ቅዳሜ 10፡00 ሰዓት
የኢትዮጵያ ተናፋቂው፣ አጓጊው እንደዚሁም ደግሞ በሁሉም የስፖርት ቤተሰቦችም ሆነ
የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ዘንድ እየተጠበቀ ያለው ታላቁ የሸገሩ ደርቢ
ጨዋታ የፊታችን ቅዳሜ ማለትም በፋሲካው ዋዜማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10፡00
ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ባለሜዳ በሆነበት በእዚህ ጨዋታ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ በርካታ
ተመልካች ወደሜዳ ስለሚመጣ ክለቡ ከእዚሁ ጨዋታ ከፍተኛ ሊባል የሚችልንና በፕሪምየር
ሊጉም ደረጃ እስካአሁን ካገኘውም ሪከርድ የሆነን ክፍያ ያገኛል ተብሎም ተጠብቋል፤
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዘንድሮ በርካታ የስፖርት አፍቃሪዎች እየተከታተሉት እና
ወደሜዳም እየጎረፉ ባሉበት ሰዓት የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች አሁንም ለየት
ያለን የአደጋገፍ ስርዓት በቅዳሜው የደርቢ ጨዋታም ላይ ይዘው ለመምጣት መሰናዶአቸውን
ያጠናቀቁ ሲሆን የሁለቱ ቡድን ተጨዋቾችም በደርቢው ፍልሚያ ለተመልካቹ ጥሩ የሆነን
ጨዋታ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ለማሳየትም መዘጋጀታቸውን እና በዕለቱም ጨዋታ
ቡድኖቻቸውንም ለአሸናፊነት ለማብቃትም ጥረትን እንደሚያደርጉ ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ
አስተያየታቸውን ሊሰጡ ችለዋል፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች በሸገሩ ደርቢ ጨዋታ በእስከዛሬ የእርስ በእርስ
ግንኙነታቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ 19 ጊዜ ሲያሸንፍ፤ ኢትዮጵያ ቡና 7 ጊዜ ማሸነፍ ችሏል፤
9 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፤ በዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር ኢትዮጵያ ቡና 1-0 በሆነ
ውጤት ያሸነፈ ሲሆን የሁለተኛው ዙር ውጤት ደግሞ ቅዳሜ 12 ሰዓት ላይ ይታወቃል፤
ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በቅዳሜው ጨዋታ የሚገናኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ 39 ነጥብን
ይዞና በደረጃው ሰንጠረዥ አናት ላይ ተቀምጦ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 35 ነጥብን
ይዞና በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ በመሆኑ የጨዋታው አጓጊነቱ በሁሉም ዘንድ ሆኗል፤
የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ አስመልክቶ የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች
ውስጥ አዳነ ግርማ እና አቡበከር ሳኒን ከኢትዮጵያ ቡና ተጨዋቾች መካከል ደግሞ መስዑድ
መሐመድንና እያሱ ታምሩን በማናገር የሚከተለውን ምላሽ ሊሰጡን ችለዋል፤ ተከታተሉት፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ vs ኢትዮጵያ ቡና
ሀትሪክ፡- በሀገራችን ትልቁ የደርቢ ጨዋታ
እስካሁን ስንት ግጥሚያን አድርገሃል?
