“ለሰባት ወር ፈታኝና መራራ የጎዳና ህይወትን መርቻለሁ
ሰባት ጊዜም ወድቄያለሁ በስምንተኛው ግን እነሳለሁ”
ጌታሁን መንግስቱ
(የቀድሞ የኢት. ብ/ቡድን ተጨዋች)
- ማሰታውቂያ -
ለዛሬው ማንነቱ በር ስለከፈተለት
ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካና የመጀመሪያው
ክለቡ ሰለሆነው መድን፦ኢንስትራክተር
ካሳሁን ተካ ጌታሁን መንግስቱ በእግር ኳሱ
ውስጥ እነዲፈጠር ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል፤
ካሳሁን ተጨዋች በሚመለምልበት ሶስተኛው
አይኑ ከሰፈር ጨዋታ አይቶ ባይወጣኝ ኖሮ
ጌታሁን የሚባለው ስም በእግር ኳሱ መንደር
አይታወቅም ነበር። መድኖች ሁሌም ለክረምት
ዝግጅት ወንጂ ይመጡ ነበር፡፡ በዛን ቀን
ደግሞ እኛ የሰፈር ጨዋታ ስናደርግ ካሳሁንን
ጨምሮ መድኖች ቆመው ይመለከቱን ነበር፡፡
በዚህ ጨዋታ ጥሩ ከመንቀሳቀስ አልፌ በባዶ
እግሬ ሹቶችን ከሩቅ እየመታሁ በተደጋጋሚ
ግብ ሳስቆጥር ተጨዋቾችን መንጥቆ
የሚያወጣው የካሳሁን አይን እኔ ላይ አረፈ፡
፡ ወዲያውኑም “ይሄንን ልጅ ያዙልኝ፤ትልቅ
ደረጃ አደርሰዋለሁ፤ የአገር ስም የሚያስጠራ
ተጨዋች አደርገዋለሁ” አላቸው፡፡“ በጀት
የለንም” ሲሉት “ከእኔ ደሞዝም ቢሆን ቁረጡ
እንጂ ያዙልኝ” አለ በዚህ የተነሳ ወደ መድን
መጣሁ አንድ አመት እየተማርኩ ምግብ
እየተመገብኩ ቆየሁ በቀጣይ አመት የመድን
ንብረት ሆንኩ፡፡
–በመድን ማሊያ የመጀመሪያ ጨዋታው
ያስቆጠራቸው ግቦችና “የስቴድየሙን ፓውዛ
ቀና ብለህ እንዳታይ ስለመባሉ፦እንስትራክተር
ካሳሁን ተካ ባልኩህ መንገድ መልምሎኝ
በአመቱ ከክለቡ ጋር ተለያየ፤ እሱ ሲወጣ አሁን
ወልዋሎ አዲግራትን ሲያሰለጥን የነበረው
ብርሃኔ ገ/እግዚአብሄር መድንን ተረከበ፤
ቡድኑ ከመብራት ኃይል ጋር የምሽት ጨዋታ
ሲያደርግ ብርሃኔ በተጠባባቂ ተጨዋችነት
ያዘኝ፡፡ መድን እስከ እረፍት 2ለ0 ይመራ
ነበር፤ገና ተጠባባቂ ከመሆኔ ቡድኑ ሊሸነፍ
በማለት ተቆጨሁ፤ እድለኛም አይደለሁም
አልኩ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳለሁ አሰልጣኙ
እኔን እያየ “ተነስና ቀይር” አለኝ እኔ ግን
