በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በአልገዛም ባይነቱ የተጋድሎ ዘመን አይረሴ የሆነ አንፀባራቂ ታሪክ በመስራት ፈር ቀዳጅ መሆኑን ያረጋገጠው አንጋፋው የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ይዞት የተጓዘውን ሁለንተናዊ የበላይነት አጠናክሮ ለመቀጠል ከመቻሉም በላይ ወደ ላቀ ልዕልና ከፍ ለማለት የበቃበት ስኬት ላይ ለመድረስ መቻሉን እንደ ታላቅ ድል ልታነሳው የምትሻ መሆኑን በአክብሮት የምትገልፀው ሀትሪክ… ይህ አንጋፋ ክለብ በዛሬው እለት የሚያስመርቀውን የእግር ኳስ አካዳሚ በማስመልከት የተሰማትን ልባዊ ደስታ በማስተላለፍ መላው የክለቡን ቤተሰቦችና የአገራቸው እግር ኳስ የለውጥ ጅማሮ ደስ የሚያሰኛቸውን የአገራችን ህዝቦች ሁሉ እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት የምትሻ መሆኗን በታላቅ አክብሮት ለመግለፅ ትወዳለች፡፡
ወራሪው የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በፋሽስታዊ መዳፉ ውስጥ ለማስገባት የጦር አዋጁን አስነግሮ እንቅስቃሴ በጀመረበት ወቅት አገር የማዳን ስልት ይዞ ኪነታዊ የቅስቀሳ ተግባር ለመፈፀም ታስቦ በታላላቅ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመው አንጋፋው የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገር ፍቅር ማህበር (የሀገር ፍቅር ትያትር) በተመሠረተበትና የአርበኝነት ተጋድሎ ማካሄድ በጀመረበት ሰሞን በአራዳ ሰፈር ታዳጊዎች የተመሰረተው የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ገና ከጅማሬው የገጠመው እጅግ የሆነ መራር ጉዞ ሳይበትነው ከቀን ወደ ቀን በሚገጥሙት ፈተናዎች እየተጠናከረ ዛሬ ለደረሰበት የደመቀ ታሪክ የበቃው ከምስረታው አንስቶ በተሰባሰቡት ታዳጊዎች የዓላማ ፅናትና ገና በጅማሬው ማለዳ ክለቡን የመምራት ኃላፊነቱን በተረከቡ ታላላቅና የተከበሩ ኢትዮጵያውያን አርበኞች አርቆ አስተዋይነት እንደሆነ ታሪክ የማይዘነጋው እውነታ እንደሆነ የስፖርት ቤተሰቡ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው የምታምነው ሀትሪክ… ይህ አንጋፋ ክለብ የተመሠረተበትን የታሪክ እርሾ ከውስጡ አሟጦ በማስወጣት ታሪክ አልባ በሆነ ትውልድ ሳይሆን የአያት ቅድመ አያት ታሪክ ወራሽ በሆነው የዛሬ ትውልድ ተጠብቆ ለመጓዝ መቻሉ በየአመቱ በሚያስመዘግባቸው ውጤቶቹ ብቻ ሣይሆን በትክክለኛው የመዋቅር ተክለ ስብዕናው ተጠብቆና ተከብሮ እንዲጓዝ ያበቃው መሆኑን ለማረጋገጥ ትወዳለች፡፡
በምስረታው የመጀመሪያው አመታት አገሪቱ በገጠማት የፋሽስት ጣሊያን ወረራ የተነሣ ወደ መራር እጣ ፈንታ ውስጥ ለመግባት የተገደደው አንጋፋው የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በአምስቱ የወረራ አመታት ከጣሊያን ወራሪ ቡድኖች ጋር በመጫወት በሠላማዊው መድረክ ድል እያደረገ አርበኞች የመሃል አዲስ አበባ ህዝብ በደስታው ብዛት እየዘመረ አገሩንና ነፃነቱን ማስከበር የሚችልበት አቅም እንዳለው የሚያምንበትን የሥነ-ልቦና ጥንካሬ የበለጠ ማዳበር የሚችልበትን እድል ለመፍጠር መብቃቱ ተደጋግሞ መታየቱን ከታሪክ ድርሳናት የተረዳችው ሀትሪክ… በዱር በገደል የሚገኙ ጀግኖች አርበኞችም በክለቡ ድል መቺነት በመበርታት ጥይት ተኩሰውና ጠላትን ገጥመው ግዳይ ጥለው ማደራቸው ክለቡ ከእግር ኳስ ስፖርት ባሻገር በነፃነቱ የአርበኝነት ትግል ላይ ወደር የሌለውና የማይናቅ ተጋድሎ ለመፈፀም እንደቻለ በገሃድ የሚያሳይ ሆኖ መቀመጡን በአክብሮት ታወሳለች፡፡