- ማሰታውቂያ -
አዳነ፡- የቅ/ጊዮርጊስ ክለብን
የተቀላቀልኩት ከ2000 ዓ.ም አንስቶ ስለሆነ
እስካሁን በቁጥር የማላውቃቸውን ብዙ
ግጥሚያዎች ነው ያደረግኩት፡፡
መስዑድ፡- ኢትዮጵያ ቡናን
ከተቀላቀልኩበት ጊዜ ጀምሮ አሁን ቁጥሩን
ለማስታወስ ቢቸግረኝም በበርካታዎቹ
የሸገር ደርቢ ጨዋታዎች ላይ ለመሳተፍ
ችያለሁ፤ ያልተጫወትኩበት ግጥሚያም
ቢኖር ሁለት ነው፤ ይኸው አሁን ለሌላ
ተጨማሪ ፍልሚያምነው ነው እየተዘጋጀው
የሚገኘው፡፡
አቡበከር፡- በፕሪምየር ሊጉ ደረጃ ከሆነ
አንድ ጊዜ ነው የተጫወትኩት፤ እሱንም
በዘንድሮው የመጀመሪያው ዙር ላይ
ነው፤ የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕን ከጨመረ
ደግሞ በአጠቃላይ ለሶስት ጊዜያት ያህል
ግጥሚያዎችን አድርጌያለሁ፡፡
እያሱ፡- ከቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ጋር
ያደረግኩት የደርቢ ጨዋታ አሁን ላይ
አራት ደርሷል፤ 3ቱ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ
ሲሆን አንዱ በሲቲ ካፕ ነው፤ አሁን ደግሞ
ለአምስተኛ ጊዜ ከእነሱ ጋር ለመፋለም
ተዘጋጅቻለው፡፡
ሀትሪክ፡- የደርቢ ጨዋታው ከሌሎች
ግጥሚያዎች አንፃር ያስጨንቀሃል?
አዳነ፡-የደርቢ ጨዋታን ሳደርግ ፈፅሞ
እኔን የሚያስጨንቀኝ አንዳችም ነገር
የለም፤ ኳስን የምጫወተውም ራሴን
ለመጥቀም እና ደጋፊዎቻችንንም በውጤት
ለማስደስት ነው፤ በተለይ ደግሞ ቡናን
ስንረታው የደስታዬ መጠንም ከፍ ስለሚል
በጨዋታው ተደስቼበት ነው የምወጣው፡
፡ እና አሁንም በእዚያ መልኩ ነው
ግጥሚያዎችን ሳልጨነቅበት ከሜዳ ስወጣ
የምታየው፡፡
መስዑድ፡- የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ
ጋር የሚኖረን የደርቢ ጨዋታ እኔን
ፈፅሞ አያስጨንቀኝም፤ ብዙ ጊዜ
ጭንቀቱ የሚኖረውም የሁለቱ ክለብ
ደጋፊዎች ላይ ነው፡፡
አቡበከር፡- በፍፁም፤ ለእኔ እንደውም
ግጥሚያውን ሳደርግ በጣምም ነው ደስ
የሚለኝ፤ እንዲህ ያለ ጨዋታዎችንም
ነው በጣምም ማድረግ የምፈልገው፤
በተለይ ደግሞ በደርቢው ጨዋታ ወቅት
በርካታ የአገራችንም የስፖርት ቤተሰብ
ግጥሚያውን ለመመልከት ወደ ሜዳ
የሚመጣበት ሁኔታ ስላለ እና እኔም በእዚያ
ጨዋታ ላይ ራሴን በጥሩ ሁኔታ አዘጋጅቼ
ክለቤን መጥቀም የምችልበት ፍላጎት ስላለኝ
ጨዋታው ምንም እንደማያስጨንቀኝ ነው
ልንገርህ የምፈልገው፡፡
እያሱ፡- የደርቢውን ጨዋታ ስታደርግ
የስቴድየሙ የድባብ መንፈሰ የሚያምር
ስለሆነ ከጭንቀቱ ይልቅ ለግጥሚያው
ከፍተኛ ትኩረት እንድታደርግና ትልቅ
ግምትንም እንድትሰጥ ነው የሚያደርግህ፤
ስለዚህም በትላልቅ ክለብ እና በደጋፊዎችህ
ታጅበህ የምታደርገው ጨዋታ ስለሆነ
ግጥሚያው ፈፅሞ አያስጨንቀኝም፡፡
ሀትሪክ፡- አንተ በተሰለፍክባቸው የደርቢ
ጨዋታዎች ተቀናቃኛችሁን ስንት ጊዜ
አሸንፋችኋል?
