በ2009 ዓ.ም መካሄድ እያለበት በተለያየ ምክንያት ሲንጓተት ወደ 2010 የተዘዋወረው የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የ2009 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ቅ/ጊዮርጊስን ከ2009 የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ አሸናፊ ወላይታ ዲቻ ጋር አገናኝቶ ቅ/ጊዮርጊስ በአሉላ ግርማና አቡበከር ሳኒ 2ግቦች አሸናፊ መሆን ችሏል።
እንደተለመደው ሁሉ በድንቅ የደጋፊዎች ዝማሬና ጭፈራ ታጅቦ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እስከ 24ኛው ደቂቃ ድረስ የረባ የግብ ማግባት ሙከራና ጎል ሳይስተናገድበት ቆይቷል።
አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የመሀል ሜዳ ላይ ሽኩቻ በተስተዋለበት በዚህ ጨዋታ ቅ/ጊዮርጊስ ኳስ ተቆጣጥሮ ወደጎል ለመድረስ ሲሞክረሸ ወላይታ ዲቻ በአንፃሩ ወደ ኀላ አፈግፍጎ በመልሶ ማጥቃትለመጫወት ሲሞክር ተስተውሏል። 24ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ዲቻው ጃኮ አረፋት ከሳጥን ውጪ የመታን ኳስ የቅ/ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ በቀላሉ ይዞታል። ከ 3ደቂቃዎች በኀላ የወላይታ ዲቻው ፀጋዬ ብርሀኑ ከቅጣት ያሻገረለትን ኳሰ ተክሉ ተስፋዬ በግንባሩ ገጭቶት ወደውጭ ወጥቷል። 32ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አሜ መሀመድ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ አሻምቶት አሉላ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ ገጭቶ ጎል ማድረግ ችሏል።
ከ 3ደቂቃዎች በኀላ የወላይታ ዲቻው ግብ ጠባቂ ኢማኑኤል ፌቮ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ አቡበከር ሳኒ ጎል ማስቆጠር ችሏል። የመጀመሪያው ግማሽ ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃ ሲቀረው አቡበከር ሳኒ ከግቡ ቀኝ በኩል ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞታል።
ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ኳስን ተቆጣጥሮ ወደ ወላይታ ዲቻ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረገው ቅ/ጊዮርጊስ ሙሉ የጨዋታ ጊዜውን የበላይነት ወስዷል። 57ኛው ደቂቃ ላይ ወላይታ ዲቻ ያገኙትን ቅጣት ምት አብዱልሰመድ አሊ አሻግሮት ፀጋዬ ብርሀኑ በግንባሩ ገጭቶት በግቡ አናት ላይ ወጥቷል። 63ኛው ደቂቃ ላይ የደጉ ደበበን ስህተት ተከትሎ ጃኮ አረፋት ከበረኛው ጋር 1 ለ 1 ተገናኝቶ የሞከረው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥቷል። ወላይታ ዲቻ ካገኛቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የሚያስቆጭ ነበር። 76ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ ኢብራሂም ፎፋና በድንቅ ሁነሰታ ያሻገረለትን ኳስ አሜ መሀመድ ሞክሮት በረኛው በግሩም ሁኔታ ይዞበታል። 80ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ዲቻው ሙባረክ ሽኩሪ የመታውን ቅጣት ምት የቅ/ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ በቀላሉ ይዞታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 6ደቂቃ ሲቀረው አበባው ቡጣቆ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው ሙሉዓለም መስፍን በግሩም ሁኔታ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ግብ ጠባቂው ይዞታል።
በመጨረሻም ቅ/ጊዮርጊስ የ2009 የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ አሸናፊ በመሆኑ የተዘጋጀለትን ዋንጫ ከእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ጁነዲን ባሻ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት እጅ ተቀብሏል።