ይሄ ሊሆን ይችላል ብዬ ስላለመንኩ ከኋላዬ
ሰው ሳይኖር ወደኋላ ዞሬ ተመለከትኩ፡፡
በዚህን ጊዜ ብርሃኔ በስጨት ብሎ “አንተን
እኮ ነው የምናገረው፤ ተነስና ቀይር” ብሎ
ሲነግረኝ አሁንም ባለማመን ድንብርብሬ
ወጣና እ… እኔን… ነው… አልኩት ብርሃኔም
“አዎን አንተን ነው፤ ምነው ኣለመንክም
እንዴ?” ሲለኝ በሙሉ ተጨዋቾች ሳቁብኝ፤
እንደተባለውም አሟሟቅኩና ተቀይሬ ገባሁ፡
፡ ብርሃኔ ወደ ሜዳ ልገባ ስል “የስቴድየሙን
ፓውዛ ቀና ብለህ እንዳታይ፤ መብራቱ ብዥታ
ይፈጥርብሃል፤ ይዞርብሃም” ብሎ ስለመከረኝ
ፍራንክ እንደጠፋበት ሰው ቀና ሳልል መሬት
መሬቱን እያየሁ ተቀይሬ ገባሁ፤ ሜዳ
እንደገባሁ እንደ ፍሬሽ ተጨዋች ሳይሆን
ልምድ እንዳለው ተጨዋች ነበር ስንቀሳቀስ
የነበረው፤ ጉልበት፣ ታሪክ የመስራት ጉጉቱ
ስለነበረኝ መብራቶችን በጣም አስቸገርኳቸው፤
ብቻ ምን አለፋህ ከእረፍት በኋላ ተቀይሬ
ገብቼ ባስቆጠርኳቸው ሶስት ጎሎች 2ለ0
ሲመራ የነበረው መድን 3ለ2 አሸነፈ እኔም
ሀትሪክ ሰራሁ፡፡ ይህ ጨዋታ ለቀጣይ
ህይወቴም ትልቅ በር ከፈተልኝ፡፡
–መብራት ኃይል ላይ በመጀመሪያ
ጨዋታው ሶስት ጎል ማስቆጠሩ ይዞለት
የመጣው አገርን የመወከል እድል፦በእግር
ኳስ ህይወቴ የመጀመሪያ የሆነው ከመብራት
ሃይል ጋር ያደረግነው ጨዋታ በእለቱ
አድናቆትና ሙገሳ ብቻ ሳይሆን ሌላም
ያልታሰበ ትልቅ ሲሳይ ይዞ ብቅ አለ፤
በህልሜም ሆነ በዕውኔ አስቤ የማላውቀውን
አገር የመወከል እድል፡፡ ከመብራት ኃይል
ጋር በነበረው ጨዋታ ተቀይሬ ስገባ የታዳጊ
ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበረው ሰውነት
ቢሻውም በእረፍት ወደ ሜዳ ይገባል፤ እሱ
ሲገባ እኔ በጣም ጥሩ ተንቀሳቅሼ ሶሰት ጎል
ሳገባ ይመለከተና “ይሄ ልጅ የት ነበር? ከየት
ነው የመጣው?” ብሎ ወዲያውኑ ታዳጊ
ብሄራዊ ቡድኑኑ እንድቀላቀል ይወስናል፡፡
እኔ ይሄንን አላውቅም ጨዋታውን
ጨርሼ ወደ መልበሻ ቤት ስገባ
አቶ ዲባባ ቦሩ የሚባሉ የክለቡ
ኃላፊ የነበሩ ይመጡና “ጌታሁን
ወደ ካምፕ እንዳትሄድ፤ ከእኔ
ጋር የምትሄደው” ይሉኝና
በመኪናቸው ይዘውኝ ይሄዳሉ፡
፡ የት ነው የሚወስዱኝ?
