የ19ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ዛሬ በሚካሄዱ 7 ጨዋታዎች ሲጀምር ፡አዳማ ከተማ በሜዳው መከላከያን ሲያስተናግድ ፡ወደ አርባምንጭ ከተማ ያቀናው ኢትዬጵያ ቡና ከባለሜዳው አርባምንጭ ከተማ ጋር የሚጫዎት ሲሆን፡በአማራ ደርቢ ወልዲያ ከተማ በሜዳው ፋሲል ከተማን ሲያስተናግድ፡ጅማ አባጅፋር በሜዳው ከ መቆለ ከተማ የሚያደርጉትን ጨዋታዎች፡ በሀትሪክ ስፖርት ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ ገፃችን በክፍል 1 ዳሰሳ እንደሚከተለው ዳሰናቸዋል፡፡
☞ አዳማ ከተማ ከ መከላከያ
ዛሬ በክልል ስታዲዬሞች ከሚካሄዱት 5 ጨዋታዎች አንዱ የሆነው የአዳማ ከተማና መከላከያ ጨዋታ አዳማ ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲዬም ከቀኑ 9:00 ይካሄዳል፡፡በመሀከላቸው ባለው የ7 ነጥቦች ልዩነት በሰንጠረዡ 6ኛ እና 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የሚገናኙት ሁለቱ ክለቦች በዛሬው ጨዋታ የሚያስመዘግቡት ውጤት እጅጉን ሲበዛ ለሁለቱም ያስፈልጋቸዋል፡፡ባለሜዳዎቹ አዳማዎች ለሻምፒዬንነት ጠንካራ ተፎካካሪ ሁነው ለመዝለቅና የሊጉን መሪዎች እግር በእግር ለመከተል የዛሬውን ጨዋታ ከማሸነፍ ሌላ አማራጭ የላቸዉም ፡፡እንግዳዎቹ ጦረኞቹም ቢሆኑ ከወራጅ ቀጠና ለመትረፍና በጊዜ በሊጉ መቆየታቸውን ለማረጋገጥ ለጨዋታው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ወደሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ክለቦች በሁለተኛው ዙር ካስመዘገቧቸው ነጥቦች አንፃር የዛሬው ጨዋታ ትልቅ ፍክክር እንደሚስተናገድበት ቢጠበቅም ባለሜዳዎቹ አዳማዎች በሜዳቸው ካላቸው አልሸነፍ ባይነት አንፃር ዛሬም በቀላሉ እጅ የሚሰጡ አይመስሉም፡፡አዳማ ከተማ በ2ኛው ዙር ማድረግ ከነበረበት 3 ጨዋታዎች 2ቱን ሲያደርግ አንዱን በሜዳው ሲያሸንፍ ሌላኛውን ከሜዳው ውጭ ተሸንፈው ማግኘት ከነበረባቸው 6 ነጥብ 3ነጥብ አስመዝግበው ለጨዋታው ሲቀርቡ ፡ጦረኞቹ ካደረጓቸው 3 ጨዋታዎች በሜዳቸው 1 አሸንፈው 1ሲሸነፉ ፡ከሜዳቸው ውጭ 1ጨዋታ አቻ አስመስግበው ማግኘት ከነበረባቸው 9 ነጥቦች 4 ነጥብ በማስመዝገብ ባለሜዳው አዳማ ከተማ በኮንፌዴሬሽን ካኘ ጨዋታ ምክንያት የ18ኛውን ሳምንት መርሃ ግብር በይደር ተይዞ በ17ኛው ሳምንት በደደቢት ከሜዳው ውጭ በደረሰበት ሽንፈት ለጨዋታው ሲቀርብ መከላከያ በ18ኛው ሳምንት በሜዳው በኢትዮጵያ ቡና ከደረሰበት የ2ለ ምንም ሽንፈት ለማገገም ለጨዋታው ቀርበዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
በውጤት ማጣት ቀውስ ወረጂ ቀጠና የሰነበተው መከላከያ የአሰልጣኝ ለውጥ ከዳረገ በሇላ በትንሹም ቢሆን መሻሻል እያሳየ ከመምጣቱም ባሻገር ለጊዜውም ቢሆን ከወራጂ ቀጠናው ወቶ በዚሁ ለመቆየት በዛሬው ጨዋታ ባለሜዳዎቹን ሊፈትን እንደሚችል የሚጠበቅ ነው፡፡በሌላ በኩል ባለሜዳዎቹ አዳማዎች የሜዳቸውን አይበገሬነት ዛሬስ ይዘው ይወጣሉ ወይ የሚለው እንዳለ ሁኖ የዛሬውን ጨዋታ አሸንፈው ከሊጉ መሪ ደደቢት ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ የሜዳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በትልቅ ተነሳሽነትና ትኩረት የሚጫዎቱ ይሆናል፡፡
