በመሸሻ ወልዴ
ቅ.ጊዮርጊስ በዛቦ ቴጉይ እና
በሳላህዲን ሰይድ ሁለት ግቦች
ሰበታ ከተማን 2ለ1 በማሸነፍ ለ14ኛ ጊዜ
የተዘጋጀውን የአዲስ አበባ ከተማ ሲቲ
ካፕ ዋንጫን ለ6ኛ ጊዜ አንስቷል፡፡ የቅዱስ
ጊዮርጊስ ክለብ ሰበታ ከተማን በተፋለመበት
የፍፃሜው ቀን ጨዋታ እስከመጨረሻው
ሰዓት ድረስ የግጥሚያው ባለድል ለመሆን
በሁሉም ተጨዋቾች ላይ ከፍተኛ እና
ጠንካራ የሆነም የአሸናፊነት መንፈስ ይታይ
የነበረ ሲሆን በጨዋታውም በተለይ ደግሞ
በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት
ከደደቢት ክለብ በመምጣት ፊርማውን
ያኖረው የአብስራ ተስፋዬ ጥሩ ብቃቱን
ያሳየበት ጨዋታ በመሆኑም በመጨረሻም
የግጥሚያው የኮከብ ተጨዋችነትን የ10 ሺ
ብር ሽልማት የውድድሩ ስፖንሰር ከሆነው
አሞሌ ሊበረከትለት ችሏል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ሰበታ ከተማን
አሸንፎ ባለድል ለሆነ በኋላ ስለቡድናቸው
ሻምፒዮናነትና ሌሎችን ጉዳዮች አንስተን
የጨዋታው ኮከብ የተባለውን የአብስራ
ተስፋዬን ያናገርነው ሲሆን ተጨዋቹም
ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፡፡
ሀትሪክ፡- ቅ.ጊዮርጊስ ሰበታ ከተማን
በማሸነፍ የሲቲ ካፑን ዋንጫ ለ6ኛ ጊዜ
አንስቷል፤ በድሉ ምን ተሰማህ? ከእነሱ
ጋር ባደረጋችሁት ጨዋታስ የአሸናፊነቱ
ውጤት ለእናንተ ይገባል?
የአብስራ፡- አዎን፤ የሰበታ ከተማ
እግር ኳስ ክለብን ድል ያደረግንበት
የአዲስ አበባ ከተማ የሲቲ ካፕ ፍፃሜ
ጨዋታ ለእኛ በውጤትም ሆነ በጨዋታ
በኩል ጥሩ የነበረልን በመሆኑ የግጥሚያው
አሸናፊ መሆናችን ሲያንሰን እንጂ የሚበዛብን
አይደለም፤ በአጠቃላይ ውድድሩ ከመጀመሪያ
ቀናት አንስቶ ሻምፒዮና እንሆናለን ብለን
ለደጋፊዎቻችን ቃል ገብተን ስለነበር ያን ነው
ለማሳካት የቻልነው፤ ሰበታን በፍፃሜው ቀን
ስናሸንፍ እኛ ጥሩ ነበርን፤ ይህን ጥሩነትም
ልናገኝ የቻልነው ከጨዋታ ወደ ጨዋታ
እየተሻሻልን ስለሄድንና ድክመቶቻችንንም
ስላረምን ነውና ቡድናችን የእዚህ ውድድር
ሻምፒዮና ሆኖ በማጠናቀቁ በጣም ደስ
ብሎናል፤ ደጋፊዎቻችንም ከሰጡን ምርጥ
ድጋፍ አንፃር ይሄ ድል ለእነሱም ጭምር
ይገባቸዋል፡፡
ሀትሪክ፡- ቅ.ጊዮርጊስ የሲቲ ካፑን
ዋንጫ ለ6ኛ ጊዜ እንዲያነሳ ዋንኛ
ጥንካሬው የነበረው ምንድን ነው?
