የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረጉ ሲሆን ነገ (ቅዳሜ) አንድ እንዲሁም ከነገ በስቲያ (እሁድ) ደግሞ ሰባት ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል። በነገው እለት የሚደረገውን እና ሰበታ ከተማ ከ ጅማ አባጅፋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን እንደሚከተለው ዳሰነዋል። መልካም ንባብ።
ጨዋታ: ሰበታ ከተማ ከ ጅማ አባጅፋር
የጨዋታ ቀን: ቅዳሜ ጥር 02/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ኢንተርናሽናል አርቢትር ሃ/የሱስ ባዘዘው
የጨዋታ ቦታ: አዲስ አበባ ስታዲየም
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን በዚህ ዙርም በውድድር አመቱ በውጤት ረገድ እንደተጠበቀው ጥሩ አቋም እያሳየ የማይገኘው ሰበታ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም (በሜዳው ጥራት ምክንያት በአወዳዳሪ ኮሚቴው ውሳኔ ጨዋታዎችን በአዲስ አበባ ስታዲየም እያደረገ ይገኛል።) መጥፎ ጅማሬን ያደረገው እና በተጫዋቾች ደሞዝ ምክንያት ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የነበረው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ የሚገኘውን ጅማ አባጅፋርን የሚያስተናግድ ይሆናል። በዘንድሮው የውድድር ዘመን ሰበታ ከተማ በሜዳው ያስመዘገበው አንድ ድል ብቻ ሲሆን ጅማ አባጅፋር ደግሞ ከሜዳው ውጪ ምንም ጨዋታ ማሸነፍ አለመቻሉ የነገውን ጨዋታ ማን ያሸንፋል የሚለው አጓጊ ጥያቄ ነው።
- ማሰታውቂያ -
ባለፉት 7 የሊጉ ጨዋታዎች እንደ ተጋጣሚያቸው አቀራረብ የሚለዋወጥ አጨዋወት ይዘው የቀረቡት እና ቀስ በቀስ ወደ አሸናፊነት መንገድ የተመለስሱት ሰበታዎች ከሜዳቸው ውጪ በስሑል ሽረ ሽንፈት ያስተናገዱ ሲሆን በነገው ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ ድል ማስመዝገብ እንደ ዳገት የከበደውን ጅማ አባጅፋርን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በሰበታ ከተማ በኩል መሀል ሜዳ ላይ መስኡድ መሀመድ፣ ዳዊት እስጢፋኖስና ታደለ መንገሻ የሚፈጥሩት ጥምረት ሰበታዎች በጥሩ አጫጭር ቅብብሎሽ ወደ ሜዳው የመጨረሻ ክፍል እንዲደርሱ ቢያስችላቸውም የሜዳው ሶስተኛ ክፍል ላይ ባለባቸው የውሳኔ ችግር የጠሩ የግብ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
ጅማ አባጅፋሮች በዘንድሮው የውድድር አመት በሜዳቸው እንደሚያስመዘግቡት አይነት ውጤት ከሜዳቸው ውጪ ማስመዝገብ የተሳናቸው ሲሆን ለዚህ ደግሞ እንደ ዋነኛ ምክንያት ይነሳ የነበረው በክለቡ እና በተጫዋቾቹ መካከል ተፈጥሮ የነበረው የደሞዝ ክፍያ ውዝግብ ነበር። ሆኖም ግን ይህ ውዝግብ ከሞላ ጎደል የተፈታ ሲሆን ተጫዋቾቹም መነቃቃት ማሳየት ጀምረዋል። ለነገው ጨዋታ በርካታ የጅማ አባጅፋር ደጋፊዎች ወደ አዲስ አበባ እየተጓዙ ሲሆን ዛሬ ማምሻውን ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሰበታ ከተማም በፌስቡክ ገፁ የጅማ አባጅፋር ደጋፊዎች በሰላም እንዲገቡ መልካም ምኞቱን ገልጿል።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሰበታ ከተማ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 4ቱን በሜዳው ያደረገ ሲሆን ከነዚህ 4ጨዋታዎች ወላይታ ድቻን ብቻ ሲያሸንፍ በወልዋሎ አ.ዩ. ተሸንፎ ቀሪዎቹን ጨዋታዎች ከፋሲል ከነማ እና ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ መለያየት ችሏል። በአጠቃላይ በሊጉ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 2ቱን ሲያሸንፍ ሁለት አቻ ወጥቶ በሶስቱ ሽንፈት በማስተናገድ የሊጉ ግርጌ ላይ ከሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና በ3ነጥቦች ብቻ ከፍ ብሎ በ8ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ጅማ አባጅፋር በአንፃሩ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 3ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጪ ሲያደርግ በሶስቱም ጨዋታዎች ከኢትዮጵያ ቡና፣ ከወልዋሎ አ.ዩ. እና ከአዳማ ከተማ ጋር ያለግብ አቻ ተለያይቷል። በአጠቃላይ በሊጉ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች ደግሞ በ2ጨዋታዎች አሸንፎ በ4ጨዋታዎች አቻ ወጥቶ በ1ጨዋታ ተሸንፎ 10 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከመሪው ወልዋሎ አ.ዩ. በ4ነጥቦች ብቻ አንሶ በሊጉ 5ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ነገ በሚካሄደው እና ኢንተርናሽናል አርቢትር ሃ/የሱስ ባዘዘው በሚመሩት ጨዋታ ሰበታ ከተማ የሚያሸንፍ ከሆነ ከጅማ አባጅፋር በላይ መቀመጥ ሲችል በአንፃሩ ጅማ አባጅፋር ድል የሚቀናው ከሆነ ወደ መሪዎቹ የሚጠጋበትን እድል ያሰፋል።
ሰበታዎች በነገው ጨዋታ በረጅም ጊዜ ጉዳት ያለው ተከላካዩ አንተነህ ተስፋዬ እና አስቻለው ግርማን በጉዳት የሚያጡ ሲሆን በጅማ አባጅፋር በኩል ደግሞ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ከጉዳቱ ሲያገግም ሄኖክ ገምቴሳ እና ብሩክ ገብረአብ ግን በነገው ጨዋታ የማይኖሩ ይሆናል።