የ22ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪሚዬር ሊግ በሶስተኛ ቀኑ ዛሬ በክልል እና በመዲናዋ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል መቆለ እና አዲስአበባ ላይ የሚካሄዱትን ጨዋታዎች በቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል፡፡
መቀለ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ
ይሄ ጨዋታ ክልል ላይ በብቸኝነት ከቀኑ 9:00 በግዙፉ ትግራይ ስታዲዬም በጥሩ መነሳሳት ላይ ያሉትን ሁለቱን ቡድኖች መቀለ ከተማን ከወላይታ ድቻ ያገናኛል፡፡ባለፈው ሳምንት ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከፊታቸው የነበሩትን ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው መገናኘታቸው ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል፡፡ባለሜዳዎቹ መቀለዎች ወደ አዲስአበባ አቅንተው ደደቢትን አሸንፈው ሲመለሱ ወላይታድቻዎች ከአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ስንብት መልስ በቅጣት ወደ ሰበታ በዞረው ጨዋታ ፋሲል ከተማን አሸንፈው ለጨዋታው በጥሩ መነቃቃት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡
ሁለት ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታ ያላቸው መቀለ ከተማና ወላይታ ድቻዎች ከጨዋታው የሚያገኙት ሶስት ነጥብ ለሁለቱም አስፈላጊ ቢሆንም ለባለሜዳዎቹ የበለጠ ያስፈልጋቸዋል፡፡መቀለዎች ጨዋታውን የሚያሸንፍ ከሆነ በዋንጫ ፉክክሩ ከመቆታቸውም ባሻገር ከመሪዎቹ ያላቸውን የነጥብ ልዩነት አጥበው ጉዟቸውን ወደ እውነተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ መሆናቸውን ከማረጋገጥ በላፈ በሰንጠረዡ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ የሚሉበት ዕድል አላቸው፡፡ወላይታ ድቻዎች ወደ ዋንጫ ፉክክሩ መጠጋት የሚችሉበት አጋጣሚ የሚፈጠር ቢሆንም እውነተኛ ተፎካካሪ ለመሆን ግን በየሳምንቱ ከየጨዋታው ሶስት ነጥብ እያስመዘገቡ የሌሎችን ነጥብ መጣል መጠበቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
በዛሬው ጨዋታ በባለሜዳዎቹ መቆለዎች በኩል የዳንኤል አድሃኖምና ያሬድ ከበደን ግልጋሎት በጉዳት የማያገኙ ሲሆን የወላይታ ድቻዎቹ ያሬድ ዳዊትና ፀጋዬ ብርሃኑም ይሄ ጨዋታ በጉዳት እንደሚያልፋቸው የተነገረ ሲሆን የቅጣት ዜና በተመለከተ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የለም፡፡
በዚህ ጨዋታ በጋቶቾ ፓኖም የሚመራው የመቀለ ከተማ አማካኝ ክፍል በሀይማኖት ወርቁ ከሚመራው የወላይታ ድቻ አማካኝ ክፍል የመሃል ሜዳውን የበላይነት ለመውሰድ የሚያደርጉት ትንቅንቅ የመሃሉን ክፍል በአመዛኙም ቢሆን የሚወስደው ቡድን ግብ ለማስቆጠር ቀዳሚ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ሁለቱም ቡድኖች የመሃል ክፍላቸው ጥሩ በማይሆንበት ጊዜ በመስመር በኩል ግብ ለማስቆጠር የማይቸገሩ እንደመሆናቸው፡ዛሬም እንደ አማራጭ ሳይሆን በሁለቱም በኩል ትኩረት ሰጥተው ግብ ለማግኘት ወደ መስመር እንደሚዎጡ ይታሰባል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ሶዶ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙበት ጨዋታ መቀለዎች 1-0 አሸንፈዋል፡፡
ፌደራል ዳኛ ወልዴ ንዳው ጨዋታውን በመሃል ዳኝነት ይመሩታል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና ከ ጅማአባጅፋር