አዳነ፡- የኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረ
ጨዋታ ተሰልፌ እነሱን ድል ያደረግንባቸው
ግጥሚያዎች ቁጥሩን ባላውቀውም ብዙ
ናቸው፡፡ ሌሎች ድሎችም በቀጣዩ ጊዜም
እንዲኖረኝ ጠንክሬ እሰራለው፡፡
መስዑድ፡- የአትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
የደርቢ ጨዋታ ላይ እኔ ኖሬ ቅ/ጊዮርጊስን
በተፋለምንበት ጨዋታ አሸናፊ የሆነው
ለሶስት እና ለአራት ያህል ጨዋታዎች
ነው፤ ወደፊት ሌሎች ድሎች እንዲኖሩኝም
ከወዲህ እየተመኘው ነው፡፡
አቡበከር፡-እኔ በተሰለፍኩበት ጨዋታ
እስካሁን ኢትዮጵያ ቡናን ለማሸነፍ
አልቻልንም፤ ማሸነፍን ግን እፈልጋለሁኝ፡፡
እያሱ፡- የኢትዮጵያ ቡና ተሰላፊ
ሆኜ በፕሪምየር ሊጉ ደርቢ ጨዋታ ቅ/
ጊዮርጊስን ያሸነፍንበት ግጥሚያ ብዛት
አንድ ነው፤ በቀጣይነት ሌሎች ተጨማሪ
ድሎች እንዲኖሩኝ ምኞቴ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በአንተ ስም የተመዘገበ ስንት
የደርቢ ጎል አለህ?
አዳነ፡- ከቡና ጋር ባደረግነው የደርቢው
የእስከዛሬ የእርስ በርስ ጨዋታ ላይ አምስት
ወይም ስድስት ጎሎችን ነው ያስቆጠርኩት፡፡
መስዑድ፡- አንድ ነው ያስቆጠርኩት፤
እሱም አባይ ይገደባል ቡና ዋንጫ ይበላል
በተባለበት እና እልማችንንም ባሳካንበት
የ2003ቱ የውድድር ዘመን ላይ ነው
ግቧን ያገባኋት፤ ያቺ በቅ/ጊዮርጊስ ላይ
ያስቆጠርኳት ግብም አሁን ድረስ በትዝታዬ
ውስጥም ያለች ነች፡፡
አቡበከር፡- ኢትዮጵያ ቡና ላይ እስካሁን
ግብ አላስቆጠርኩም፤ ግብ ማስቆጠር
እፈልጋለሁ፡፡
እያሱ፡- አንድም ግብ በቅ/ጊዮርጊስ ላይ
ማግባት አልቻልኩም፡፡
ሀትሪክ፡- የደርቢ ጨዋታን በድል ስትወጣ
በውስጥህ ምን አይነት ስሜት ነው የሚፈጠርብህ?
አዳነ፡-የኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚኖረንን
የደርቢ ጨዋታ ሁሌም በድል ስናጠናቅቅ
የደስታዬ መጠን ሁሌም ነው ከፍ
የሚለው፤ የቅዳሜ እለቱም የፋሲካ ዋዜማ
ጨዋታ በደጋፊዎቻችን በኩል በጣም
የሚጠበቅ እና ጨዋታውንም አሸንፈን
እነሱን ማስደስት ስለምንፈልግ ሁሉም
ለግጥሚያው ልዩ ትኩረትም ነው እየሰጠው
ያለው፤ ጨዋታውን ማሸነፍ ስንችል
ደግሞ ደስታችን እጥፍ ደርብርብም ነው
የሚሆነው፡፡
መስዑድ፡-የደርቢ ጨዋታን ስታሸንፍ
የደስታው መጠን እጥፍ ድርብ ይሆንብሃል፤
እኔም እነዚያን ያጣጣምኳቸውን የደስታ
ጊዜያቶች ልዩ ቦታ እስጣቸዋለሁ፡
አቡበከር፡- ደጋፊዎቻችን ተጋጣሚያ
ችንን ቡናን ተቀናቃኝ ነው ብለው
ስለሚያስቡ እና ከአንተም ብዙ ነገርንም
ስለሚጠብቁ ጨዋታውን ስታሸንፍ በጣም
ነው ደስ የሚላቸው እና የእነሱም ደስታ
ለአንተም ልዩ ደስታን ይፈጥርልሃል፤
እንደቅ/ጊየርጊስ ተጨዋችነቴ ለእኔ እስካሁን
ይህ የማሸነፍ እድሉ ባይገጥመኝም ይህን
ጨዋታ ቅዳሜ ማሸነፍ ከቻልን የተለየ
የደስታ ስሜት ነው የሚፈጠርብኝ፡፡
እያሱ፡- የደርቢ ጨዋታን የድል ውጤት
ደጋፊው ከሌላው ጊዜ ጨዋታዎች በተሻለ
ሁኔታ ስለሚጠብቀው እና የተቀናቃኝህን
ቡድንም አሸንፈህ እንድትወጣም
ስለሚፈልጉ ያኔ ድሉ ሲገጥምህ ሁሉም
ነገር በጣም ነው ደስ የሚልህ፤ እና እኔም
ቅዱስ ጊዮርጊስን በረታንባቸው ጨዋታዎች
ደስታዬ ልዩ ነው የነበረው፡፡
ሀትሪክ፡- ከደርቢ ጨዋታ በፊት ያለውን
ለሊት እንዴት ነው የምታሳልፈው?
