በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ዛሬ ሲጀመር በቅድሚያ የተገናኙት ፋሲል ከተማ እና ወልዋሎ አ.ዩ ነበሩ። በጨዋታውም ፋሲል ከተማ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
8:08 ሲል የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ ለማስተናገድ የፈጀበት 1ደቂቃ ብቻ ነበር። የወልዋሎ አ.ዩ. ግብ ጠባቂ ዘውዴ መስፍን ለጓደኞቹ ወርውሬ አቀብላለሁ ሲል በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሮት ፋሲልን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከዚህ በኋላ ቀዝቀዝ ብሎ የተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሙከራ ሳይደረግበት 17ደቂቃዎችን መዝለቅ ችሏል። 17ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ፕሪንስ ሰቨርኒሆ ከግራ በኩል ያሻገረለትን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ ይገኝ የነበረው ከድር ሳሊህ ተንሸራቶ ቢሞክረውም ሳይደርስበት ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ምንም እንኳን በጨዋታው ጅማሬ ግብ ቢቆጠርባቸውም ወልዋሎዎች ባለመደናገጥ ወደ ፋሲል ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል።
26ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል ወደግብ መድረስ የቻሉት ወልዋሎዎች ፕሪንስ ሰቨርኒሆና ሙሉዓለም ጥላሁን መናበብ ባለመቻላቸው ፕሪንስ ሰቨርኒሆ በግራ እግሩ የመታው ኳስ በርቀት ወደውጭ ወጥቷል። ሁለቱ ተጫዋቾች መናበብ ቢችሉ ኖሮ የአቻነቷን ግብ ማስቆጠር ይችሉ ነበር። ከ4 ደቂቃዎች በኋላ 30ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ፕሪንስ ሰቨርኒሆ በግል ጥረቱ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደግብ በግራ እግሩ አክርሮ የመታውን ኳስ የፋሲሉ ግብ ጠባቂ ሚካኤል ሳማኬ በግሩም ሁኔታ አውጥቶታል።
ግቡ ከተቆጠረበት ደቂቃ ጀምሮ የወልዋሎ ተጫዋቾች ተጭነው የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ፋሲል ከተማዎች በአንፃሩ ወደኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። 45ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ከድር ሳሊህ ከሳጥን ውጪ አግኝቶ የሞከረው ኳስ በተከላካዮች ተደርቦ ወደውጭ በመውጣቱ የማዕዘን ምት መሆን ችሏል። ከዚህ በኋላ ይሄ ነው የሚባል ሙከራ ሳይደረግበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ችሏል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ሞቅ ብሎ የተጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል መሻሻል የታየበት እና በተደጋጋሚ ወደግብ በመድረስ ግብ ጠባቂዎች ስራ በዝቶባቸው የዋሉበት ነበር።
- ማሰታውቂያ -
59ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ሙሉዓለም ጥላሁን ከቀኝ በኩል ግሩም ኳስ ቢያሻግርም የሚጠቀምበት ተጫዋች ባለመኖሩ እድሉ ባክኗል። 62ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማው አምሳሉ ጥላሁን ከቅጣት ምት ያሻገረለትን ኳስ በጨዋታው ድንቅ ሆኖ የዋለው አብዱራህማን ሙባረክ(ግሪዳው) በግንባሩ ገጭቶት ለጥቂት ወደውጭ ወጥቷል። ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ወደ ኋላ በማፈግፈግ እና በተገኙት አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት ወደ ወልዋሎ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ይህንን ተከትሎ 69ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማው መሀመድ ናስር የወልዋሎውን ግብ ጠባቂ ከግብ ክልሉ መውጣት ተመልክቶ ወደግብ የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥቷል። 70ኛው ደቂቃ ላይ በወልዋሎ አ.ዩ. በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ከድር ሳሌህ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞበታል። የጨዋታው መጠናቀቂያ እየተጠበቀ በነበረበት ሰዓት 94ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ፕሪንስ ሰቨርኒሆ በድንቅ ሁኔታ ተከላካዮችን አታሎ ወደግብ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው በድንቅ ሁኔታ አውጥቶታል። ይህ ሙከራም የጨዋታው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በፋሲል ከተማ 1-0 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ — ፋሲል ከተማ
“እስከዛሬ የምንታወቅበትን አጨዋወት አይደለም የተጫወትነው፤ የምንፈልገውን 3ነጥብ አሳክተናል፤ ከጨዋታ ጨዋታ ቡድናችን ይስተካከላል ብዬ አስባለሁ። ከሁሉም በላይ ግን ወሳኙ ነገር 3ነጥብ ማሳካት ነበር እሱን በማድረጋችን በጣም ደስተኛ ነኝ።”
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማሪያም — ወልዋሎ አ.ዩ.
“ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ ያው ዛሬ ተሸንፈናል፤ የገባብን ግብ በተጋጣሚ ብቃት የተገኘ ሳይሆን በራሳችን የግል ስህተት የተቆጠረ ነው፤ የተቆጠረው ግብ የጨዋታው ጅማሬ ላይ በመሆኑ ተጫዋቾቻችን ላይ የመደናገጥ ስሜት ፈጥሯል። በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ተጠናክረን ለመቅረብ ጥረት እናደርጋለን።”