የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረጉ ሲሆን ዛሬ (ቅዳሜ) አንድ ጨዋታ የተደረገ ሲሆን ነገ (እሁድ) ደግሞ ሰባት ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል። በነገው እለት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ድሬደዋ ከተማ የሚያደርጉትን ጨዋታ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን እንደሚከተለው ዳሰነዋል። መልካም ንባብ።
ጨዋታ: ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ድሬደዋ ከተማ
የጨዋታ ቀን: እሁድ ጥር 03/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ኢንተርናሽናል አርቢትር አማኑኤል ኃ/ስላሴ
የጨዋታ ቦታ: አዲስ አበባ ስታዲየም
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን በዚህ ዙርም በውድድር አመቱ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው ቅዱስ ጊዮርጊስን በውጤት ረገድ በሊጉ ከባድ ጊዜያትን እያሳለፈ የሚገኘውን ድሬደዋ ከተማን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት የሚያስተናግድ ይሆናል። በዘንድሮው የውድድር አመት ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ጥሩ የሚባል ሪከርድ ሲኖረው በ3ጨዋታዎች 1 ግብ ብቻ ነው የተቆጠረበት። ድሬደዋ በአንፃሩ ከሜዳው ውጪ መጥፎ ሪከርድ ነው ማስመዝገብ የቻለው። በ4ጨዋታዎች 12 ግቦች የተቆጠሩበት ሲሆን 4ግቦችን ብቻ ነው ማስቆጠር የቻሉት። ይህንንም ተከትሎ የነገውን ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ የማሸነፍ እድሉ ሰፊ ቢመስልም በየሳምንቱ አዳዲስ ነገር ማሳየት የለመደው ሊጉ የነገውንም ጨዋታ በእርግጠኝነት ለመገመት አዳጋች ያደርገዋል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ቡድኑ ግብ የማግባት ችግር ያለበት ሲሆን ለዚህ እንደመፍትሄ ሊቀርብ የሚችለው የአንጋፋው አጥቂ ሳልሃዲን ሰዒድ ከጉዳት መመለስ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪም ከጉዳት መልስ ከአቤል ያለው እና ከጌታነህ ከበደ ጋር የፈጠረው አስደናቂ ጥምረት በነገው ጨዋታ ለድሬደዋ ተከላካይ ፈተና ይሆንበታል ተብሎ ይጠበቃል። በድሬደዋ በኩል ከሜዳው ውጪ ሲጫወት በርካታ ግብ ማስተናገዱ እንደ ድክመት ይወሰዳል። የድሬደዋ ከተማ የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች ለተከላካይ ክፍሉ እግዛ አለማድረግ እና የተከላካይ ክፍሉ አለመናበብ እና እጅግ ደካማ መሆን ተደምሮበት የድሬደዋ ከተማን የሊግ ጉዞ ቁልቁል እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ደግሞ መሀል ሜዳ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ አይደክሜ ተጫዋቾች ሙሉዓለም መስፍን እና ሀይደር ሸረፋ ብልጫ እንዲወሰድበት እና ተደጋጋሚ ጫና እንዲፈጠርበት ያስገድደዋል። ስለሆነም ቅዱስ ጊዮርጊስ በማሸነፍ ወደ ሊጉ መሪዎች በጣም ለመጠጋት እንዲሁም ድሬደዋ ከተማ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ለመሸሽ ነገ ከባድ ፍልሚያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
- ማሰታውቂያ -
በዘንድሮው የውድድር ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 3ቱን በሜዳው ያደረገ ሲሆን ከነዚህ 3ጨዋታዎች መቐለ 70 አንደርታን እና ሰበታ ከተማን ሲያሸንፍ ከስሑል ሽረ ጋር ያለግብ አቻ መለያየት ችሏል። በአጠቃላይ በሊጉ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 2ቱን ሲያሸንፍ አራት አቻ ወጥቶ በአንድ ጨዋታ ሽንፈት በማስተናገድ የሊጉ አናት ላይ ከሚገኘው ከወልዋሎ አ.ዩ. በ4ነጥቦች ብቻ ዝቅ ብሎ በ10ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ድሬደዋ ከተማ በአንፃሩ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 4ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጪ ሲያደርግ በሶስቱ ጨዋታዎች ተሸንፎ ሲዳማ ቡናን ብቻ ማሸነፍ ችሏል። በአጠቃላይ በሊጉ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች ደግሞ በ2ጨዋታዎች አሸንፎ በ4ጨዋታዎች ተሸንፎ በ1ጨዋታ ብቻ አቻ ወጥቶ 7 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ3ነጥቦች ብቻ አንሶ በሊጉ 14ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ነገ በሚካሄደው እና ኢንተርናሽናል አርቢትር አማኑኤል ኃ/ስላሴ በሚመሩት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያሸንፍ ከሆነ ወደ መሪዎቹ መጠጋት ሲችል በአንፃሩ ድሬደዋ ከተማ ድል የሚቀናው ከሆነ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነጥብ መስተካከል ያስችለዋል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አቡበከር ሳኒ ከጉዳት ያገገመ ሲሆን ናትናኤል ዘለቀ እና ለዓለም ብርሀኑ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል። ድሬዎች በነገው ጨዋታ ምንያህል ተሾመ ፣ አማኑኤል ተሾመ ፣ ሳሙኤል ዘሪሁን እና በረከት ሳሙኤልን በጉዳት አያሰልፉም። ባለፈው ሳምንት ያልተሰለፈው ሳምሶን አሰፋ መኖርም አጠራጣሪ ነው።