ባለሜዳዎቹ አዳማዎች ተጋጣሚያቸውን የሚያሸንፉ ከሆነ ነጥባቸውን ወደ 29 በማድረስ ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ጠባብ ዕድል ይኖራቸዋል፡፡በተለይም ጅማ ስታዲዬም ላይ በሚካሄደው የጅማ አባጅፋር እና መቆለ ከተማ ጨዋታ የሚሸናነፉ ከሆነ እና ፈረሰኞቹ ነጥብ የሚጥሉ ከሆነ ለአዳማ ከተማ ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበትን መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ሲሆን በተቃራኒው ነጥብ የሚጥሉ ከሆነ እስከ 8ደረጃ ዝቅ ሊሉ ይችላሉ፡፡
እንግዳዎቹ ጦረኞች በዛሬው ጨዋታ የሚያሸንፉ ከሆነ ነጥባቸውን ወደ 22 በማድረስ ሰንጠረዡ እስከ 10ደረጃ ከፍ የሚሉበት አጋጣሚ የሚፈጠር ሲሆን ሽንፈት የሚያስተናግዱ ከሆነ አሁን ያሉበትን 12 ደረጃ ለቀው በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ በመውረድ ወራጂ ቀጠና ገብተው 20ኛውን ሳምንት ይጠብቃሉ፡፡
በቅጣት እና ጉዳት ዜና ባለሜዳዎቹ አዳማዎቹ በጉዳት የሚካኤል ጆርጂ ፡ሱራፌል ዳኛቸው እና ኤፍሬም ዘካሪያስን ግልጋሎት የማያገኙ ሲሆን በእንግዳዎቹ በኩል ሽመልስ ተገኝ በቅጣት ፡የምንይሉ ወንድሙ፡ቴዎድሮስ በቀለና ተመስገን ገ/ፃድቅን ግልጋሎት በጉዳት አያገኝም፡፡
የ2010 የርስበርስ ግንኙነት ስንመለከት በመጀመሪያው ዙር
ሁለቱ ክለቦች በአዲስአበባ ስታዲዬም በተገናኙበት ጨዋታ ያለ ግብ አቻ መለየታቸው ይታወሳል፡፡
ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወ/ጊዬርጊስ በመሃል ዳኝነት ይመሩታል፡፡
☞ አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በተለያዬ ሁለት ተቃራኒ ፍላጎቶች በእንግዳዎቹ በኩል ለሻምፒዮንነት በባለሜዳዎቹ በኩል ላለመውረድ በሚደረግ ፍልሚያ በተለያዩ ወቅታዊ የቡድን አቋም ላይ ሁነው የሚገናኙት አርባምንጭ ከተማ እና ኢትዬጵያ ቡና በአርባምንጭ ስታዲዬም የሚያደርጉት ጨዋታ 9:00 ይጀምራል፡፡
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን ባስመዘገቡት ውጤት በደረጃ ሰንጠረዡም ሆነ በነጥብ ተራርቀው ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ከወዲሁ በበርካቶች ከሚጠብቁት የክልል ስታዲዬም ጨዋታዎች አንዱ ነው፡፡ባለሜዳዎቹ አዞዎቹ በዘንድሮው የውድድር ጊዜ ከሊጉ መጀመሪያ ሳምንት እስካሁን ያስመዘገቡት ውጤት በቀጣዩ አመት በሊጉ ስለመቆየታቸው ማስተማመኛ የሚሆን አይደለም፡፡ከሊጉ የመውረድ ስጋት የተደቀነባቸው አዞዎቹ የአሰልጣኝ ለውጥ ከማድረግ በተጨማሪም የአመራር እና የተጨዋቾችን ኮንትራት ውል የማቋረጥ አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ ቢቀላቅሉም ውጤት እየቀናቸው አይደለም፡፡ቡድኑ በየሳምንቱ በየጨዋታው ከሊጉ ከመውረድ ለመትረፍ በትኩረት ቢጫዎትም የሚያስመዘግቡት ውጤት አሁን ያሉበትን ደረጃ የሚያጠናክር እየሆነ መምጣቱ በደጋፊዎቻቸውም የመውረድ ስጋትን አጭሯል፡፡
