በይስሀቅ በላይ
በያዝነው የውድድር ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያደገው የሰበታ ከተማ እግር ኳስ ቡድን የዲያጆ አካል ከሆነው የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ጋር የ18.5 ሚሊዮን ብር የአጋርነት (ስፖንሰርሺፕ) ድጋፍ ስምምነት ባለፈው ማክሰኞ የድርጅቱና የሰበታ ከተማ ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ እንግዶችና የሚዲያ አካላት በተገኙበት በኢንተርኮንቲኔታል ሆቴል ተፈራርመዋል፡፡
ሰበታ ከተማ እና ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ የስፖንሰርሺፕ (የድጋፍ) ስምምነት ያደረጉት ለአራት ዓመታት ሲሆን ስምምነቱም በአራት ደረጃዎች የተከፋፈለ እንደሆነ በእለቱ በኢንተርኮነቲኔታል ሆቴል በተደረገው የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ ለተገኙት እንግዶችና የሚዲያ አካላት ይፋ አድርገዋል፡፡ በዕለቱ በነበረው ስነ ስርዓት ላይ እንደተገለፀው በአራት ደረጃዎች በተከፋፈለው የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት በመጀመሪያው ዓመት 3.5 ሚሊዮን፣ በሁለተኛው ዓመት በ3 ሚሊዮን፣ በሶስተኛው እና በአራተኛው ዓመት ደግሞ በእያንዳንዳቸው የአራት አራት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ መስማማታቸው ነው የተገለፀው፡፡
ከዚሁ ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ለሰበታ ከተማ ደጋፊዎች የተለያዩ የድጋፍ መስጫ ቁሳቁሶችን ለሶስት ዓመታት የሚያቀርቡ ሲሆን ክለቡ ቁሳቁሶችን ለደጋፊው በመሸጥ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዲያገኝ እንደሚረዳውም ነው የተገለፀው፡፡ ሜታ አቦ ከሚያደርገው የቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ በመጀመሪያው ዙር የድጋፍ ትግበራው የክለቡን ስታዲየም የማደስ ከዚሁ ጋር የምድር ቁፋሮ፣ የማዳበሪያ እና የሜዳ ሳር ተከላንም እንደሚከታተል ነው የተገለፀው፡፡
- ማሰታውቂያ -
በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝተው ንግግር እንዳደረጉት የኩባንያው የመንግስት ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳግማዊ ሸዋንግዛው “በየጊዜው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እያደገ ብዙ ተመልካች እየሳበ መምጣቱን ለማስተዋል ችለናል” ካሉ በኋላ “የእግር ኳሱ እያደገ መምጣትም ኩባንያችን ለሰበታ ከተማ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ እግር ኳስ መሻሻል የበኩላችንን የምንወጣበት ሰዓት መሆኑን ለመረዳት አስችሎናል” ብለዋል፡፡
“የሰበታ ከተማ እግር ኳስ ቡድን አጋዥ በሚፈልግበት ጊዜ መምጣቱ አስደስቶናል” በማለት በዕለቱ ንግግር ያደረጉት የሰበታ ከተማ ስፖርት ክለብ የበላይ ጠባቂ የሆኑት አቶ ብርሃኑ በቀለ “የተፈረመው አጋርነት ቡድኑን የሚያጠናክርና ለፕሪምየር ሊጉ የተሻለ ተፎካካሪ እንዲሆን ያደርገዋል” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ቀደም ሲል የመንግስት የነበረውና በ225 ሚሊዮን ዶላር ወደ ዲያጆ ይዞታነት የተዘዋወረው ሜታ አቦ ቢራ በ1959 ዓ.ም የተመሠረተ በኢትዮጵያ ቀደምት ቢራ ጠማቂ ከሆኑት ፋብሪካዎች አንዱ ሲሆን ዲያጆ ከተረከበተው ጊዜ ጀምሮ ለፋብሪካው ማስፋፊያ ከ119 ሚሊዮን ዶላር በላይ ፈሰስ በማድረግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማገዝ ላይ የሚገኝ ግዙፍ ድርጅት ነው፡፡ ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማገዝ መዋዕለ ነዋዩን በማፍሰስና ማህበራዊ ኃላፊነቱን በከፍተኛ ሁኔታ በመወጣቱ ከወዲሁ በብዙዎች ዘንድ አድናቆት እየተቸረው ይገኛል፡፡