አዳነ፡- ለቅ/ጊዮርጊስም ሆነ ለኢትዮጵያ
ብሄራዊ ቡድን በበርካታ የኢንተርናሽናል
ግጥሚያዎች ላይ ተሰልፌ የተጫወትኩኝ
በመሆኑ ከደርቢው ግጥሚያ በፊት ሌሊቱን
የማሳልፈው ጥሩ እንቅልፍን በመተኛት
ነው፤ ገና ጀማሪ ተጨዋች እያለሁም
ጭምር እንዲህ ያሉ ጨዋታዎች ለእኔ
ምንም ነገርም አይመስሉኝም፡፡
መስዑድ፡- የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ
ጋር በሚኖረን የደርቢ ጨዋታ አሁን
የተካበተ ልምድ ኖሮኝ አይደለም ጀማሪ
በነበርኩባቸውም ጊዜያቶች ያለውን ለሊት
በምንም ነገር ሳልረብሽ ነው የማሳልፈው፤
ያን እለት ካምፕ ውስጥም ነው ጥሩ
እንቅልፍም በመተኛትም ካሳለፍኩ በኋላ
የነጋታውን ጨዋታ በጥሩ አዕምሮ ላይ
ሆኜ የማደርገው፡፡
አቡበከር፡-እንደሌላው ጊዜ ነው፤ ተኝቼ
በጣም አርፌና ሳልጨነቅም ነው ለሊቱን
የማሳልፈው፡፡
እያሱ፡- ግጥሚያው ተጠባቂ የደርቢ
ጨዋታ ቢሆንም ለሊቱን ከሌላው ጊዜ
በተለየ ሁኔታ አላሳልፍም፤ ያም ቢሆን ግን
የእዚያን እለት ጨዋታ ድባብ ደስ የሚል
ስለሆነ ጥሩ ዝግጅት ማድረግ እንዳለብኝ
ግን መቼም ቢሆን አልረሳውም፡፡
ሀትሪክ፡- በሁለታችሁ መካከል የሚደረገውን
የሜዳ ላይ ጨዋታ ብዙዎች ደርቢ የሚለውን
ስሜት አይመጥነውም ይላሉ፤ በዚህ ምን
ትላለህ?