በአንፃሩ እንግዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች በሊጉ መጀመሪያ ሳምንታት ከነበሩበት ችግር ተላቀው አሁን በትክክለኛውና ወደ ስኬት እሚያደርሳቸው ባቡር ላይ ከተሳፈሩ ሰነባብተዋል፡፡በዛሬው ጨዋታ በትልቅ የአሸናፊነት ስነልቦና ላይ ያሉት ቡናዎች በባለሜዳዎቹ አዞዎች በቀላሉ ይሸነፋሉ አለያም ነጥብ ይጥላሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ሁለቱ ክለቦች በሁለተኛው ዙር ካደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች ያስመዘገቡትን ውጤት ስንመለከት ባለሜዳዎቹ አርባምንጭ ከተማዎች ማግኘት ከነበረባቸው 9 ነጥብ 3 ነጥብ ሲያስመዘግቡ፡ኢትዮጵያ ቡናዎች ማግኘት ከነበረባቸው 9 ነጥብ ሁሉንም በማሰስመዝገብ የሊጉ መጀመሪያ ዙር ሲጠናቀቅ ከነበሩበት 7ኛ ደረጃ ከፍ ብለው መሪውን ደደቢት በመከተል በ2 ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ባለሜዳዎቹ አዞዎቹ በ18ኛው ሳምንት ከሜዳቸው ውጭ በኢትዬ ኢለክትሪክ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ለጨዋታው ወደ ሜዳ ሲገቡ እንግዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተከታታይ ውጤት እየቀናቸው የማሸነፍ ሪከርዳቸውን ለማስቀጠል የሚፋለሙ ይሆናል፡፡
የዛሬው ጨዋታ ውጤት ከመቼውም በላይ ለባለሜዳዎቹም ሆነ ለእንግዳዎቹ አስፈላጊ ነው፡፡ባለሜዳዎቹ ዛሬ ተጋጣሚያቸውን የሚያሸንፍ ከሆነ እና የአዲግራቱ ስታዲዬም ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቆ ድሬድዋ ከተማ በተጋጣሚው ነጥብ የሚጥል ከሆነ ለጊዜውም ቢሆን አዞዎቹ ወራጂ ቀጠናውን ለቀው የሚወጡበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡በሌላ በኩል አዞዎቹ የሚሸነፉ ከሆነ እራሳቸውን የበለጠ ከወራጂ ቀጠናው የሚያዛምዱ ይሆናል፡፡
እንግዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች በጨዋታው ውጤት የሚቀናቸው ከሆነ እና የሊጉ መሪ ደደቢት በድሬዳዋ ከተማ የሚሸነፍ ከሆነ ቡናዎች ከሊጉ መሪ በነጥብ እኩል በመሆን በጎል ተበልጠው 20ኛውን ሳምንት በተስፋ የሚጠብቁበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡በተቃራኒው ቡናዎች የሚሸነፉ ከሆነ ሰንጠረዡ እስከ 6ኛ ደረጃ ሊወርዱ ይችላሉ፡፡
የሁለቱ ክለቦች የቅርብ ግንኙነት በመጀመሪያ ዙር አዲስ አበባ ላይ በተገናኙበት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ 2ለ ምንም ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡
ጨዋታውን በመሃል ዳኝነት አልቢትር ዳዊት አሳምነው ይመሩታል፡፡
☞ወልዲያ ከተማ ከ ፋሲል ከተማ (አማራ ደርቢ)
ሁለቱን የአማራ ተወካይ ክለቦች እርስበርሳቸው የሚያገናኘው የደርቢ ጨዋታ በወልዲያ ሼህ ሙሃመድ አሊ አላሙዲን ስታዲዬም ዛሬ 9:00 ላይ ይካሄዳል፡፡