ዛሬ አዲስአበባ ላይ በርካታ ተመልካቾች እንደሚታደሙበት የሚጠበቀው የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ከቀኑ 10:00 ይጀምራል፡፡ለዚህ ጨዋታ ባለሜዳዎች ቡናዎች በሸገር ደርቢ እዚሁ ሜዳ በቅርብ ተፎካካሪያቸው ቅ/ጊዬርጊስ ሽንፈት አስተናግደው ለጨዋታው ሲቀርቡ፡ጅማ አባጅፋሮች በሜዳቸው ኢለክትሪክን በጎል ተንበሽብሸው በማሸነፍ ለዚህ ጨዋታ በትልቅ ጠንካራ የአሸናፊነት ስነልቦና እንደሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች የዛሬው ጨዋታ ውጤት ለሁለቱም ቡድኖች ትልቅ ዋጋ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች ጨዋታውን አሸንፈው ከባለፈው ሽንፈት ከማገገም ባለፈ በዋንጫ ፉክክሩ ቀጥተኛ ተፎካካሪ ሁኖ ለመቆየት ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ከማግኘት ሌላ አማራጭ የለም፡፡ቡናዎች ጨዋታውን በማሸነፍ ከተጋጣሚያቸው ከሊጉ መሪ ጅማአባጅፋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ዝቅ ለማድረግ በደጋፊዎቻቸው ፊት የማይፈነቅሉት ነገር
አይኖርም፡፡ጅማአባጅፋሮች በበኩላቸው በእጃቸው ያለውን ወርቃማ ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም በዛሬው ጨዋታ ባለሜዳዎቹን ኢትዮጵያ ቡናዎች የሚፋለሙ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናዎች በአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሚዝ እየተመሩ በኳስ ቁጥጥርና በፈጣን ሽግግር በተጋጣሚ ላይ ጫና በመፍጠር ግብ ለማስቆጠር የሚሞክር ቡድን ለመስራት እየሞከሩ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት በሸገር ደርቢ በረጅሙ ወደፊት ለአጥቂ ክፍሉ በሚጣሉ ኳሶች ግብ ለማግኘት መጫዎቱ አነጋጋሪ ቢሆንም በዛሬው ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን በተጋጣሚው ላይ በመውሰድ ግብ ለማስቆጠር እንደሚጫዎትና ባለፈው ሳምንት ተጠባባቂ የነበሩት ኤሊያስ ማሞና ሀይሌ ገ/ተንሳይ በዚህ ጨዋታ በቋሚ አሰላለፍ ጨዋታውን እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡
ጅማአባጅፋሮች በሁለቱ የመስመር ተከላካዮች አማካኝነት ሜዳውን በመለጠጥ ኳሶችን ወደ ሜዳው ጠርዝ በማውጣት የማጥቃት ዕቅዳቸውን ለማሳካት በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ከመጫዎታው ባሻገር ለአጥቂ ክፍሉ አልፎ አልፎ ከመስመር በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ግብ ለማግኘት እንደሚጫዎቱ ይጠበቃል፡፡ከተከታዮቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የቅርብ ተፎካካሪውንና ባለሜዳውን ለማበርከክ ሲጫዎት የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ኦኪካ ኦፎላቢ ዛሬስ ግብ ያስቆጥራል ወይ የሚለው በጨዋታው የሚጠበቅ ነው፡፡በጨዋታው ከማሸነፍ ውጭ ለሁለቱም አዋጭ አይሆንም፡፡በተለይም ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከዚህ ጨዋታ ሶስት ነጥብ ማግኘት ካልቻሉ ከወዲሁ ከዋንጫው ፉክክር እውነተኛ ተፎካካሪ መሆናቸው የሚያበቃለት ይመስላል፡፡
በዛሬው ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የጉዳት ዜና ባይኖርም፡የኢትዬጵያ ቡናው አስናቀ ሞገስ በቅጣት በጨዋታው እንደማይኖር ታውቋል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ጅማ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙበት ጨዋታ ጅማ አባጅፋሮች በሜዳቸው 2-0 ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡
ጨዋታውን በመሃል ዳኝነት ፌደራል ዳኛ ማናዮ ወ/ፃድቅ የሚመሩት ይሆናል፡፡