በጨዋታው ተደስተው ሊጋብዙኝ
ነው? እያልኩ ሳሰላስል “ጌታሁን
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሸው ለታዳጊ
ብሄራዊ ቡድን ስለመረጠህ ሆቴል
ግባ ተብለህ ነው” ሲሉኝ ማመን
አልቻልኩም፡፡ ታዳጊ ብሄራዊ
ቡድኑን በዚህ ሁኔታ ተቀላቀልኩ፤
በጣም የሚገርምህ ከታዳጊ ቡድኑ
ጋር አብሮ ስስራ የነበረ ተጨዋች
ተቀንሶ እኔም ከቡድኑ ጋር በታሪክ
ለመጀመሪያ ጊዜ አገሬን ለመወከል
ወደ ሞዛምቢክ ሄድኩ፡፡
–ለእውቅና ካበቃው መድን
ወደ ኢትዮጵያ ቡና ስላደረገው
ዝውውር፦ በአጭር ጊዜ ውስጥ
የብዙ አሰልጣኞች ትኩረት
ሆንኩ፤ በመድንና በታዳጊ
ብሄራዊ ቡድን የማደርጋቸው
እንቅስቃሴዎች የፈላጊዬን
ቁጥር አበዙት፡፡ በተለይ ለታዳጊ
ብሄራዊ ቡድን እየተጫወትኩ
ባለበት ሰአት ኢትዮጵያ ቡናዎች
ከመድን ሊያስኮበልሉኝ ጠይቁኝ፤
እኔም በልጅነቴ የኢትዮጵያ ቡና
ደጋፊ ስለነበርኩና በጨዋታቸው
ስለምደሰት እንዲሁም በዚያ
በሚያምር ደጋፊ ታጅቦ መጫወትን
ስለተመኘሁ አሰልጣኝ ስዩም አባተና
እንዳንድ ደጋፊዎች ሆቴል ድረስ
መጥተው ሲያነጋግሩኝ ለአፍታም
አላመነታሁም እሺ ግን ከአርጀንቲና
ስመለስ አልኳቸው፤እነሱም
“ከአርጀንቲና ስትመለሱ ኤርፖርት
እጠብቅሃለን” አሉኝ፤ በጣም
የሚገርምህ ከአርጀንቲና ስንመለስ
ያልጠበቅኩት ነገር ነበር የገጠመኝ፡
፡ በአንድ በኩል የቡና፤ በሌላ
ወገን የጊዮርጊስ ደጋፊዎች እኔን
ለማነጋገር ጠበቁኝ፡፡ በመሃል የኢትዮጵያ
ቡና ደጋፊዎች ይዘውኝ ሄዱ፤ ከእነሱ ጋር
ተስማምቼ ለቡና ፈረምኩ፡፡ የቡና አገባቤ
እንደዚህ ነው፡፡
–ለኢትዮጵያ ቡና ሲጫወት ተቀይረህ
ውጣ ሲባል እምቢ ስላለበት አጋጣሚ፦ከላይ
በገልፅኩልህ መሰረት ቡና ገባሁ፤ ከቡናዎች
ጋር የተስማማሁት 10 ሺህ የፊርማ ገንዘብ
ሊሰጡኝ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው 10
ሺህ ብር የዛሬ 2 ሚሊየን ብር ማለት ነው፡፡
ቡናዋች ለፊርማ ብለው ቃል የገቡልኝ ገንዘብ
ብትጠብቅ ደጋግሜ ሰጡኝ እንጂ ብዬ ብጠይቅ
መልስ የሚሰጠኝ ሰው አጣሁ በዚህም በጣም
ተበሳጨሁ፡፡ ከፍተኛ ጭቅጭቅም ተፈጠረ፤
የመጫወት ፍላጎቴም በጣም ቀነሰ፡፡ በዚህ
መጥፎ ስሜት ውስጥ እያለሁ እሁድ ቀን
ከትግራዩ ጉና ጋር የ8 ሰአት ጨዋታ ነበረን፡፡
የጨዋታው አሰላለፋ ውስጥ ስዩም ሊያስገባኝ
እንደሆነ ስለተረዳሁ ለስዩም ቅሬታዬን
ለመግለፅ ዛሬ እንዳታሰልፈኝ መጫወት
አልፈልግም አልኩት በዚህ ጊዜ እሱም “አንተ
ነህ አሰልጣኙ እኔ? ወደህ ሳይሆን በግድህ
ትጫወታለህ” አለኝ፡፡ እንዳለውም አሰላለፍ