ይሄው የአማራ ደርቢ ጨዋታ ዛሬ ወልዲያ ላይ ሲካሄድ ሁለቱም ክለቦች በውጤት ማጣት ላይ ሁነው ሲገናኙ ባለሜዳዎቹ ወልዲያዎች የውድድር አመቱን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ እየተፈተኑ ከወራጂ ቀጠናው ለመራቅ ጨዋታውን ማሸነፍ የግድ ሲሆንባቸው ፡እንግዳዎቹ ፋሲል ከተማዎች በበኩላቸው በዕቅዳቸው ያካተቱትን ሻምፒዬን የመሆን ህልም ዕውን ለማድረግ በየሳምንቱ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ አስፈላጊ በመሆኑ ዛሬም የዚህ ጨዋታ አሸናፊ ለመሆን ይፋለማል፡፡
በእንግዳዎቹ ፋሲል ከተማዎች በኩል በውጤት ማጣትና በቡድኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጥሩ ባለመሆኑ አሰልጣኝ ምንተስኖትን ጌቱን አሰናብተው የቀድሞውን የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን መሾማቸው የሚታወቅ ሲሆን አሰልጣኙ ዛሬ አፄዎቹን እየመራ የመጀመሪያውን ጨዋታ ሲያደርግ ደጋፊዎች ጥሩ ውጤት ሊመዘገብ እንደሚችል በአዲሱ አሰልጣኝ መሳይ እምነት ጥለዋል፡፡በዚህ ጨዋታ ሁሌም በፋሲላውያኑ ልብ የማይረሳው አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዬረርጊስ ፋሲል ከተማን ከከፍተኛ ሊጉ ያሳደገው እና ዛሬ ወልዲያ ከተማን እየመራ የቀድሞ ክለቡን ይገጥማል፡፡
በሁለተኛው ዙር ሁለቱ ክለቦች ካደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች ያስመዘገቧቸው ነጥቦች ውጤት እየራቃቸው መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ባለሜዳዎቹ ካደረጓቸው ጨዋታዎች በ2 ጨዋታ ተሸንፈው በ1 አቻ ተለያይተው ማግኘት ከነበረባቸው 9 ነጥቦች 1 ነጥብ ብቻ ሲያስመዘግቡ እንግዳዎቹ አፄዎቹ 1ጨዋታ ሲየያሸንፉ በ1ጨዋታ አቻ ሲለያዩ በ1ጨዋታ ተሸንፈው ማግኘት ከነበረባቸው 9 ነጥቦች 4ነጥብ አስመዝግበዋል፡፡
በዛሬው ጨዋታ ወልዲያ ከተማ ባለፈው ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ ከደረሰበት የ2ለምንም ሽንፈት ለማገገም ይሄ ጨዋታ ወሳኝ ሲሆን፡በእንግዳዎቹ ፋሲል ከተማዎች በኩልም ቢሆን በሜዳቸው ከጅማ አባጅፋር ያለ ግብ ነጥብ ተጋርተው መለየታቸው የሚታወስ ሲሆን በተሎ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይሄው ጨዋታ ወሳኝ ይሆናል፡፡
በዚህ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ የሚያሸንፉ ከሆነ እና ሲዳማ ቡና የሚሸነፍ ከሆነ ነጥባቸውን 22 በማድረስ በደረጃ ሰንጠረዡ አሁን ካለሉበት 11ኛ ደረጃ አንድ ደረጃ የሚያሻሽሉበት አጋጣሚ የሚፈጠር ሲሆን ፡የሚሸነፉ ከሆነና ከስሩ ያሉት የሚያሸንፉ ከሆነ ወራጂ ቀጠናውን በድጋሚ የሚቀላቀል ይሆናል፡፡በሌላ በኩል እንግዳዎቹ ፋሲል ከተማዎች ውጤት የሚቀናቸው ከሆነ የሌሎችን ክለብ ውጤቶችን ጠብቀውም ቢሆን በደረጃ ሰንጠረዡ እስከ 5ኛ ከፍ የሚሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል የሚጠበቅ ነው፡፡
በጉዳትና ቅጣት ዜና በአፄዎቹ በኩል አብዱራህማን ሙባረክ፡አይናለም ሀይለ፡ያሬድ ባዬ በጉዳት በዛሬው ጨዋታ የማይሰለፉ ሲሆን በወልዲያ ከተማ በኩል የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና እስካሁን የተነገረ ነገር የለም፡፡