አዳነ፡- የቅ/ጊዮርጊስ እና ቡና
የሚያደርጉት ጨዋታ ላይ የሁለታችንም
ክለብ ተጨዋቾች ደጋፊዎቻችንን በውጤት
ማስደሰትን ስለምንፈልግ እንደሌላው ጊዜ
ኳሱን ዘና /ሪላክስ/ አድርገን ስለማንጫወት
እና ማሸነፍን ብቻ ስለምናስብ ያለው
ጭንቀት ግጥሚያውን ሳይመጥነው ቀርቶ
ይሆናል፡፡
መስዑድ፡- የደርቢ ጨዋታዎች
እንደተጠበቁ እና አንዳንዴም ግጥሚያዎቹ
በሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን ለማየት
ለሚመጡ ደጋፊዎች ሳይመጥኑ
የሚጠናቀቁት በእኛ አገር ላይ ብቻ
ሳይሆን በውጪውም አለም ላይ ነው፤ ያን
እለት ግጥሚያውን አንዱ ቡድን አንዱን
ብቻ እንዲያሸንፍ ብቻ ስለሚፈለግ እና
ጨዋታውም በጥንቃቄ ስለሚደረግ እንዲህ
ያለ ነገሮች በእግር ኳሱ የሚያጋጥሙ
ነገሮች ናቸው፡፡
አቡበከር፡- የሁለታችን የደርቢ ጨዋታ
ከውጪ ሲታይና ውስጥ ላለነው ተጨዋቾች
ስንመለከተው የተለያዩ ሃሳቦች ሊሰጥበት
ይችል ይሆናል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች አንድ
በአንዱ መሸነፍን ስለማይፈልጉ እና ጥንቃቄ
በማድረግም ስለሚጫወቱ ጨዋታው
ላያምር ይችል ይሆናል፡፡ እኛ ግን እልህ
አስጨራሽ ትግል ነው የምናደርገው እና
ስለጨዋታው ውጭ ያየው ሰው ምላሽ
ቢሰጥበት ይበልጥ ጥሩ ነው እላለው፡፡
እያሱ፡- ኢትዮጵያ ቡናና ቅ/
ጊዮርጊስ በሚያደርጉት ጨዋታ ክለቦቹ
የአንድ ከተማ ትላልቅ እና ተቀናቃኝ
እንደዙሁም ደግሞ በብዙ ደጋፊዎቻቸው
የሚደገፉ ስለሆኑ ከጨዋታው የግድ ሶስት
ነጥብን ለማግኘት በጥንቃቄ ስለሚጫወቱ
ግጥሚያው ላያምር ይችል ይሆናል፤ አንዱ
ቡድን ግብ አግብቶ ውጤቱን ለማስጠበቅ
ዘግቶ የሚጫወትበትም እንቅስቃሴ ስላለ
ጨዋታው አንድአንድ ጨዋታዎች ላይ
ሊቀዘቅዝ ይችላል፡፡
ሀትሪክ፡- የፋሲካ ዋዜማ ላይ የደርቢው
ጨዋታ መደረጉ ይህን ትችት የሚያስቀይርና
ጥሩም የሜዳ ላይ እርቅ ይሆናል ብለህ
ታስባለህ?
አዳነ፡-የፋሲካ ዋዜማ ላይ እኛና ቡና
የምናደርገው የደርቢ ጨዋታ ከሌላው
ጊዜ አኳያ ግጥሚያው በአቻነቱ ወደር
የማይገኝለት እና ምርጥም ፉክክር
የሚሆንበት ጨዋታ ይሆናል ብዬ
አስባለሁ፡፡ ለእዚህም ጨዋታ ውበት
ማማር የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎችም
በተለይ የእኛዎቹ የሚያምር ድጋፋቸውን
ዘንድሮ ወደ ሜዳ በመጉረፍ ላይ ስለሆኑም
ጨዋታው ምርጥ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡
፡ ከቡና ጋር በሚኖረን ጨዋታ እስካሁን
የእኛ ቡድን ከሊጉ ሌሎች ቡድኖች አኳያ
እነሱ እያረፉ በመምጣት ሲጫወቱ እኛ ግን
እስካሁንም እረፍት ሳናደርግ እና ከመዳከም
አንፃርም የአቅም ማነስም ገጥሞን ነጥብ
የጣልንባቸው ጨዋታዎችም ያሉ ቢሆንም
በቡናው የፋሲካ እለት ዋዜማ ጨዋታ
