በመሸሻ ወልዴ
የቅ/ጊዮርጊሱ ስኬታማው የተከላካይ
ስፍራ ተጨዋች አስቻለው ታመነ
በዝውውር መስኮቱ ለመጪዎቹ
ሁለት ዓመታት ለቡድኑ ለመጫወት
ፊርማውን አኑሯል፤ አስቻለው በእዚህ
ጊዜ የተጨዋችነት ቆይታውም ክለቡን
ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ለመጥቀምም
መዘጋጀቱን ይናገራል፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋች ከሆነበት ጊዜ
ጀምሮ በየጨዋታው ጥሩ ብቃቱን በማሳየት
በደጋፊዎቹ ዘንድ የሚወደደው ይኸው
ተጨዋች በክረምቱ ወራት የውል ጊዜው
መጠናቀቁን ታሳቢ በማድረግ ወደ ተለያዩ
ክለቦች ያመራል የሚል ዜና ተናፍሶ የነበረ
ቢሆንም ተጨዋቹ እኔ ለፕሮፌሽናል
ተጨዋችነት ወደ ውጪ ካላመራው በስተቀር
ወደየትም አልሄድም፤ የምጫወተውም ለቅ/
ጊዮርጊስ እና ለቅ/ጊዮርጊስ ብቻ ነው ያለበትን
ምላሹን አሁን ላይ ለቡድኑ በመፈረም
ሊያረጋግጥ ችሏል፡፡
የቅ/ጊዮርጊሱ አስቻለው ታመነ ለቡድኑ
ፊርማውን ከማኖሩ በፊት ለፕሮፌሽናል
ተጨዋችነት ወደ ግብፅ ያመራል ተብሎ
ቢጠበቅም ከደመወዝና ከጥቅማ ጥቅም ጋር
በተያያዘ ለመስማማት ባለመቻል ጉዞውን
መሰረዙንና እዚሁ ለቅ/ጊዮርጊስ ለመጫወትም
ፍላጎት ማሳደሩን ገልፆልናል፤ ከዚሁ
ተጨዋች ጋር ለክለቡ ፊርማውን ስለማኖሩና
ሌሎችን አጠር ያሉ ጥያቄዎችን አንስተንለት
በሚከተለው መልኩ ምላሹን ሰጥቶናል፡፡
ሀትሪክ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ ለመጫወት
ዘግይተህም ቢሆን ፊርማህን አኑረሃል፤ ወደ
ሌላ ክለብ ልታመራ አስበህ ነበር?
- ማሰታውቂያ -
አስቻለው፡- በፍፁም፤ አሁንም ደግሜ
መናገር እፈልጋለሁ፤ በፕሮፌሽናል
ተጨዋችነት ወደ ውጪ ሀገር ካላመራሁ
በስተቀር መጫወት የምፈልገው ለቅ/ጊዮርጊስና
ለቅ/ጊዮርጊስ ብቻ ነው፤ ያ ስለሆነም የውጪው
ጉዞ ስላልተሳካልኝ ጥሩ ጊዜን ላሳለፍኩበት
ክለቤ ለሁለት ዓመት ለመጫወት ፊርማዬን
አኑሪያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ወደ ውጪ ሀገር ወደየት
ልታመራ ነበር ያሰብከው?
አስቻለው፡- የፕሮፌሽናል እግር ኳስ
ተጨዋች ለመሆን ወደውጪ ላመራ
የነበርኩበት ሀገር ግብፅ ነበረች፤ እዛ
ለመሄድና ለመጫወትም ከኤጀንቴ ጋር በብዙ
ጉዳዮች ዙሪያ ተነጋግረንም ነበር፤ በኋላ
ላይ ግን በደመወዝ ክፍያና ጥቅማ ጥቅም
ልንስማማ ስላልቻልን ጉዞዬን ልሰርዘው
ችያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ወደ ግብፅ ልታመራ የነበርክባቸው
ክለቦች እነማን ናቸው? በደመወዝ ክፍያው
ዙርያስ ያልተስማማችሁባቸው ሂደቶችስ ምን
መልክ ያላቸው ናቸው?
አስቻለው፡- ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች
እየተጫወቱ ባለበት የግብፅ ሊግ በመሄድ
ልጫወትባቸው የነበርኩባቸውን ክለቦች እኔ
ላውቅ ባልችልም ኤጀንቴ ግን ሊወስደኝ
ያሰበባቸው ቡድኖች ነበሩ፤ ከእሱ ጋር
ስንነጋገርም አንተ ለመጫወት ፈቃደኛ ሁን፤
ተስማማ እንጂ ክለቦቹን እነግርሃለሁ ብሎኝም
ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በደመወዝ ክፍያው ዙሪያ
እነሱ በመጀመሪያው ዓመት በሁለተኛው
ዓመት እንደዚሁም ደግሞ በሶስተኛው ዓመት
ሊሰጡኝ ያሰቡት ክፍያ በጣም አነስተኛ እና
እዚህ ሀገር ከሚከፈለው ደመወዝ አኳያም
ያነሰ በመሆኑ እዚሁ ለቅ/ጊዮርጊስ ልጫወት
ፊርማዬን ማኖር ችያለው፡፡
ሀትሪክ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ ለመጫወት
ውልህን አራዝመሃል፤ ዘንድሮ ከአንተ ምን
ይጠበቅ?
አስቻለው፡- በቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ
ባለኝ የተጨዋችነት ቆይታዬ ሁሌም ቢሆን
በሜዳ ላይ ራሴን ብቁ ተጨዋች አድርጌ
ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረትን የማደርግ
ተጨዋች ስለሆንኩ የእዚህ ዓመትም ላይ
ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቡድኔን ልጠቅመው
እና ውጤታማም ላደርገው ዝግጁ ሆኛለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- የቅ/ጊዮርጊስን የእዚህ ዓመት
የተጨዋቾች ስብስብ በምን መልኩ ነው
የምትገልፀው? በውድድር ዘመኑስ ምን
ውጤትን ትጠብቃለህ?
አስቻለው፡- የቅ/ጊዮርጊስን የተጨዋቾች
ስብስብ በተመለከተ በአሁን ሰዓት የምናገረው
ክለባችን ውስጥ ያሉት ነባር ተጨዋቾችም
ሆኑ በዝውውር መስኮቱ ያስፈረምናቸው
ተጨዋቾች ጥሩ ችሎታና ብቃት ያላቸው
መሆኑ ነው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ እነዚህ
ተጨዋቾችም በቡድኑ ውስጥ በሚኖራቸው
ቆይታም አንድ ታሪክን መስራት የሚፈልጉ
መሆናቸውን የተረዳንበት ሁኔታም አለና
በዚህ ቡድን ሙሉ እምነት አለኝ፤ የውድድር
ዘመኑ ላይ ልናመጣ ያሰብነው ውጤት ደግሞ
ቅ/ጊዮርጊስ ሁሌም ቢሆን የሚጫወተው
ለሻምፒዮናነትና ለአንደኝነት ነው ይህን የድል
ውጤት ለማግኘትም ከፍተኛ መስዋትነትን
እንከፍላለን፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ……?
አስቻለው፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስን
በተመለከተ በእዚህ ዓመት ኳሳችን በሰላም
ተጀምሮ በሰላም የሚጠናቀቅበትን ነገር ብናይ
በጣም ደስ ይለኛል፤ ለእዚህ ደግሞ የሁሉም
ክለቦች ደጋፊና የደጋፊዎች ማህበራት ጥልቅ
ስራን ሊሰሩ ይገባልና ፈጣሪ ለሁሉም ነገር
ይርዳን እላለሁ፡፡