ጨዋታ : ሀዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ
የጨዋታ ቀን: ረቡዕ ታህሳስ 29/2012
የጨዋታ ሰዐት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ፌደ አርቢትር ቢንያም ወርቅአገኘው
ቦታ: ሀዋሳ ኢ/ስታድዮም
ካሳለፍናቸው ሁለት አመታት የሜዳ ላይ ረብሻዎች እና የስፓርታዊ ጨዋነት ችግሮች ስንክሳር የፀዳ የሚመስለው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ተኛ ሳምንቱ ላይ ደርሷል።
በዚህ በበዐል ሰሞን መርሀግብር በነገው እለት (ረቡዕ) በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድዮም በሁለት ጨዋታ ሰባት ግብ ከዘነበባቸው በኋላ በስድስተኛ ሳምንት መርሀ ግብር ወደ መቐለ ተጉዘው ያለ ምንምን ግብ አቻ በውጣት አንድ ነጥብ ይዘው የተመለሱት እና በ8 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች እና ባሳለፍነው ሳምንት የአምናውን ቻምፕዮን መቐለ 70 እንደርታን በሰልሀዲን ሰዒድ እና በአቤል ያለው ግቦች 2-1 በማሸነፍ በሊጉ በ9 ነጥብ 6ተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚገናኙ ይሆናል።
በሊጉ ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት የተሳነው ሀዋሳ ከተማ በስድስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ አሸንፎ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቶ ሁለት ጊዜ ደሞ ሽንፈትን ቀምሷል። በተለይ ደግም በ4ተኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 4 ግብ እና በ5 ተኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና 3 ግብ ማስተናገዱን ተከትሎ የቡድኑ የመከላከል ብቃት ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ይገኛል። ሆኖም ግን የቡድኑ የማጥቃት ስልት በቂ ግብ እያመረተ አለመገኘቱ የቡድኑ ችግር የመከላከል ስልቱ ላይ ብቻ እንዳልሆን የሚያስያ ነው።
- ማሰታውቂያ -
በአንፃሩ 14ተኛ ዋንጫቸውን ካነሱ በኋላ ከሊጉ ዋንጫ ጋር ለሁለት አመታት የተራራቁት ፈረሰኞቹ በያዝነው የውድድር አመት በ ሰርጂዮቪች መሪነት ዋንጫውን ለማንሳት ተስፋ ያደረጉ ይመስላል ሆኖም በእስካሁኑ የስድስት ሳምንታት ጉዞ ብልጭ ድርግም የሚል ውጤት እያሳዩ ይገኛሉ።
በፈረሰኞቹ በኩል የአስቻለው ታመነ እና የፍሪንፓንግ የተከላካይ ስፍራ ጥምረት እና የሙሉአለም (ዴኮ) ለተከላካዮች የሚሰጠው ሽፋን ግብ ማስቆጠር የተራራ ያህል ከከበደው የዘንድሮው የሀዋሳ ከተማ የማጥቃት ስልት ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በሊጉ ልምድ ያላቸውን እና ውጤታማ መሆን የቻሉትን ሁለት አጥቂዎች (ጌታነህ ከበደ እና ሰልሀዲን ሰዒድን) የያዘው የቅዱስ ጊዮርጊስ የአጥቂ ክፍል በተደጋጋሚ መመልከት እንደቻልነው ከአማካኝ ክፍሉ በቂ የሆነ የማግባት እድል እየተፈጠረለት አይደለም አሰልጣኝ ሰርጂዮቪች በነገው እለት ይህንን ችግር ለመቅረፍ ወደ ሜዳ ይዘው ሊገቡት የሚችሉት ስልት ተጠባቂ ቢሆንም መቐለን ከገጠመው ቡድን የተለየ አሰላልፍ እናያለን ተብሎ አይጠበቅም።
ሀዋሳ ከተማዎች ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ማግኘት የሚችሉ ከሆነ ወደ መሪነቱ ጎራ መቀላቀል የሚችሉ ሲሆን ቀን ከከዳቸው እና ሽንፈትን የሚቀምሱ ከሆነ ግን የወራጅ ቀጠናውን ሊቀላቀሉ ይችላል። በአንፃሩ ፈረሰኞቹ ድል የሚቀናቸው ከሆነ ወደ ሊጉ አናት የሚጠጉ ሲሆን ሶስት ነጥቡን አሳልፈው የሚሰጡ ከሆነ ደግሞ ከደረጃቸው የሚያሽቆለቁሉበት ሁኔታ የሚፈጠር ይሆናል።
በነገው ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ በኩል የቸርነት አውሽ መግባት አጠራጣሪ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩልም ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የነበሩት ግብ ጠባቂው ለዓለም ብርሀኑ እና አማካዩ ናትናኤል ዘለቀ የማይኖሩ ሲሆን የአቡበከር ሳኒም መግባት አጠራጣሪ ነው።