የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ
የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ዛሬ እና ነገ በሚደረጉ 8ጨዋታዎች ጅማሬውን የሚያደርግ ይሆናል።
በ16ኛው ሳምንት በዕለተ ቅዳሜ አ/አ ላይ ሁለት ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን 8:00 ሲል ፋሲል ከተማ ከ ወልዋሎ አ.ዩ እንዲሁም 10:00 ሲል መከላከያ ከ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የሚገናኙ ይሆናል።
ፋሲል ከተማ ከ ወልዋሎ አ.ዩ
ጎንደር ፋሲለደስ ስታዲየም ላይ መደረግ የነበረበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአንዳንድ የፀጥታ ችግር ምክንያት አ/አ ስታዲየም ላይ እንዲደረግ ተወስኗል።
- ማሰታውቂያ -
የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ውጤት
ፋሲል ከተማ በመጀመሪያው ዙር ካደረጋቸው 15ጨዋታዎች 5ቱን አሸንፎ በ7 አቻ ወጥቶ በ3 ተሸንፎ 12ግቦችን አስቆጥሮ 13ተቆጥሮበት በ22 ነጥቦች እና በ1 የግብ እዳ 6ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ካለፉት ካደረጋቸው 10ጨዋታዎች 1ብቻ ማሸነፍ የቻለው እና እንደ አጀማመሩ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው ወልዋሎ አ.ዩ. ከ15ጨዋታዎች 3ብቻ አሸንፎ እንደ ፋሲል ከተማ ሁሉ በ7ቱ አቻ ተለያይቶ ቀሪዎቹን 5ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ ከወራጅ ቀጠናው በ3ነጥቦች ብቻ ከፍ ብሎ በ16 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ አዲግራት ላይ ተገናኝተው ጨዋታቸውን 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።
በፋሲል ከተማ በኩል ረጅም ጉዳት ላይ የነበሩት ተከላካዮቹ አይናለም ኃይለ እና ያሬድ ባየህ ልምምድ የጀመሩ ቢሆንም የዛሬው ጨዋታ የሚያልፋቸው ይሆናል። በሌላ ዜና ፋሲል ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተው እና የ4 ጨዋታዎች ቅጣት የተጣለበት ራምኬል ሎክ ቅጣቱን ባለመጨረሱ የዛሬው ጨዋታ የሚያልፈው ይሆናል። በወልዋሎ በኩል ደግሞ ሳምሶን ተካ በጉዳት ብርሀኑ አሻሞ በቅጣት እንዲሁም ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ከ20 አመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመመረጡ በዚህ ጨዋታ ለቡድናቸው ግልጋሎት የማይሰጡ ይሆናል።
ኢ/ዳኛ ብሩክ የማነብርሃን የሚመሩት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ልክ 8:00 ሲል አ/አ ስታዲየም ላይ የሚደረግ ይሆናል።
መከላከያ ከ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ
ዛሬ ከሚደረጉ 7ጨዋታዎች መካከል አ/አ ስታዲየም ላይ የሚደረገው ሁለተኛ ጨዋታ መከላከያ ከ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የሚያደርጉት ነው።
በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ መጥፎ አቋም ማለት በሚቻል የውጤት መውረድ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ ጨዋታ ነው። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ከቀጠረ በኋላ መሻሻልን እያሳየ የሚገኘው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በአንደኛው ዙር እጅግ ደካማ የነበረውን የተከላካይ ክፍሉን በአግባቡ ካላጠናከረ አሁንም እንዳለፉት አመታት ሁሉ ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን እንዳይሆን ያሰጋል። በመከላከያ በኩልም አሰልጣኝ ሻ/ል ምንያምር ፀጋዬን አሰናብቶ የቀድሞውን የሰበታ ከተማ አሰልጣኝ የነበሩትን አሰልጣኝ ስዩም ከበደን መቅጠሩ የሚታወስ ነው። በአንደኛው ዙር የመከላከያ ድክመት ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው የቡድኑ ግብ ማስቆጠር ችግር ሲሆን ለዚህም እንደማሳያ ሊጠቀስ የሚችለው በ15 ጨዋታዎች ቡድኑ ማስቆጠር የቻለው 6ግቦችን ብቻ መሆኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ቡድኑ ብዙ ግብ የማግባት አማራጮች አለመኖራቸው እንደ ችግር ይነሳል። ለዚህም መከላከያ ካስቆጠራቸው 6ግቦች 5ቱን ምንይሉ ወንድሙ ማስቆጠሩ ለዚህ ተጠቃሽ ማስረጃ ነው።
የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ውጤት
መከላከያ በመጀመሪያው ዙር ካደረጋቸው 15ጨዋታዎች 3ቱን አሸንፎ በ6 አቻ ወጥቶ በ6 ተሸንፎ 6ግቦችን አስቆጥሮ 14ተቆጥሮበት በ15 ነጥቦች እና በ8 የግብ እዳ 13ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በበኩሉ ከ15ጨዋታዎች 3ብቻ አሸንፎ በ5ቱ አቻ ተለያይቶ ቀሪዎቹን 7ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ ከተጋጣሚው መከላከያ በ1 ነጥብ ዝቅ ብሎ በ14 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ አ/አ ላይ ተገናኝተው ጨዋታቸውን 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።
ከመከላከያ በኩል ረጅም ጉዳት ላይ የነበሩት አዲሱ ተስፋዬ እና ቴዎድሮስ በቀለ አሁንም በጉዳት ምክንያት የዛሬው ጨዋታ የሚያልፋቸው ሲሆን ከኢትዮ-ኤሌክትሪክ በኩል ካሉሻ አልሀሰን በጉዳት የማይሰለፍ ይሆናል።
10:00 ሲል አ/አ ስታዲየም ላይ የሚካሄደውን ጨዋታ ኢ/ዳኛ ሀ/የሱስ ባዘዘው የሚመሩት ይሆናል።