በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ዉድድር ለመሳተፍ ባለፈው ሐሙስ ረፋድ ላይ ወደ ሲሸልስ የተጒዘዉ ቅ.ጊዮርጊስ የአዲሱ የዉድድር ዘመን የቻምፒዮንስ ሊግ ዘመቻውን በድል ጀመረ ፤ቅ.ጊዮርጊስ ሳላህዲን ሰይድ ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ባለሜዳዉ ኮት.ዲ.ኦርን በማሸነፍ የቻምፒዮንስ ሊግ አጀማመሩን አሳምራል።
13 ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን በማንሳት በሀገር ዉስጥ ዉጤታማ የሆነው ቅ.ጊዮርጊስ የመልስ ጨዋታውን በመጪው እሁድ ሀዋሳ ላይ የሚያደርግ ሲሆን በድምር ውጤት ተጋጣሚዉን ካሸነፈ ወደ ምድብ ድልድል ለመግባት የሚያስችለውን ውጤት ለማግኘት ከኮንጎው ሊዮፓርድ እና ከካሜሩኑ ዩኤምኤስ ዲ ሉም አሸናፊ ጋር እንደሚያደርግ የካፍ መርሃ ግብር ይጠቁማል ።የቅ.ጊዮርጊስን ጨዋታ ለመከታተል የክለቡ የቦርድ ሊቀመንበር እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ወደ 35 የሚጠጉ ደጋፊዎች አብረው መጒዛቸውና ቡድኑን ማበረታታቸዉ ተሰምቷል።
ከጨዋታዉ በፊት ለካፍ ኦን ላይን መግለጫ የሰጡት የክለቡ የቦርድ ሊቀመንበር “ወደ እዚህ የመጣነው ለማሸነፍ ነው” ያሉ ሲሆን የቡድኑ የፊት አጥቂ አዳነ ግርማ በበኩሉ ጨዋታዉን ለማሸነፍ እና ብዙ ርቀት የመጒዝ ሃሳብ እንዳለው ገልፃ ይህን ለማሳካት ያለንን አቅም መጠቀም አለብን በማለት ከጨዋታው በፊት አስተያየቱን ለካፍ ኦን ላይን መስጠቱ ይታወሳል።የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በድል ያጠናቀቁት ቅ.ጊዮርጊሶች ሰኞ ረፋድ ወደ አ.አ ይመለሳሉ።