ቅዳሜ ዕለት ሊደረግ የነበረው እና በብሔር ብሔረሰቦች በዓል ምክንያት ወደዛሬ የተዛወረው የሁለተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንድ ጨዋታ ዛሬ ተደርጓል።
አዲስ አበባ ላይ ሰበታ ከተማን ያስተናገደው ቅ/ጊዮርጊስ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በውድድር አመቱ የመጀመሪያውን 3ነጥብ ማስመዝገብ ችሏል። በመጀመሪያው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅ/ጊዮርጊስ ወደ ወልቂጤ አቅንቶ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያለግብ አቻ የተለያየ ሲሆን ሰበታ ከተማ በአንፃሩ ሜዳው ላይ ወልዋሎ አ.ዩ. አስተናግዶ 3-1 መሸነፉ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች የዛሬውን ጨዋታ የመጀመሪያ 3ነጥብ ለማግኘት የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ በጉጉት ተጠብቆ ነበር።
በጨዋታው ቅ/ጊዮርጊስ የጨዋታውን ብቸኛ ግብ ለማግኘት 69 ደቂቃዎችን መጠበቅ ግድ ሆኖበት ነበር። 69ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አጥቂ አቤል ያለው ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ መሆን ችላለች። በጨዋታውም አንድ የማይጠበቅ ነገር የተከሰተ ሲሆን ይህም በተለምዶ ካታንጋ በሚባለው ቦታ ለብሔር ብሔረሰቦች በዓል ተተክሎ የነበረ የእንጨት ርብራብ ባለማንሳቱ የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ተራርቀው ሊቀመጡ ተገደዋል። ይህ ጉዳይ የነገውም ጨዋታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳርፍ ከወዲሁ ጥንቃቄ መደረግ አለበት።
- ማሰታውቂያ -
ውጤቱንም ተከትሎ ቅ/ጊዮርጊስ የውድድር አመቱን የመጀመሪያ 3ነጥብ ማሳካት የቻለ ሲሆን ሰበታ ከተማ ደግሞ ሁለተኛ ሽንፈቱ ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህም መሰረት ቅ/ጊዮርጊስ በ4 ነጥብ እና በ1 ንጹሕ ግብ 6ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሰበታ ከተማ በአንፃሩ ያለምንም ነጥብ እና በ3 የግብ እዳ 15ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ተገዷል።
ሊጉን ሁለቱንም ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለውና በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው ወልዋሎ አ.ዩ. በ6 ነጥብ እና በ3 ንጹሕ ግብ መሪነቱን ሲይዝ ፋሲል ከነማ፣ ሐዋሳ ከተማ፣ ባህርዳር ከተማ፣ አዳማ ከተማ እና ቅ/ጊዮርጊስ በእኩል 4ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከ2ኛ እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ኢትዮጵያ ቡና፣ ሰበታ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያለምንም ነጥብ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። የፋሲል ከተማው ሙጂብ ቃሲም እና የወልዋሎ አ.ዩ. ሰመረ ሐፍተይ በእኩል 3ግቦች የኮከብ ግብ አግቢነቱን ሲመሩ ሽመክት ጉግሳ፣ ካርሎስ ዳምጠው፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ አዲስ ግደይ እና ዲዲየር ሊብሬ በእኩል 2ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
ሊጉ ነገ ረቡዕ ሲቀጥል 11:00 ሲል ኢትዮጵያ ቡና ከጅማ አባጅፋር ጋር ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስቴዲየም የሚያደርግ ይሆናል።