- ማሰታውቂያ -
ኪነትና እግር ኳስ የአምስቱ አመታት የነፃነት ተጋድሎ የትግል ስልቶች ጣምራ ጦሮች ሆነው መጓዛቸው በተጨበጠ መልኩ በታየባቸው በእነዚያ የወረራ አመታት ውስጥ አንጋፋው የሀገር ፍቅር ትያትርና ታላቁ የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት በክለብ የፈፀሟቸው ጀብዱዎች በታሪክ ድርሳናት በክብር ተፅፈው የተቀመጡ መሆናቸውን የምታምነው ሀትሪክ…በተለይ የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት ክበብ ከአምስቱ አመታት የጠላት ወረራ በኋላ በአገሪቱ በተለያዩ ወቅት መንግሥታዊ አመራሩን በተቆናጠጡ አካላትና አመራሮች ልዩ ልዩ አቋሞች የተነሣ የቅርፅና የሊግ ለውጥ እየተደረገበት ደብዛው እንዲጠፋ ለማድረግ የተካሄደበትን ጥረት ተቋቁሞና ራሱን ጠብቆ በቁርጠኝነት አሁን ለደረሰበት ልዕልና ለመብቃት የቻለ መሆኑ የክለቡንና በተከታታይነት የነበሩ ስመ ጥርና አንጋፋ አመራሮች አርቆ አሳቢነት የተሞላበትን ዘመን አይሽሬ ራዕይ የሚያሳይ መሆኑን ታረጋግጣለች፡፡
ባለፉት ሰማንያ አመታት ባደረጋቸው ጉዞዎች ከገጠማቸው ፈታኝና ሞጋች ውጣ ውረዶች ባሻገር እጅግ አስደሳችና ማራኪ ጉዞዎችን ለመጓዝ የበቃው ይህ አንጋፋ የስፖርት ክለብ በአገሪቱ የእግር ኳስ መዋቅር በተካሄዱት ልዩ ልዩ የሊግ ውድድሮች ላይ ከማንኛውም ክለብ በላይ የላቀ ውጤት ከማስመዝገቡ ባሻገር ከ1990 ጀምሮ በአዲስ መልክ በተዋቀረው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላይ በመጀመሪያው አመት ሳይሳተፍ በተሳትፎ በቁጥር በአንድ ከሚበልጡት ክለቦች በላይ በመጓዝ የአስራ ሶስት ዋንጫዎች አሸናፊ ለመሆን መብቃቱ በአገሪቱ የእግር ኳስ ተሳትፎ ውስጥ ማንም የማይደርስበት ውጤት ላይ ለመቀመጥ የቻለበትን እውነታ በተጨባጭ ማሳየቱን የምትረዳው ሀትሪክ.. ክለቡ አገሪቱን ወክሎ በተወዳደረባቸው አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ መጓዝ የሚገባውን ጉዞ ለማሳየት አለመቻሉ ከአገር ውስጥ ስኬቱ ባሻገር በኢንተርናሽናል ውድድሮች ላይ ለመድገም የሚችልበትን ጥንካሬ መገንት የሚገባው መኑን ተደጋግሞ የተነገረ ታሪካዊ ድክመት ሆኖ መዝለቁ ሊገታ የሚችልበትን ስራ ሰርቶ ማሳየት እንደሚጠበቅበት ትጠቁማለች፡፡
አንጋፋው ክለብ በአገር ውስጥ እግር ኳስ እድገት ላይ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ራሱን ከማጠናከር ባሻግር ሌሎች ክለቦች የሚገጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ ተደጋጋሚ ድጋፍ ከማድረጉ ባሻገር የክለቡ የቅርብ ሰው የሆኑ ባለሃብቶች ለብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኝ ቅጥር እንዲያካሄዱና ለተጨዋቾች ተደጋጋሚ ሽልማትና የሕክምና ወጪ በመሸፈን ስፖርቱን ወደ ውጤት ለማምጣት ብርቱ እገዛ ለማድረግ መቻላቸው ተደጋግሞ የተገለፀ መሆኑን የምታስታውሰው ሀትሪክ… የግሉን ስታዲየም ለመገንባት እንቅስቃሴ ጀምሮ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለመዘግየት መቻሉ ቢታመንም በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ የላቀ ሚና ሊጫወት እንደሚችል የሚታመንበትን የታዳጊዎች የእግር ኳስ አካዳሚን አሰርቶ ዛሬ ለማስመረቅ መቻሉ ከክለቡ የምንጊዜም ስኬት በላይ ተደርጎ የሚቆጠር መሆኑን ልትጠቁም ትወዳለች፡፡
አጋፋው የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የደረሰበት የላቀ አቅምና ዛሬ የሚያስመርቀው የታዳጊዎች የእግር ኳስ አካዳሚ ለዚህ ታላቅ ክለብ ብቻ ሣይሆን ለአሪቱ እግር ኳስ የተበረከተ ታሪካዊ ቡራኬ እንደሆነ መላው የስፖርት ቤተሰብ ይረዳዋል ብላ የምታምነው ሀትሪክ.. ይህ በእግር ኳሳችን ላይ የፈነጠቀው አዲስ የማለዳ ጀንበር ለክለቡ ቤተሰቦች ብቻ ሣይሆን ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ዜጎች በሙሉ የሚሰጠው ደስታ የላቀ እንደሆነ ጠንቅቃ ትረዳለች፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ የዘመናት ውጣ ውረድ ያሳዘናቸው ኢትዮጵያውያዊያን በሙሉ በታላቁ አፍሪካዊ የእግር ኳስ አመራር በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ስም የተሰየመው “ይድነቃቸው ተሰማ የወጣቶች የእግር ኳስ አካዳሚ” መገንባቱ የሚሰጠውን ጥቅምና የሚያመጣውን ለውጥ ስታነሳ የዛሬውን የምርቃት እለት የተለየ አድርጎ ቢያስብ የሚደንቅ እንደሆነ የምትረዳው ሀትሪክ… በአገሪቱ እግር ኳስ ውስጥ ፈር ቀዳጅ የሆነው ይህ አንጋፋ ክለብ አሁንም በፈር ቀዳጅነቱ በመጓዝ ታላቅ ታሪክ ያስመዘገበበት የዛሬው እለት ለመብቃት መቻሉን ታደንቃለች፡፡
የኢትዮጵ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዉ መንግሥት ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ለጋሹ ባለሀብት ሼህ ሞሀመድ አሊ አልአሙዲ፣ ሌሎችም ታላላቅ ባለስልጣናት እንዲሁም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ሊ/መንበር የሆኑት ኢሳ ሃያቱና የኮንፌዴሬሽኑ ሌሎች ባለስልጣናት፤ እንዲሁም ሮጀር ሚላን ጨምሮ ታዋቂ የአህጉሪቱ የስፖርት ሰዎችና በርካታ ታላላቅ እንግዶችና የሚዲያ አካላት በተገኙበት በዛሬው እለት በደመቀ ስነ ስርዓት የሚመረቀው ይሄው የታዳጊዎች የእግር ኳስ አካዳሚ በቢሾፍቱ ከተማ በ24 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ተንጣሎ የተሰራ መሆኑን ለማረጋገጥ የበቃችው ሀትሪክ… ይህ በውስጡ ሁለት ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የመጫወቻ ሜዳዎችን ጨምሮ የመመገቢያ አዳራሽ፣ የመልበሻ ክፍሎች፣ ዘመናዊ የህክምና ማዕከል፣ ጂምናዚየምና ቤተመጽሐፍት ያካተተው አካዳሚ እጅግ ውብና ዘመናዊ በሆነ መልኩ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብቶ መጠናቀቁ ታውቋል፡፡
