ለወራቶች ሲያወዛግብና መፍትሔ አጥቶ የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ በፊፋ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ይመስላል።
ፊፋ ለበርካታ ወራቶች የእግር ኳሱን መንደር ሰላም ነጥቆ ለቆየውና አልቋጭ ብሎ ላስቸገረው ውዝግብ መፍትሄ ይሆናል ብሎ ያመነበትን ውሳኔ የፊፋ አጣሪ ኮሚቴ ይፋ አድርጓል።
ትናንት ምሽት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደረሰ እንደተባለውና ሀትሪክ ከታማኝ ምንጮቿ እንዳገኘችው መረጃ መሠረት የፊፋ አጣሪ ኮሚቴ ከሁለት ሳምንት በፊት ያደረገውን ማጣራት ተከትሎ የመጨረሻ ያለውን ውሳኔ በመወሰን ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ አሳውቋል።
ሀትሪክ ጋዜጣና ድረ ገፅ እንዳገኙት መረጃ ከሆነ ፊፋ ትናንት ምሽት በላከው ደብዳቤና ውሳኔ መሠረት ቀደም ሲል በአስመራጭነት ሲሰራ የነበረው ኮሚቴ ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስና አዲስ አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም ለፕሬዚዳንትነትና ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ሲወዳደሩ የነበረው በሙሉ እንዲሰረዝና እንደ አዲስ ዕጩዎች እንዲቀርቡ ፌዴሬሽኑም አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት የፊፋን የምርጫ ህግ እንዲያፀድቅና በህጉ መሠረትና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ምርጫውን እንዲያከናውን የፊፋ አጣሪ ኮሚቴ ጠንከር ያለ ውሳኔ አስተላልፏል።
ይህ የፊፋ ውሳኔ ያልተጠበቀና ብዙዎችን ያስደነገጠ ሲሆን በተለይ ለስልጣን ሲቋምጡ የነበሩና ለውዝግቡ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ ግለሰቦች በውሳኔው ክፉኛ መደናገጣቸው የተሰማ ሲሆን በፊፋ አጣሪ ኮሚቴ ውሳኔ መሠረት ክልሎች አዳዲስ ዕጩዎችን ሲመርጡ አሁን ከሰሩት ስህተት በመታረም በጥንቃቄ መምረጥ እንዳለባቸው ነው አስተያየት ሠጪዎች የሚናገሩት።
ሰበር ዜና | በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የፊፋ አጣሪ ኮሚቴ ውሳኔ ለፌዴሬሽኑ ተላከ አስመራጭ ኮሚቴው እንዲፈርስ ዕጩ ተወዳዳሪዎችም እንደ አዲስ እንዲወዳደሩ ወሰነ
Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.