የ24ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪሚዮር ሊግ በወሳኝ ምዕራፍ ለሻምፒዮንነት እና ላለመውረድ በሚደረጉ ትንቅንቆሽ ዛሬ በአዲስ አበባ እና በክልል ስታዲዮሞች በሚካሄዱ 7 ጨዋታዎች ከቀኑ በ9:00 የሚጀምር ሲሆን በዳሰሳችን 2 የአዲስ አበባ ጨዋታዎችን እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል፡፡
ኤሌክትሪክ ከ ወላይታድቻ
በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገቧቸው ውጤቶች ከወራጂ ቀጠናው ግርጌ ተላቀው በወራጂ ቀጠናው አፋፍ ላይ ተቀምጠው ከመውረድ ለመትረፍ በሚያደርጉት ጉዞ ባለፈው ሳምንት በርካታ ግቦች በተስተናገዱበት የአዲስ አበባው ጨዋታ ደደቢትን 4-3 አሸንፈው በትልቅ መነሳሳት ላይ ያሉት ኤሌክትሪኮች ዛሬ በ9:00 ባለፈው ሳምንት በሜዳቸው ሶዶ ላይ ሲዳማ ቡናን አስተናግደው፡በጨዋታው መገባደጃ ባስቆጠሯቸው ግቦች ከሽንፈት ተርፈው ነጥብ በመጋራት፡በሊጉ በደረጃ መዳቢነት የተቀመጡትን ወላይታ ድቻዎችን ያስተናግዳሉ፡፡
ይሄ ጨዋታ ለሻምፒዮንነት የሚደረገውን ፉክክር ያኸል ትልቅ ግምት ባይሰጠውም የጨዋታው ውጤት ግን ለሁለቱም ቡድኖች አስፈላጊነቱ ወሳኝ ነው፡፡ወላይታ ድቻ በሰንጠረዡ 9ኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጥም አሁንም ቢሆን በቁጥራዊ ስሌት ከመውረድ ስጋት ነፃ ለመሆን በተለይም ይህን ጨዋታ ማሸነፍ እጅጉን ያስፈልጋቸዋል፡፡ባለሜዳዎቹ ኤሌክትሪኮች ጨዋታውን በሜዳቸው ከማድረጋቸውም ባሻገር ላለመውረድ በሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ በወራጂ ቀጠናው ያሉት አርባምንጭ ከተማ እና ወልዲያ ከተማ በተመሳሳይ ሰዓት እርስ በርሳቸው መገናኘታቸው ምናልባትም የኤሌክትሪክን በወራጂ ቀጠናው አፋፍ የመቆየት አለያም ከፍ የማለት ዕድል ያሰፋዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ወላይታ ድቻዎች በወራጂ ቀጠና ከሚገኙት ክለቦች አሁን በመሀከላቸው ያለውን የ5 ነጥብ ልዩነት አስፍተው በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ የሚሉበት ዕድል ባይኖርም በመጠኑም ቢሆን እራሳቸውን ከመውረድ ስጋት ማራቅ የሚችሉበትን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም ዛሬ ባለሜዳዎቹን ኤሌክትሪኮች ለማሸነፍ የሚፋለሙ ይሆናል፡፡በ24 ነጥብ በሰንጠረዡ 13ኛ ደረጃ የተቀመጡት ባለሜዳዎቹ ይህን ጨዋታ አሸንፈው ደረጃቸውን ያሻሽሉ ይሆን ?? ከሚለውም ባሻገር በኤሌክትሪክ ቤት ብቻውን ጎልቶ የወጣው የፊት መስመር ተሰላፊው አልሃሰን ካሉሻ ዛሬስ ግብ ያስቆጥር ይሆን የሚለው የሚጠበቅ ነው፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር የኢትዮጵያ ኘሪሚዮር ሊግ ሶዶ ስታዲዮም ላይ ባደረጉት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ የጦና ንቦች 2-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡
ጨዋታውን በመሃል ዳኝነት አርቢትር ጌቱ ተፈራ ይመሩታል፡፡
መከላከያ ከ ቅዱስጊዮርጊስ
በመጀመሪያው ዙር የኘሪሚዮር ሊግ ጨዋታ ያለ ግብ ነጥብ ተጋርተው በመካከላቸው ባለው ሰፊ የነጥብ ልዩነት በደረጃ ሰንጠረዡ 11ኛ እና 2ኛ ላይ የተቀመጡት ጦረኞቹና ፈረሰኞቹ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ 11:00 ይጀምራል፡፡ቀስ በቀስ ከወራጂ ቀጠናው ተላቆ የወጣው መከላከያ ዛሬ ከአፍሪካ መድረክ ማግስት ዳግመኛ ወደለመደው ወንጫ ፊቱን የመለሰውን ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያስተናግድበት ጨዋታ በርካቶች በጉጉት ይጠበቁታል፡፡ጦረኞቹ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ወደ ሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል አቅንተው በድሬዳዋ ከተማ 1-0 ተሸንፈው ሲመለሱ ተጋጣሚያቸው ቅ/ጊዮርጊስ እዚሁ አዲስአበባ ላይ ዝናባማ በነበረው የመዲናዋ የአየር ሁኔታ ወልዋሎን በደጋፊዎቻቸው ፊት 1-0 ረተው ዳግም ወደዋንጫው የተመለሱበትን ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን ዛሬ ይህን ጨዋታ አሸንፈው የሊጉ አናት ላይ ለመቀመጥ የሚጫዎቱ ቢሆንም ከጦረኞቹ ብርቱ ፈተና
እንደሚጠብቃቸው ይታሰባል፡፡
ጦረኞቹ በሁለተኛው ዙር በመጠኑም ቢሆን በጥሩ መሻሻል በመጀመሪያው ዙር ከነበሩበት የውጤት ማጣትና የመውረድ ስጋት ወጥተው በሊጉ መሃል ሰፋሪ ሁነው ለማጠናቀቅ የሚያስችላቸው ዕድል በማመቻቸት በጥሩ ፎርም ላይ ናቸው፡፡ለዚህም ባለፈው ሳምንት በድሬድዋ ከተማ ሽንፈት ከማስተናገዳቸው በፊት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግበዋል፡፡ጦረኞቹ በ28 ነጥብ ከተቀመጡ 11ኛ ደረጃ ከፍ ለማለት ይሄን ጨዋታ አሸንፈው የሌሎችን ውጤት ጠብቀውም ቢሆን እስከ 9ኛ ደረጃ ከፍ የሚሉበትን አጋጣሚ ለማመቻቸት ፈረሰኞቹን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ የሚጠበቅ ይሁን እንጁ ፈረሰኞቹ በቀላሉ ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ያጣሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡
በተለይም ፈረሰኞቹ ለሻምፒዮንነት በሚያደርጉት ጉዞ ከዚህ ጨዋታ የሚያስመዘግቡት ውጤት እጅጉን ወሰኝነቱ የጎላ ነው፡፡በ3 ግቦች ተበልጠው በ2ኛ ደረጃ እንደመቀመጣቸው ይሄን ጨዋታ በብዙ ግቦች የሚያሸንፉ ከሆነ ወደ ሊጉ አናት መሪነት ለመመለስ የሚያስችላቸው አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል ሁሉ ፡በሊጉ ባለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር የሚሸነፉ ከሆነ አሁን ያሉበትን 2ኛ ደረጃ ሊነጠቁ ይችላሉ፡፡
ጨዋታውን በመሃል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ የሚመሩት ይሆናል፡፡