በአገሪቱ በክለብ ንብረትነት ደረጃ ሲሰራ የመጀመሪያው የሆነው የእግር ኳስ አካዳሚ እውን ይሆን ዘንድ የክለቡ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆኑት አቶ አብነት ገ/መስቀል የተጫወቱት የላቀ ሚና በታሪክ ድርሳን ተደጋግሞ የሚጠቀስ መሆኑን የምታምነው ሀትሪክ.. እኚህ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ይህ አካዳሚ እውን ይሆን ዘንድ በአስተባባሪነትና በእውቀትም ሆነ በገንዘብ ከእስከ የማይባል ድጋፍ በማበርከት ረገድ የፈፀሙት የላቀ ድርሳናቸው ዘመን አይሽሬ ወደ ሆነ ደረጃ ከፍ ለማድረግ መብቃቱን ታረጋግጣለች፡፡
የእግር ኳስ አካዳሚው እጅግ ዘመናዊ በሆነ መልኩ ተሰርቶ ወደ አገልግሎት መግባቱ የመላውን ኢትዮጵያዊያን ፍላጎት እውን ለማድረግ ወሳኝ ጥቅም እንደሚሰጥ ማንም ወገን በተጨበጠ መልኩ ይረዳዋል ብላ የምታምነው ሀትሪክ… ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች በዚህ መሰል ዘመናዊ የስልጠና ማዕከል ማለፋቸው የእግር ኳስን ሀሁ ገና በማለዳው የሚማሩበትን የስለጠነ መንገድ ተግባራዊ ስለሚያደርግ ለእግር ኳሳችን እንደ መልካም ትንሳኤ ሊቆጠር የሚገባው መሆኑን ትረዳለች፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ የታዳጊዎች የእግር ኳስ አካዳሚ በዛሬው ዕለት በደመቀ ስነ ስርዓት በሚመረቅበት ወቅት እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ተሳታፊ በመሆን በመጀመሪያው ዙር ግጥሚያ የሲሸልሱን ኮትዲኦር ገጥሞ በደርሶ መልስ 5ለ0 በሆነ ውጤት ለማሸነፍ የቻለው የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በቀጣዩ ጨዋታ ወደ ኮንጎ ብራዛቪል በመጓዝ ተጋጣሚው የሆነውን የሊዮፓርድስ ክለብን በሜዳው 1ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ለመመለስ
መቻሉ ክለቡ በኢንተርናሽናል ውድድር ላይ የነበረውን ደካማ ውጤት ለመቀልበስ ምን ያህል ቁርጠኛ አቋም እንደያዘ የሚያረጋግጥ መሆኑን የምትረዳው ሀትሪክ… ታላቁ ክለብ በመልሱ ጨዋታ ያስመዘገበውን ውጤት አስጠብቆ ለመውጣት መዘናጋትን በፍፁም ሊቀበለው እንደማይገባ በማሳሰብ በጥንቃቄ ላይ የተመሠረተ አጨዋወትን ተግባራዊ ማድረግ የሚጠበቅበት መሆኑን ትገልፃለች፡፡
በአህጉር አቀፍ ውድድር ላይ በቻምፒየንስ ሊጉ ወደ ምድብ ማጣሪያ አልፎ የማያውቀው የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት
ክለብ የራሱንም ሆነ የአገሪቱን የእግር ኳስ ታሪክ ለመለወጥ የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ለአገሪቱ እግር ኳስ
ተሳትፎ ሌላ ተጨማሪ ግብአት እንደሚሆን የምታምነው ሀትሪክ… ይህ አንጋፋ ክለብ ወደ ምድብ ድልድሉ በመግባት
አዲስ ታሪክ ለመክፈት ከቻለ 550 ሺህ ዶላር ሽልማት ለማግኘት መቻሉ ተጨማሪ ስኬት ከመሆኑ በላይ ብራዛቪል
ላይ የተገኘው ድል ዛሬ ለሚካሄደው የታዳጊዎች እግር ኳስ አካዳሚውና የምርቃት ስነ ስርዓት እጥፍ ድርብ የሆነ
ድምቀትና ግርማ ሞገስ እንደሚሰጠው በጨዋታ መላውን የክለቡን ቤተሰቦችና ኢትዮጵያውያንን በሙሉ በተገኙት
ስኬቶች የተሰማትን ደስታ መነሻ በማድረግ እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት ትሻለች፡፡