ስምንተኛ ሳምንት ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዕለተ እሁድ 7 ጨዋታዎችን በሰባት ከተሞች ያስተናግዳል።ወልቂጤ ላይ የሚካሄደው የወልቂጤ ከተማ ና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ ከጨዋታው በፊት በዚህ መልኩ ዳሰነዋል።
ወልቂጤ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ
የጨዋታ ቀን: እሁድ ጥር 2/2012
የጨዋታ ሰዓት: ከቀኑ 9:00 ሰዓት
ዳኛ: ፌደራል አርቢትር አክሊሉ ድጋፌ
ቦታ: ወልቂጤ ስታድየም
በአሰልጣኝ ደግአረገ የሚመሩት ወልቂጤዎች ጅማ አባጅፋርን ሲገጥሙ ያልተጠቀሙባቸውን የፍፁም ተፈሪ፣ የቶማስ ምህረቱ፣የአዳነ አባይነህ ና የበቃሉ ገነነን አገልግሎት በነገው ጨዋታም ማግኘታቸው አጠራጣሪ ነው።
በመቐለ 70 እንደርታዎች በኩል በያዝነው ውድድር ዓመት በጉዳት ምክንያት ምንም ጨዋታዎችን ማድረግ ያልቻለው ሚኪኤሌ ደስታ አሁንም ከቡድኑ ውጪ ሲሆን በስድስተኛው ሳምንት ከፈረሰኞቹ ጋር በነበረው ጨዋታ በሁለት ቢጫ ከሜዳ የተሰናበተው አንተነህ ገብረክርስቶስ ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።
- ማሰታውቂያ -
እድሳቱን ካጠናቀቀ በኋላ ሁለተኛ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታን የሚያስተናግደው የወልቂጤ ስታድየም በ8ተኛው ሳምንት የሰራተኞቹና የሞዐም አናብስቶቹን ጨዋታ የሚያስተናግድ ይሆናል። ባሳለፍነው ሳምንት በጅማ አባጅፋር የተሸነፋት ወልቂጤዎች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ መቐለዎችም የአሸናፊነት ጉዞዋቸውን ለማስቀጠል ነገ ከፍተኛ ፋክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በፕሪምየር ሊጉ ዝቅተኛ ግብ ያስቆጠሩት(2 ግቦች) ወልቂጤዎች አጨራረስ ላይ ያላቸውን ችግር ካልፈቱ ፕሪምየር ሊጉ ላይ የመቆየት ፍላጎታቸውን ማሳካት ላይ ችግር ሊፈጥርባቸው እንደሚችል መገመት አይከብድም። መስመር ና መሀል ላይ እንደነ ጫላ ተሺታ፣አብዱልከሪም ወርቁ ና ሄኖክ አወቀ የግብ እድሎችን በመፍጠር የማይታሙ ተጨዋቾችን የያዙት ወልቂጤዎች ግብ ማስቆጠር ላይ መቸገራቸው ቡድኑ ከወገብ በላይ ያለው ቅንጅት ላይ ጥያቄ እንዲነሳ የሚያደርግ ነው። ሥስት ግቦችን ብቻ ያስተናገደው የወልቂጤ ተከላካይ ክፍል ፈጣን የመቐለ ተጨዋቾችን መቆጣጠር ላይ ነገ ከፍተኛ ሥራ የሚጠብቀው ይሆናል።
ጃኮ አራፋት፣ጫላ ተሺታ ና አብዱልከሪም ወርቁ ላይ ትኩረት ያደረገው የወልቂጤዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያደረገ ያለውን የሻምፒዮኖቹን ተከላካይ ክፍል ሰብሮ ለመግባት ጅማ አባጅፋር ላይ ከነበረው አቀራረብ መጠነኛ የሆነ ለውጥ ማድረግ ግድ ይለዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት አዳማ ከተማን በማሸነፍ ደረጃቸውን ወደ ሁለተኝነት ከፍ ማድረግ የቻሉት መቐለዎች የሊጉ መሪ ወልዋሎ ላይ ጫና ለማሳደር ከነገው ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ግድ ይላቸዋል። ከሜዳቸው ውጪ ሥስት ጨዋታዎችን አካሂደው በአንድ አሸንፈው በሁለቱ ሽንፈት ያስተናገዱት መቐለ 70 እንደርታዎች ከሌሎች ክለቦች አንፃር ጥሩ የሚባል ቁጥር ቢሆንም ለዋንጫ ከታጩት ክለቦች ዝርዝር ውስጥ መሆናቸው ግምት ውስጥ ሲገባ ከዚህ በላይ ጥረት ይጠይቃቸዋል።
አብዛኛውን ጊዜ 4-4-2 እና 4-2-3-1 የጨዋታ አቀራረብን የሚመርጡት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ለነገው ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ ሲጫወቱ የሚመርጡትን 4-4-2 የጨዋታ ስልትን ይመርጣሉ ተብሎ ይገመታል። ከፊት አማኑኤል ገብረሚካኤልና ኦኪኪ ኦፎላቢን የሚያጣምሩት መቐለዎች በመሀል ሜዳ ከያሬድ ከበደና ዮናስ ገረመው በሚነሱ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ይገመታል።