በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ 16 ቡድኖች የሚሳተፉበት የምድብ ድልድል ውስጥ በመግባት የመጀመሪያ የሆነው ቅ.ጊዮርጊስ ትናንት እሁድ አ.አ ላይ ከዲ.ሪ.ኮንጎው ኤስ. ቪታ ላይ ጣፋጭ ሶስት ነጥብን በመንጠቁ ወደ ቀጣዩ ዙር (ስምንት ውስጥ)የመግባት ተስፋውን አለምልሞታል።
በ2017ቱ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ በምድብ c ከቱኒዚያው ኤስፔራንስ፣ከደ.አፍሪካው ማማሎዲ ሰንዳውንስና ከዲ.ሪ.ኮንጎው ኤስ ቪታ ጋር የተደለደለው ቅ.ጊዮርጊስ የምድቡን ሶስተኛ ጨዋታ ትናንት ከቀኑ በ10:00 ሠዓት በአ.አ ስታዲየም ከኤስ ቪታ ጋር አድርጎ የቡድኑ ግብ አዳኝ የሆነው ሳላህዲን ሠይድ በ60ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ሶስት ነጥብ በማግኘቱ ከምድቡ ሁለተኛ ሆኖ የማለፍ ተስፋው እንዲሰፋ አድርጎታል።
ባለ ሜዳው ቅ.ጊዮርጊስ እና እንግዳው ኤስ ቪታ የመጀመሪያውን 45 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ምንም ግብ ያጠናቀቁ ሲሆን በርካታ የግብ ዕድሎችን የፈጠሩት ቅ.ጊዮርጊሶች ጥብቅ የመከላከል ታክቲክ ይዞ የገባው የቪታን የተከላካይ መስመር ጥሰው በመግባት ግብ ለማስቆጠር 60 ደቂቃዎችን መጠበቅ ግድ ሆኖባቸዋል።
የጨዋታው 60ኛ ደቂቃ ግን የቅ.ጊዮርጊሶች ተደጋጋሚ ግብ የማስቆጠር ጥረት ፍሬ ማፍራቱን ኤስ ቪታዎች ይዘውት የገቡት የመከላከል ስትራቴጂ መክሸፉን ያረጋገጠ ክስተት ተፈጠረ።
የቅ.ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ብ/ቡድን ግብ አይምሬ የሆነው 7 ቁጥር ለባሹ ሳላህዲን ሠይድ አልደፈር ብሎ 60 ደቂቃዎች ድረስ የተጋዘውን የቪታው ግብ ጠባቂ ኔልሰን ሉኮንጎ ሶንግማንን መረብ በመድፈር የቅ.ጊዮርጊስን አሸናፊነት ያወጀች ግብ ተቆጠረች።
ይህቺ ለቅ.ጊዮርጊሶች ከማሸነፉ በዘለለ ስምንት ውስጥ በመግባት ሌላ አዲስ ታሪክ የመስራት ዕድሉ ከፊታቸው ሰለመኖሩ ጥቆማ ከመስጠትዋ በተጨማሪ ግባን ያስቆጠረው ሳላህዲን ሠይድም ከኮከብ ጎል አግቢነት ፉክክሩ ውስጥ እንዳልወጣ ይልቁንም ለኮከብ ጎል አግቢነት የተያያዘውን ሩጫ በ6 ጎል አጠናክሮ መቀጠሉን ያረጋገጠች ወርቃማ ጎል ሆና ተገኝታለች።
ቅ.ጊዮርጊስ የትናንቱን ጨዋታ በድል በማጠናቀቁ ሰባት ነጥብ ካለው ኤስፔራንስ በሁለት ዝቅ ብሎ በአምስት ነጥብ ምድቡን በሁለተኛነት እየተከተለ ሲሆን በኤስፔራንስ በሜዳው 2ለ1 የተሸነፈው ማማሎዲ ሰንዳውንስ በሶስት እንዲሁም ኤስ ቪታ ያለ ምንም ነጥብ በሶስተኛና በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር 16ቡድኖች የሚገኙበት የምድብ ድልድል ውስጥ በመግባት አዲስ ታሪክ ያፃፈዉ ቅ.ጊዮርጊስ ሌላ ወርቃማ ታሪክ የሚያፅፍበት ዕድል በእጁ ላይ ያለ ሲሆን ከምድቡ ሁለተኛ ሆኖ ስምንት ውስጥ ለመግባት የፈታችን ጁላይ 1 ቀን የደ.አፍሪካውን ሰንዳውስን አ.አበባ ላይ ማሸነፍ ከቻለ ለሌላ አዲስ ታሪክ በጣም የሚቃረብበት ዕድል ይፈጠራል።
ቅ.ጊዮርጊስ በሜዳው ከኤስ ቪታ ላይ ጣፋጭ ሶስት ነጥብ በማግኘቱ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋውን አለመለመ፤ሳላህዲን ሠይድ የቅ.ጊዮርጊስ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን ቀጥሎበታል
Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.