ደጋፊዎቻችን እንዲከፉብን ስለማንፈልግ
የፋሲካ እለት ቡናን አሸንፈን በአሉን
ሁለተኛ ፋሲካ ለማድረግ እንፈልጋለን፡፡
መስዑድ፡- የፋሲካ ዋዜማ ላይ
የሚደረገው የሁለታችን የደርቢ ጨዋታ
ጥሩ የመሸናነፍ መንፈስ እና ተመልካቹም
በኳስ የሚዝናናበት ፉክክር ይሆናል ብዬ
አስባለሁኝ፤ ያን እለት ጨዋታውን ማድረግ
መቻሉም ለበአሉም ልዩ ድምቀትም ነው
የሚሆነው፡፡
አቡበከር፡- የእግር ኳስ ጨዋታ
ሰላማዊና ፍቅር የተሞላበትም ስፖርታዊ
ውድድር ነው፤ የደርቢው ጨዋታ
በእምነቱ ተከታዮች የፋሲካ ዋዜማ ቀን ላይ
መካሄዱም ባህሉን የተለየም ያደርገዋል
ብዬም አስባለሁ፤ ያን እለት ሁሉም
ማሸነፍንና መሸነፍንም በፀጋ በመቀበል
ባህሉን በደስታ እንዲያሳልፍም እፈልጋለሁ
እና በሁለታችን መካከል ደጋፊውን የሚክስ
ጨዋታ እናሳያለን ብዬም ነው እምነቴን
የምጥለው፡፡
እያሱ፡- የቅ/ጊዮርጊስና የአትዮጵያ
ቡና ደርቢ ጨዋታ የፋሲካ በአል ዋዜማ
ላይ መደረግ መቻሉ ጨዋታውን በርካታ
ደጋፊዎች እንዲከታተሉት ያስችላቸዋል፤
በዕለቱ ምርጥ ፉክክርም ያደርግበታል ብዬም
አምናለሁ፡፡ ተመልካቹ በአሉን በደስተኝነት
እና በኳስም ተዝናንቶ ይወጣበታልም ብዬ
አስባለሁና ያንን በጉጉት እየጠበቅኩኝ ነው
የምገኘው፡፡
ሀትሪክ፡- በደርቢው ጨዋታ ሁሌም
የሚያስቸግርህ እና የምትፈራው ተጨዋች አለ?
አዳነ፡- በደርቢ ጨዋታው እኔ
የትኛውንም ተጨዋች ፈርቼ አላውቅም፡፡
መስዑድ፡- ሳላህዲን ሰይድ ጠንካራና
ከባድ አጥቂ ስለሆነ እሱን ልንጠነቀቅ ነው
የሚገባን፡፡
አቡበከር፡- ማንም የለም፤
እያሱ፡- እኔም ጋር ስትመጣ የምፈራው
ተጨዋች የለም፤ ለሁሉም ተጨዋቾች ግን
እኩል ግምትና ክብርን እሰጣለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- በእዚህ መሰል የደርቢ ጨዋታ ላይ
የተመልካች ረብሻና አስፀያፊ ቃላትም ሲወረወር
ይደመጣል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
አዳነ፡-የኢትዮጵያ ቡናና የእኛ የደርቢ
ጨዋታ ላይ ከእዚህ በፊት በሜዳ ላይ
ለሚፈጠሩት ረብሻዎችና ላላስፈላጊም
የቃላት ምልልሶች የስፖርታዊ ጨዋነቱ
እንዲደፈርስ የምናደርገው እኛ ተጨዋቾች
ነንና ከድርጊታችን ልንቆጠብ ይገባል፤
የደርቢ ፍልሚያን ለመመልከትና እኛን
ለማበረታታት በርካታ ተመልካች መጥቶ
ነው የሚያየን፤ የሁለታችንም ተጨዋቾች
ደጋፊዎችን ከእዚህ በፊት ስናስቀይም
አልፈናል፤ አሁን እነሱን ልናከብር ይገባል፤
የረብሻ መንስሄ የሚሆኑ ተጨዋቾቻችንንም
እኛ የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች በመገሰፅ
ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ልናደርግ
ይገባል፤ የአገራችን የእግር ኳስ አፍቃሪ
ኳሱ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ይፈልጋል፤
