በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ህዳር 3/2010ዓ.ም ሊደረግ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን ውድድር ለማለፍ ለነበረበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና 3ተጫዋቾችን ለብሔራዊ ቡድኑ በማስመረጡ ምክንያት ሳይደረግ ለሌላ ጊዜ ተላልፎ የነበረው ጨዋታ ዛሬ እንዲደረግ ቀን ተቆርጦለታል።
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በደደቢት በመሸነፉ በውጤት ቀውስ ውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ወልድያን በማሸነፍ ወደ ድል ጎዳና በመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይሆናል።
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በ7ኛ ሳምንት ጨዋታ በአ/አ ስታዲየም በደደቢት የ3-1 አስከፊ ሽንፈት እንደደረሰበት ይታወሳል። ይህ ሽንፈቱ ለኢትዮ-ኤሌክትሪክ ተከታታይ 3ኛ የ3-1 ሽንፈቱ ነው። ካደረጋቸው 6ጨዋታዎች 1ጨዋታ ብቻ ማሸነፍ የቻለው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በ5 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ገና ከጅምሩ ላለመውረድ በመጫወት ላይ የሚገኘው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዬን አሰናብቶ የቀድሞ የአዳማ ከተማ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩትን አሸናፊ በቀለን ከሾመ በኋላ ዛሬ የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል። ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በ7ኛ ሳምንት ጨዋታ በአዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ እየተመራ የመጀመሪያ ጨዋታውን ወልድያ ከተማን በኤልያስ ማሞ 2ግቦች ታግዞ በማሸነፍ በጥሩ ሞራል ለዛሬው ጨዋታ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ቡና 1 ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከመሪው ደደቢት በ5 ነጥቦች ርቆ 11ነጥቦችን በመሰብሰብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ዛሬ 11፡30 ሲል በአ/አ ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል።
ቅድመ ዳሰሳ | በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ።
Editor at Hatricksport website