ደቂቃ ላይ አኩዌር ቻሞ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር በመጀመሪያዎቹ 10ደቂቃዎች ውስጥ 2-0 እንዲመሩ አስችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ደደቢቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ብልጫ መውሰድ የቻሉ ሲሆን በተለይ የመሀል ሜዳ ክፍል ላይ ላቅ ያለ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። በአንፃሩ መከላከያዎች በተቆጠረባቸው ሁለት ፈጣን ግቦች ተደናግጠው ተስተውለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ደደቢቶች የኤፍሬም አሻሞን ፍጥነት በመጠቀም በመልሶ ማጥቃት ወደ መከላከያ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ ሙከራ ሲያደርጉ ታይተዋል።
20ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ሳሙኤል ሳሊሶ በግሩም ሁኔታ የመታውን ኳስ የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ክሌመንት አዞንቶ በድንቅ ሁኔታ ወደ ውጭ አውጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ የመከላከያዎቹ ሳሙኤል ሳሊሶ፣ ምንይሉ ወንድሙ እና የተሻ ግዘው ተደጋጋሚ ሙከራ በማድረግ ወደ ጨዋታው ሪትም ለመግባት ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ምንም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተው ወደ መልበሻ ቤት ሊያመሩ ችለዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ተሽለው ለመቅረብ ጥረት ያደረጉት መከላከያዎች በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም ኢላማውን የጠበቀ ባለመሆኑ ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል። የመከላከያው ሳሙኤል ታዬ ያገኘውን ቅጣት ምት ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ክሌመንት በቀላሉ ይዞታል። የመከላከያው በኋላ ግርማ ከማዕዘን ምት የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ ቢገጨውም ኳሱ ወደ ውጭ ወጥቷል። 66ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ ከቅጣት ምት የሞከረው ኳስ በርቀት ወደውጭ ሲወጣ እንዲሁም 74ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ታዬ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ የመታውን ኳስ የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ክሌመንት አዞንቶ በቀላሉ ይዞታል።
የመደበኛው የጨዋታ ክ/ጊዜ ሊጠናቀቅ 10ደቂቃዎች ሲቀሩት 80ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ ተከላካይ ስዩም ተስፋዬ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን 3-0 እንዲመራ አስችሎታል። ከ8ደቂቃዎች በኋላ 88ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ሌላ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በደደቢት 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
- ማሰታውቂያ -
የአሰልጣኞች አስተያየት
ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ -ደደቢት
“በዛሬ ጨዋታ ቡድናችን ጥሩ ነበር:: እሚያስፈልገንን 3ነጥብ አሳክተናል፡፡”
አሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ -መከላከያ
“በዛሬው ጨዋታ የአቋም መውረድ ሳይሆን ባለን በሌለን ሀይል አጥቅተን ለመጫወት ጥረት አድረገናል፡፡ ሆኖም እነሱ ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው ወጥተዋል::”