ስለዚህም የፋሲካ ዋዜማ ላይ በሚኖረን
ጨዋታ ተመልካች ተፈንክቶ የማናይበት
የስፖርታዊ ጨዋነት የሚሰፍንበት ማሸነፍን
እና መሸነፍን አሜን ብለን በመቀበል ከሜዳ
ልንወጣ የምንችልበትን ስራዎች በመስራት
በዓሉን በደስታ እንድናሳልፈው ነው
የምመኘው፡፡
መስዑድ፡- የደርቢ ጨዋታው ላይ
የሚፈጠሩት ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ
ድርጊቶች ለማናችንም ስለማይበጅ ብዙ
ነገሮችን ልናሻሽል ይገባል፤ በእዚህ አመት
እየታየ ያለው ለውጥ ጥሩ ነው ይሄ ሊቀጥል ይገባል፡፡
አቡበከር፡- የሁለታችንም ክለብ
ደጋፊዎች የእዚህ የደርቢ ጨዋታ ላይ
ሁሌም እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ
ቡድናቸው ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው
ቢያበረታቱ ጥሩ ነገር ነው፤ አሁን ዘንድሮ
እየታየ ያለው ነገርም የሚበረታታ ነውና
በእዚሁ ነው ሊቀጥሉ የሚገባው፡፡
እያሱ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ
ቡናን የደርቢ ጨዋታ ለመመልከት ሁሌም
ወደ ስቴድየሙ በርካታ ተመልካች ሲመጣ
አስተውለናል፤ መጥቶም እርስ በእርስ
በሚኖሩት ያለመግባባቶች የስፖርታዊ
ጨዋነት ጥሰቶችን አይቶ ይመለሳል፡፡ ይህ
መፈጠር መቻሉ ለማናችንም አይበጅም፤
ስለዚህም የእኛም የቅዱስ ጊዮርጊስ
ደጋፊዎችም የቡና ደጋፊዎችም በእዚህ
የደርቢ ጨዋታ ላይ ቡድኖቻቸውን ብቻ
ቢያበረታቱና ለድልም እንዲበቃ ቢያደርጉ
መልካም ነውና ይህንን በቅዳሜው ጨዋታ
እጠብቀዋለሁኝ፡፡ በዚህ አመት እየታየ ባለው
የደጋፊዎች ድጋፍም ልደነቅ ችያለው፡፡
ሀትሪክ፡- በደርቢው ጨዋታ ለሚመደቡት
ዳኞች ምን አይነት ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል?
አዳነ፡- የደርቢ ጨዋታዎች ላይ
የሚመደቡ ዳኞች ብዙ ጊዜ ጫና
ይበዛባችኋል፤ ያንን ጫና የሚፈጥሩትም
በውሳኔው አሰጣጥ በኩል ተደጋጋሚ
ስህተትን ስለሚፈጥሩ ስለሆነ ብዙ ጊዜ
ተጠያቂ ይሆናሉ፤ ዳኞቹ ራሳቸውን
በመፈተሽ ችግራቸውን ማቃለል ይችላሉ፡፡
የደርቢው ጨዋታ ላይ አንድ ጥፋት ሲሰራ
ከካፒቴኑ ውጪ ሌሎች ግርግር እንዳይፈጥሩ
ሃላፊነቱን ለካፒቴኑ ብቻ ቢሰጡና ያን
እውን ቢያደርጉ የእውነት እና ትክክለኛ
የሆነንም ፍትሃዊ እና ጥሩ የህግ ውሳኔንም
ቢያስተላለፉ ከጨዋታው የሚጠብቁትን ጥሩ
ነገርን ይዘን ይወጣሉ፤ እኛም እነሱ ሊሳሳቱ
ቢችሉ እንኳን አንድአንዴም ከጎናቸው
ልንሆን የምንችልበትን ነገርም ልናሳያቸው
ይገባልና ስለ እነሱ ማለትን የምፈልገው
ይሄን ነው፡፡
መስዑድ፡- የደርቢ ጨዋታን ለመምራት
ለሚችል ዳኛ መጀመሪያ ውሳኔዎችን
የሚወስነው በቅፅበት ስለሆነ አንድአንዴ
እኛም እንደአመጣጡ ልንቀበለው ያገባል፤
