የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት የዕለተ ሰኞ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ
በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ(ሰኞ) በሚደረጉ 2 የክልል ጨዋታዎች ፍፃሜውን ያገኛል። የዚህ ቀን ሁለቱም ጨዋታዎች በሊጉ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙትን 4ቡድኖች የሚያገናኙ ይሆናል።
ሶዶ ላይ አስከፊ የውድድር ጊዜን እያሳለፉ የሚገኙት ወላይታ ድቻ እና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የሚጫወቱ ይሆናል። ወላይታ ድቻ በክለቡ 8አመታት ያሳለፉትን አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ካሰናበተ በኋላ በቀድሞ የክለቡ ከ17 አመት በታች አሰልጣኝ በነበረው ዘነበ ፍሰሀ እየተመራ ወደሜዳ የሚገባ ሲሆን ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በበኩሉ አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩን አሰናብቶ በቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ኢትዮ-ኤሌክትሪክን ይዘው የመጀመሪያ ጨዋታችውን ያደርጋሉ።
በ8ኛው ሳምንት ጨዋታ ወላይታ ድቻ ወደ ይርጋለም ተጉዞ ሲዳማ ቡናን ገጥሞ በአለማየሁ አባይነህ ቡድን የ3-1 ሽንፈት አስተናግዶ ነው ወደ ወልድያ የተጓዘው። ውጤቱንም ተከትሎ ወላይታ ድቻ 5ነጥቦችን ብቻ በመሰብሰብ የሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛል። ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በአንፃሩ በ8ኛው ሳምንት የሊጉን መሪ ደደቢትን አስተናግዶ በተመሳሳይ 3-1 መሸነፉ ይታወሳል። ባሳለፍነው ረቡዕ የ2ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታውን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አድርጎ 2-1 ድል በማድረግ ወደ አሸናፊነት ተመልሶ ወደ ሶዶ ተጉዟል። ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በሊጉ 8ነጥቦችን ይዞ ከወራጅ ቀጠናው በ3 ነጥቦች ርቆ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በወላይታ ድቻ በኩል የተሰማ አዲስ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን በኢትዮ-ኤሌክትሪክ በኩል ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫወቱ ጉዳት ያስተናገዱት ተከላካዩ አወት ገ/ሚካኤል እና አጥቂው ቢንያም አሰፋ ከቡድኑ ጋር ወደ ሶዶ ባለመጓዛቸው በዛሬው ጨዋታ የማይሳተፉ ይሆናል።