በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት አንድ ጨዋታ አ/አ ስታዲየም ላይ ሲደረግ መሪው ደደቢት እና አዲስ አዳጊው ወልዋሎ አ.ዩ. ተገናኝተው ባለሜዳው ደደቢት ከሙሉ የጨዋታ ብልጫ ጋር 4-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
በጨዋታው ደደቢት በ4-4-2 የጨዋታ ዘይቤ ወልዋሎ አ.ዩ. በአንፃሩ በ4-3-3 የጨዋታ ዘይቤ ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ከጨዋታው መጀመር በፊት የደደቢት እግር ኳስ ክለብ በቅርቡ ህይወታቸው ያለፈውን የወልዋሎ አ.ዩ. መስራች አቶ ሰለሞን ገ/ፃዲቅ በማሰብ ፎቷቸው የታተመበትን ስጦታ ለወልዋሎ አ.ዩ. አምበል አበርክተዋል።
ጨዋታው በተመጣጣኝ ሁኔታ የተጀመረ ሲሆን የመጀመሪያውን ሙከራ ማድረግ የቻሉት ወልዋሎዎች ነበሩ። 5ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ፕሪንስ ሰቨርኒሆ ከቀኝ የሜዳው ክፍል ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ክሌመንት አዞንቶ በቀላሉ ይዞታል። ከዚህ ሙከራ 3ደቂቃዎች በኋላ የወልዋሎ አ.ዩ. ተከላካይ ተስፋዬ ዲባባ የሰራውን ስህተት የተገኘውን ኳስተጠቅሞ የደደቢቱ አማካይ ሽመክት ጉግሳ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ በመጀመሪያዎቹ 10ደቂቃዎች ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከዚህ ግብ መቆጠር በኋላ ሙሉ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ደደቢቶች በተደጋጋሚ የወልዋሎን የግብ ክልል መፈተሽ ችለዋል። 17ኛው ደቂቃ ላይ ወጣቱ የደደቢት አጥቂ አቤል ያለው ከግብ ጠባቂው ጋር 1-1 ተገናኝቶ የሞከረውን ኳስ የወልዋሎ ግብ ጠባቂ ዘውዱ መስፍን ይዞታል። ከ2 ደቂቃዎች በኋላ አቤል ያለው በድጋሚ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ተከላካዮችን በግሩም ሁኔታ አታሎ የሞከረው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥቷል። ይህ ሙከራ በርካታ አማራጮች ለነበሩት አቤል ያለው በመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ የሚያስቆጭ ነበር። በዕለቱ ድንቅ ሆኖ ያመሸው የአብስራ ተስፋዬ በድንቅ ሁኔታ አታሎ ያሻገረለትን ኳስ ጌታነህ ከበደ በማስቆጠር ቡድኑ ደደቢት 2-0 እንዲመራ አስችሎታል። በተደጋጋሚ ፍጥነቱን በመጠቀም የወልዋሎ ተከላካዮችን ሲያስጨንቅ የዋለው አቤል ያለው ድንቅ ብቃቱ ላይ መገኘቱ የንጉሴ ደስታን ቡድን አስፈሪ አድርጎታል። ይህንንም ተከትሎ 38ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ መትቶት ለራሱ ሁለተኛውን ለቡድኑ ሶስተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ይህንን ፍፁም ቅጣት ምት ተከትሎ የወልዋሎ ደጋፊዎች ቅሬታቸውን ሲገልፁ ተስተውለዋል።
በመሀል ሜዳ ክፍል ላይ እጅግ ከፍተኛ ብልጫ የተወሰደባቸው ወልዋሎዎች አልፎ አልፎ ወደ ደደቢት የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ይህንንም ተከትሎ 42ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤል ግርማ የደደቢት ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ አግኝቶ የሞከረውን ኳስ በዛሬው ጨዋታ ብዙ ስራ ያልበዛበት የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ክሌመንት አዞንቶ በቀላሉ ይዞታል።
የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ ሰዓት ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩት የደደቢት ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ከጉዳት የተመለሰው የወልዋሎ አጥቂ ሙሉዓለም ጥላሁን መትቶ ቡድኑን ከሽንፈት ያላዳነችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል። በዚሁም ሁለቱ ቡድኖች በደደቢት 3-1 መሪነት ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ወርዶ የቀረበው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ45 ደቂቃ ውስጥ ከ 3 ወይም ከ4 ያልበለጡ ሙከራዎች ተደርገውበት ሊጠናቀቅ ችሏል። ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ 8ኛው ደቂቃ ላይ 53ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ የግራ ተከላካይ ሰለሞን ሀብቴ ከግራ ክንፍ ያሻገረውን ኳስ አጥቂው ጌታነህ ከበደ በግንባሩ ሞክሮት የወልዋሎው ግብ ጠባቂ ዘውዱ መስፍን በቀላሉ ይዞታል። 61ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ አማካይ አቤል እንዳለ ከመዓዘን ያሻገረውን ኳስ ተከላካዩ ስዩም ተስፋዬ በግንባሩ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ደደቢት አሸናፊነቱን እንዲያረጋግጥ አስችሏል። እጅግ የተቀዛቀዘው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ለደጋፊዎችም አስደሳች አልነበረም። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 10ደቂቃዎች ሲቀሩት 80ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ ሺመክት ጉግሳ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት ስዩም ተስፋዬ በቀጥታ ወደግብ ሞክሮት የወልዋሎው ግብ ጠባቂ ዘውዱ መስፍን በቀላሉ ይዞታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ አንድም የረባ ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታው በደደቢት 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
የደደቢት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ
“የተጋጣሚአችን ቡድን እንቅስቃሴ በመከላከል ላይ እና በመሀል ሜዳ ላይ ያመዘነ ስለነበረ በመጫን እና በፈጣን ማጥቃት ሙሉ ለሙሉ ጨዋታውን ተቆጣጥረን አሸንፈን መውጣት ችለናል። በተጫዋቾቼ በጣም ደስተኛ ነኝ።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የወልዋሎ አ.ዩ. ዋና አሰልጣኝ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር
“የዛሬው ጨዋታ ላይ የነበረብን ትልቁ ችግር የልምድ ጉዳይ እና በራሳችን ስህተቶች በተቆጠሩብን ጎሎች ተሸንፈናል። መሀል ክፍላችን ላይ ተጨማሪ ተጫዋቾች አስፈርመን በመጨመር ተሻሽለን ለመቅረብ እንሞክራለን።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።