የአብስራ፡- ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሲቲ
ካፑ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ሻምፒዮና
ልንሆን የቻልነው በእያንዳንዱ ግጥሚያዎቻችን
ላይ ሜዳ ስንገባ ያለን ህብረት እና አንድነት
ጥሩ ስለሆነ ነው፤ በጨዋታ እንቅስቃሴው
ላይ ሁላችንም ጨዋታዎችን ለማሸነፍ
ምን ምን ማድረግ እንዳለብን እንነጋገር
ነበር፤ የሚሳሳት ሰው ካለም ያንን ስህተቱን
በፍጥነት እንዲያስተካክልም የምንመካከርበት
ነገር ስለነበር ያ ቡድናችንን ሲጠቅመው ነበር፤
ከዛ ውጪም ደጋፊዎቻችንም በመከላከያው
ጨዋታ ሽንፈትን ካስተናገድንበት ጨዋታ
አንስቶም ከእኛ ጎን ስለነበሩና ጥሩ ድጋፍም
ይሰጡን ስለነበር ይሄ ጭምርም ነው
ለሲቲ ካፑ ባለድልነት ሊያበቃን የቻለውና
እነሱንላመሰግናቸው እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከእሁዱ ጨዋታ በመነሳት
የቅ.ጊዮርጊስ የፍፃሜ ተጋጣሚ ስለነበረው
ሰበታ ከተማስ ምን ትላለህ?
የአብስራ፡- የሰበታ ከተማ እግር
ኳስ ክለብን በተመለከተ በፍፃሜው ቀን
ጨዋታ ላይ ምንም እንኳን በእኛ ሽንፈትን
አስተናግደው ከሜዳ ይውጡ እንጂ ጥሩና
ትልቅ ቡድን ነበሩ፤ ከዛ ውጪም የሀገሪቷን
ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ተጨዋቾችም
በስኳዱ ውስጥ አካተው የያዙበት አጋጣሚም
ስለነበር በጨዋታው ከእነሱ በተሻለ መልኩ
ልንንቀሳቀስ ብንችልም እነሱም የዋዛ
አልነበሩም፡፡
ሀትሪክ፡- የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ
ዋንጫን አነሳችሁ፤ ይሄ ለእናንተ ምን
ትርጉም አለው ?
የአብስራ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ የሲቲ
ካፑን ዋንጫ አሁን ላይ ገና ከጅማሬው
ለማንሳት መቻሉ በፕሪምየር ሊጉ ላይ
ለሚኖረው ውድድር ትልቅ መነቃቃትን
ይፈጥርለታልና ይሄ ውጤት ለእኛ ትልቅ
ትርጉም ነው ያለው፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአሁን
ሰዓት ከግጥሚያ ወደ ግጥሚያ እየተሻሻለ ያለ
ቡድን ነው፤ ለዛም ነው መሻሻል ስላሳየ የሲቲ
ካፕ ዋንጫን ሊያገኝ የቻለውና ከእዚ ድል
በመነሳት ቡድናችን ዘንድሮ በሚያደርጋቸው
ሌሎች በርካታ ውድድሮችም የሀገሪቱን
ትላልቅ የድል ዋንጫዎች ለማግኘትም
ዝግጁ እንደሆነ በእዚሁ አጋጣሚ ለመናገር
እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰበታ
ከተማን በአሸነፈበት የፍፃሜው ጨዋታ
የግጥሚያው ኮከብ ተጨዋች ተብለህ
ተሸልመሃል፤ በእዚህ ምን አይነት ስሜት
ተፈጠረብህ ?
የአብስራ፡- ከሰበታ ከተማ ጋር
ባደረግነው የፍፃሜ ጨዋታ ከእኔ የጨዋታው
ከከብ ተጨዋችነት ይልቅ ቅድሚያ ያስደሰተኝ
የቡድኔ ሻምፒዮና ለመሆን መቻል ነው፤
ቀጥሎ ደግሞ ገና ከጅማሬዬ ለቡድኔ ጥሩ
ለመንቀሳቀስ በመሞከር ግጥሚያው ኮከብ
ተጨዋች ተብዬ መሸለሜ ለእኔ ቡድኑን
ወደፊት በጥሩ መልኩ እንዳገለግልና ወሳኝ
ተጨዋችም እንድሆን ስለሚረዳኝ በእዚህ
ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…. ?
የአብስራ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስም ሆኑ
የሌሎች ክለብ ደጋፊዎች በአዲስ አበባ
ከተማ ዋንጫ ላይ ለየክለቦቻቸው የሰጡት
ድጋፍ የስፖርታዊ ጨዋነትን የተላበሰ
ስለነበር በእዚህ ሁላችንም ልንደሰት እና
ከተማችንንም ልናስከብራት ችለናል፤ ይሄ
ድጋፍ ወደ ፕሪምየር ሊጉም ላይ ተሸጋግሮ
ዘንድሮ ሰላማዊ ውድድርን እንድንመራ
ፈጣሪ ይርዳን፡፡