የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት የዕለተ ሀሙስ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ
በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት 8 ጨዋታዎች ዛሬ በሚደረግ 1 ጨዋታ ጅማሬአቸውን ያደርጋሉ።
አ/አ ላይ በሚደረገው በዚህ ጨዋታ 11፡00 ሲል ቅ/ጊዮርጊስ ከጅማ አባጅፋር ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።
በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ጅማ አባጅፋር በሊጉ ደካማ ጅማሬ ቢያደርግም በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ድል በማድረግ ነጥቦችን በመሰብሰብ በሊጉ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
- ማሰታውቂያ -
በ9ኛው ሳምንት አ/አ ስታዲየም ላይ ቅ/ጊዮርጊስ መከላከያን ገጥሞ ያለግብ 0-0 ሲለያይ ጅማ አባጅፋር በአንፃሩ በሜዳው ሌላውን አዲስ አዳጊ ወልዋሎ አ.ዩን አስተናግዶ ተመስገን ገብረኪዳን፣ ዮናስ ገረመው እና ንጋቱ ገ/ስላሴ ባስቆጠሯቸው ግቦች 3-0 ማሸነፉ ይታወሳል።
ጅማ አባጅፋር በዘንድሮው የውድድር አመት በአብዛኛው 4-4-2 የጨዋታ ዘይቤ ይዞ ወደ ሜዳ ሲገባ ተስተውሏል። በዚህ የጨዋታ ዘይቤም ለቡድኑ እጅግ ወሳኝ የሆኑ 3 ተጫዋቾችን መጥቀስ ይቻላል። የቀኝ ተከላካዩ ሄኖክ አዱኛ የቀኝ አማካዩ ዮናስ ገረመው እና ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ። በተለይ ዮናስ ገረመው እና ኦኪኪ አፎላቢ ባለፉት 3ጨዋታዎች በጋራ 5ግቦችን በማስቆጠር ቡድኑን በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ እንዲል አስችለውታል። ቅ/ጊዮርጊስ በአንፃሩ 4-3-3 የጨዋታ ዘይቤን ይዞ ወደሜዳ እየገባ ይገኛል። አጥቂዎቹን ሰልሀዲን ሰዒድ እና አሜ መሀመድን በጉዳት ካጣ በኋላ የአጥቂ አማካዮቹን ኢብራሂም ፎፋና እና አብዱልከሪም ኒኪማን በሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ሚና ለማጫወት ተገዷል። በዚህም ምክንያት ቅ/ጊዮርጊስ ግልፅ ግብ የማግባት ችግር ሲያጋጥመው ተስተውሏል። ጅማ አባጅፋር ካደረጋቸው 9ጨዋታዎች 4ቱን ከሜዳው ውጪ ያደረገ ሲሆን ዛሬ ወደ አ/አ ተጉዞ 5ኛ ከሜዳው ውጪ የሚያደርገው ጨዋታ ይሆናል፡፡ ጅማ አባጅፋር ካደረጋቸው 4 ጨዋታዎች ወደ አርባምንጭ ተጉዞ በኦኪኪ አፎላቢ ሀትሪክ ያሸነፈበት ጨዋታ ብቸኛው ከሜዳው ውጪ ያስመዘገበው ድል ሆኖ ተመዝግቦለታል። በ2 ጨዋታዎች ማለትም በመቐለ ከተማ እና በድሬዳዋ ከተማ የተሸነፈ ሲሆን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር አ/አ ስታዲየም ላይ ያለ ግብ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።
ቅ/ጊዮርጊስ በአንፃሩ ማድረግ ከሚገባው 5 የሜዳው ላይ ጨዋታዎች 4ቱን ተጫውቷል። (ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አ/አ ላይ ያደረገው የ6ኛ ሳምንት ጨዋታ ባለሜዳው ኢት. ቡና ነበር።) ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ማድረግ የሚገባው ጨዋታ ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ይታወሳል። ካደረጋቸው 4 የሜዳው ላይ ጨዋታዎች ኢትዮ-ኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ ከተማን በተመሳሳይ 3-1 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ከመቀሌ ከተማ ጋር 1-1 እንዲሁም ከመከላከያ ጋር 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።
በአጠቃላይ በፕሪሚየር ሊጉ ቅ/ጊዮርጊስ ማድረግ ከሚገባው 9ጨዋታዎች 7ቱን አድርጎ 3ጨዋታዎችን አሸንፎ በ4 አቻ ተለያይቶ 13 ነጥቦችን ሰብስቦ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ጅማ አባጅፋር በአንፃሩ 9ጨዋታዎችን አድርጎ 4ጨዋታዎችን አሸንፎ 2ጨዋታዎችን አቻ ወጥቶ 3ጨዋታዎችን ተሸንፎ ማግኘት ከሚገባው 27ነጥቦች 14ቱን አሳክቶ ከቅ/ጊዮርጊስ በ1 ነጥብ በልጦ ከመሪው ደደቢት ደግሞ በ5ነጥቦች ርቆ 2ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ከቅ/ጊዮርጊስ በኩል ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት ሰልሀዲን ሰዒድ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ታደለ መንገሻ አሁንም ለቡድኑ ግልጋሎት አይሰጡም። ከክለቡ እንደተሰማው ሰልሀዲን ሰዒድ በጂምናዚየም የአካል ብቃት ልምምድ የጀመረ ሲሆን ታደለ መንገሻ ደግሞ ከቡድኑ ጋር ልምምድ ጀምሯል። ዛሬ በተሰማ ሌላ ዜና ደግሞ የአጥቂ አማካዩ አብዱልከሪም ኒኪማ በገጠመው ከባድ የጉንፋን ህምም ምክንያት ከትናንት በስቲያ እና ትላንት ልምምድ ባለመስራቱ ይህ ጨዋታ የሚያልፈው ይሆናል፡፡ በሌላ ዜና አዲሱ ፈራሚ ጋዲሳ መብራቴ በትናንትናው የመጨረሻ ልምምድ ላይ ጉዳት አስተናግዶ ልምምዱን አቋርጦ መውጣቱን ተከትሎ በዛሬው ጨዋታ የማይኖር ይሆናል። በጅማ አባጅፋር በኩል ከወልዋሎ አ.ዩ ጋር ሲጫወቱ አማካዩ ዮናስ ገረመው፣ የፊት አጥቂዎቹ አኪኪ አፎላቢ እና ተመስገን ገብረኪዳን ተጎድተው ከሜዳ በመውጣታቸው ለዛሬው ጨዋታ የመድረሳቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አ/አ ስታዲየም ላይ 11፡00 ሲል የሚጀምር ይሆናል።