ጨዋታውን ግን በጥሩ ሁኔታ ለመወጣት
የውድድሩ አዘጋጅ አካል ብቃት ያለው
እና ብዙ ዓመት ያጫወተ ዳኛን ሊመድብ
ይገባል፤ ይህ ዳኛ ቢሳሳት እንኳን ጥፋቱን
ለማስተካከል ቶሎ ይችላልና እኛም
ተጨዋቾች በደርቢው ጨዋታ ወቅት
እነሱ ሊሳሳቱ ቢችሉ እንኳን አንድአንዴ
ከጎናቸውም ሆነን ልንጠብቃቸው ይገባናል፡፡
አቡበከር፡- በኢትዮጵያ ቡና እና በቅ/
ጊዮርጊስ ክለቦች መካከል በሚደረገው የደርቢ
ጨዋታ ላይ ሁልጊዜም ዳኞች ግጥሚያው
ተጠባቂና ጫና ያለው ከመሆኑ አኳያ
ጨዋታውን አቻችለው ለመውጣት እና
ለመጨረስ ነው የሚፈልጉት፤ ሲያቻችሉ
ስህተትን ይፈፅማሉ፤ እኛ ስለእነሱ ውሳኔ
ብዙ መፍረድ ባንችልም እነዚህ ዳኞች
ያመኑበትን ውሳኔ ቢያስተላልፉ ለእግር
ኳሱ ይበልጥ መልካም ነው የሚሆነው፡፡
እያሱ፡- የደርቢ ጨዋታዋች ላይ
ብዙ ጊዜ ዳኞች ሲቸገሩ የሚታዩት
እንደአብዛኛዎቹ ሌሎች ግጥሚያዎቻቸው
ሁሉ በእዚህም ጨዋታ ላይ የራሳቸውንና
የሚያምኑበትን ውሳኔ ከመወሰን ይልቅ
የውጪውን ማለትም ከተመልካች አካባቢ
የሚመጣውን ነገር ስለሚያዳምጡ ነው፤
የሁለታችን የደርቢ ጨዋታ ላይ ብዙ ጊዜ
በርካታ ደጋፊዎች ወደሜዳ ስለሚመጡ
ዳኞች ጆሮአቸውን ለእነሱ ይሰጡና በውሳኔ
አሰጣጥ ላይ ብስጩ ሆነው ስለሚዳኙ
ይሳሳታሉ፤ ከተሳሳቱም በኋላ ለማካካስም
ይፈልጋሉ፡፡ ጨዋታው አቻ እንዲያልቅም
የሚፈልጉም ዳኞች አሉና ከእንዲህ
ያሉ አሰራሮች በመውጣት ያመኑበትን
የራሳቸውን ውሳኔ ቢያስተላልፉ ብዙ
ነገሮችን ሊያቃልሉ ይችላሉና ከግጥሚያው
በፊት በእነዚህ ነገሮች ላይ ተዘጋጅተው
ሊመጡ ነው የሚገባው፡፡
ሀትሪክ፡- በደርቢው ጨዋታ ጎል
የምታስቆጥር ይመስልሃል?
አዳነ፡- የቡድናችን ደጋፊዎች ሁሌም
ከእኔ ጎል ስለሚጠብቁ አዎን ቡና ላይ ጎል
አገባለሁ፡፡
መስዑድ፡- እኔም ጎል አገባለሁ ነው
የምለው፡፡
አቡበከር፡- የመሰለፍ እድሉን ያን እለት
በእርግጠኝነት ካገኘው ጎል አስቆጥራለሁ፡፡
እያሱ፡- አዎን፤ ግብ የማስቆጠር
ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- የደርቢ ጨዋታውን ማን
በበላይነት ያጠናቅቃል ብለህ ታስባለህ?
አዳነ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ደርቢውን
በስኬት ያጠናቅቃል፡፡
መስዑድ፡- ግጥሚያውን ማሸነፋችን
የማያጠራጥር ነውና ድሉን ቅዳሜ ዕለት
ጠብቁ፡፡
አቡበከር፡- እኛ ነን ሃ! ቅዱስ ጊዮርጊስ
ቡናን በእርግጠኝነት አሸንፎት ይወጣል፡፡
እያሱ፡- እንደ አንደኛው ዙር ሁሉ
አሁንም የአሸናፊነቱን ውጤት ይዘን
የምንወጣው እኛ ኢትዮጵያ ቡናዎቹ ነን፡፡
ሀትሪክ፡- ውጤቱን ገምት?
አዳነ፡- 2ለ0
መስዑድ፡- በእዚህ ውጤት ይጠናቀቃል
በሚል ቁጥር መገመት ባይሆንልኝም
ቡድናችን የጨዋታው አሸናፊ ይሆናል፡
አቡበከር፡- 2ለ0 ነው የሚያልቀው፡፡
እያሱ፡- ኢትዮጵያ ቡና 2-0 ቅ/ጊዮርጊስ