የኢትዮጵያ ፕሪሚየር እንዲህ እንዲያ እያለ እነሆ 6ኛ ሳምንት ላይ ደርሷል። ሊጉ እስካሁን ድረስም ለ5 ሳምንታት በፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነት እና እንግዳ ክለብን በመልካም አቀባበል እየተካሄደ ሲሆን ይህም ይበል የሚያስብል ሆኖ እስከ ሊጉ ፍፃሜ መቀጠል አለበት ብለን እናምናለን።
በሊጉ 6ኛ ሳምንት 8ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ የሚካሄዱ ሲሆን አርብ እና እሁድ አንድ አንድ እንዲሁም ቅዳሜ ስድስት ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል። ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል 5ቱ ጨዋታዎች ክልል ላይ ሲደረጉ ቀሪዎቹ 3ጨዋታዎች ደግሞ አዲስ አበባ ላይ የሚደረጉ ይሆናል። ከነዚህ ጨዋታዎች መካከል ነገ(ቅዳሜ) ሲዳማ ላይ ሲዳማ ቡና ከድሬደዋ ከተማ የሚያደርጉትን ጨዋታ በዚህ ቅድመ ዳሰሳ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ።
ጨዋታ: ሲዳማ ቡና ከድሬደዋ ከተማ
የጨዋታ ቀን: ቅዳሜ ታህሳስ 24/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ፌዴራል አርቢትር ኢያሱ ፈንቴ
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ6ኛ ሳምንት ነገ ሲዳማ ቡና ከድሬደዋ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ በፌዴራል አርቢትር ኢያሱ ፈንቴ መሪነት 9:00 ላይ የሚጀምር ይሆናል። ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ የተለያየ እና የተዘበራረቀ አቋም እና ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ። ከከባባድ ሽንፈቶች በኋላ በሜዳው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለግብ አቻ የተለያየው ድሬዳዋ ከተማ የተከላካይ ክፍሉ ድክመት በሊጉ ብዙ ዋጋ እያስከፈለው እንደሆነ የተቀመጠበት የሊጉ ደረጃ ዋነኛ ማሳያ ነው። ሲዳማ ቡና ደግሞ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻልን እያሳየ የሚገኝ ሲሆን ከሊጉ መሪዎች በ1ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ መቀመጥ ችሏል። በ4ኛው ሳምንት ሲዳማ ቡና ወደ ሐዋሳ አቅንቶ በአማኑኤል እንዳለ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ይገዙ ቦጋለ ግቦች ታግዞ ሀዋሳ ከተማን አሸንፎ ሲመለስ ድሬደዋ ከተማ በአንፃሩ በሜዳው ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ ያለግብ አቻ ተለያይተዋል።
- ማሰታውቂያ -
ሁለቱ ቡድኖች በ5ሳምንት የሊጉ ጉዞ በደረጃ ሰንጠረዡ ከላይ እና ከታች የተቀመጡ ሲሆን ሲዳማ ቡና ከመሪዎቹ ወልዋሎ አ.ዩ እና መቐለ 70 እንደርታ በ 1ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ በ9ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ተጋጣሚው ድሬደዋ ከተማ ደግሞ የሊጉ ግርጌ ላይ ካለው ሀዲያ ሆሳዕና 2ነጥቦች ከፍ ብሎ በ2ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።