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር በተገናኙበት የአፄፋሲለደሱ ስታዴም ጨዋታ ያለግብ ነጥብ ተጋርተው መለያዬታቸው ይታወሳል፡፡
ጨዋታውን በመሃል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ይመሩታል፡፡
☞ጅማ አባጅፋር ከ መቐለ ከተማ
ዘንድሮ ሊጉን ተቀላቅለው ክሰተት የሆኑት ሁለቱ ክለቦች በደረጃ በሰንጠረዡ በ1 ነጥብ ተበላልጠው 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የሚፋለሙበት ይሄው የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ጅማ ስታዲዬም 9:00 ላይ ይጀምራል፡፡
በዚህ ጨዋታ አሸናፊ የሚሆነው ክለብ ውጤቱ ከሶስት ነጥብ በላይ ነው፡፡እርስበርስ በዋንጫ ፉክክር በሚያርጉት ጉዞ የበለጠ በቀጣይ ተፎካካሪ ሁኖ ለመቆየት በጨዋታው ውጤት ማስመዝገብ ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ ነው፡፡ባለሜዳዎቹ በመጀመሪያው ዙር ከነበራቸው ጥንካሬ በሁለተኛው ዙር በትንሹም ቢሆን ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ስንመለከት ውጤታማ አለመሆናቸው ለዚህ ጨዋታ የበለጠ ተትኩረት የሚሰጡ ይሆናል፡፡
በእንግዳዎቹ በኩል በሁለተኛው ዙር ማድረግ ከነበረባቸው ሶስት ጨዋታዎች በ16ኛው ሳምንት በሜዳው አርባምንጭ ከተማን በጎል ተንበሽብሸው ካሸነፉበት ጨዋታ ውጭ ሌላ ጨዋታ አላደረጉም፡፡በኮንፌደሬሽን ካኘ ጨዋታ ምክንያት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በይደር የተያዘ ጨዋታ ሲኖር በ17ኛው ሳምንት አዲግራት ላይ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር በነበረባቸው ጨዋታ በደጋፊዎች በተነሳ ረብሻ ጨዋታው መቋረጡ የሚታወቅ ሲሆን ከረፍት የሚመለሱት መቆለዎች ጨዋታውን ለማሸንፍ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም፡፡
ጅማ አባጅፋሮች በሁለተኛው ዙር ካደረጓቸው 3 ጨዋታዎች በ1አሸንፈው በ1 ተሸንፈው በ1አቻ ውጤት አስመዝግበው ፡ማግኘት ከነበረባቸው 9 ነጥብ 4ነጥብ ሲያስመዘግቡ እንግዳዎቹ ካደረጓቸው 1ጨዋታ 3ነጥብ አስመዝግበው በቀሪ ተስተካካይ የጨዋታ መርሃ ግብር 2 ጨዋታ ይቀራቸዋል፡፡በዛሬው ጨዋታ መቆለዎች በአሸናፊነት ስነ ልቦና ለጨዋታው የሚቀርቡ ሲሆን ባለሜዳዎቹ አፄ ፋሲለደስ ላይ ካስመዘገቡት የአቻ ውጤት ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሜዳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በደጋፊዎቻቸው ፊት ተጋጣሚያቸውን ለማሸነፍ የሚጫዎቱ ይሆናል፡፡
ጨዋታውን ባለሜዳዎቹ አሸንፈው ነጥባቸውን ወደ 32 በማድረስ የኢትዮጵያ ቡናን ውጤት ጠብቀው በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ 2ኛነት ከፍ ሊሉ የሚችሉበት ዕድል ሲኖር እንግዳዎቹም በተመሳሳይ የሚያሸንፉ ከሆነ ነጥባቸውን ወደ 31 በማድረስ ወደ 2ኛነት ከፍ የሚሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡
በጉዳት እና ቅጣተት ዜና በሁለቱም ቡደድኖች በኩል እስከካሁን የተነገረ ነገር የለም፡፡
ጨዋታውን በመሃል ዳኝነት ፌደራል ዳኛ ተፈሪ ዳኘ እንደሚመሩት ታውቋል፡፡