ውስጥ አስገባኝ አማራጭ አልነበረኝም ደስተኛ
ሳልሆን ገባሁ፤ በዚህ የተነሳም እንቅስቃሴዬ
ጥረ ስላልነበረ ተቀይሬ እንድወጣ ተጠየቁ፤
በዚህን ጊዜ አልወጣም አልኩ ተጨዋቾችም
ዳኛውም እንድወጣ ቢወተውቱኝም ቢጮሁም
አልወጣም አልኩ፡፡ በከፍተኛ ተቃውሞ ውስጥ
ሆኜ 90ውን ደቂቃ ጨርሼ ወጣሁ፡፡ በወቅቱ
ያደረግኩት ድርጊት አግባብ እንዳልሆነ
ውስጤ ቢያውቅም ቢያንስ በዚህ ምክንያት
ደጋፊውም ሚዲያውም አልወጣም ያለበት
ምክንያት ምንድ ነው? ብለው ሲጠይቁ
የደረሰብኝ ነገር ይፋ ይወጣል ብዬ ሆን ብዬ
ያደረግኩት ነገር ነበር፡፡ በዚህ ውሳኔዬ ግን
10 ሺህ ብሬን ከማግኘቴ ይልቅ በድርጊቴ
የተበሳጩት የክለቡ አመራሮች ይባስ ብለው
ለስድስት ወራት ከማንኛውም የእግር ኳስ
እንቅስቃሴ ታግደሃል ብለው ከቡድኑ ውጪ
አደረጉኝ፡፡
–እራሱን ለማጥፋት በረኪና ስለመጠጣቱ፡
– ከላይ እንዳልኩህ 10 ሺህ ብሬን አገኛለሁ
ብዬ የሰራሁት ሂሣብ ሌላ ያልታሰበ መዘዝ ይ
ዞብኝ መጣ፡፡ ብሬንም ተከልክዬ እንደገና 6
ወር ከምወደው እግር ኳስ ውጪ ሁን ተብዬ
ቅጣት ሲጣልብኝ በጣም ተበሳጨሁ፡፡ ሰማይና
ምድሩ ዞረብኝ፡፡ ሕይወቴን ጨለማ ሲወርሰው
ታየኝ፡፡ በአጭሩ እራሴን መቆጣጠር አቃተኝ፡
፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለው በአይምሮዬ
የመጣው አንድ ነገር ምንድነው… “ገንዘቤንም
አጥቼ፤ ሰርቼም እንዳልበላ ተደርጌ በሕይወት
ከምኖር ለምን በረኪና ጠጥቼ እራሴን አጥፍቼ
አልገላገልም” ብዬ ከእራሴ ጋር አወራሁ፡
፡ በዚህን ጊዜ አንድ የማላውቀው መንፈስ
“ትክክል ነህ፤ እራስህን አጥፋ አጥፋ አለኝ
ደጋግሞ” እኔም አላመነታሁም፡፡ በረኪና
አንስቼ ግጥም አደረኩ፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነውን
አላስታውሰውም፡፡ በወሬ ደረጃ ሲነግሩኝ ግን
አንድነት የሚባለው የክለባችን ተጨዋች ዕቃ
እረስቶ ወደ ካምፓችን ሲመለስ እኔ መሬት
ላይ ተዘርሬ አረፋ ስደፍቅ አይቶ በጣም
በመደንገጡ “ኧረ… ጌታሁን… ሞተ…” ብሎ
በጩኸት ግቢውን ሲያቀልጠው ተጨዋቾቹ
ከሰርቪስ፣ ሰራተኞቹ ከያሉበት ተሯሩጠው
መጥተው ከወደኩበት አፋፍሰው በሰርቪስ
ወደ ሰናይ ክሊኒክ ወሰዱኝ፡፡ የጠጣሁት
በረኪና በሰውነቴ ውስጥ ሳይሰራጭ ሕክምና
በማግኘቴ ተረፍኩ እንጂ ይሄኔ ጌታሁን
ታሪክ ሆኖ ይቀር ነበር፡፡ በወቅቱ የገጠመኝ
ነገር ከባድ እንደሆነ የምታውቀው እራሴን
ስቼ ብዙ ጊዜ መቆየቴ እና ለአንድ ወር
ተኝቼ መታከሜ ነው፡፡ ትዕግስት በማጣቴና
ባለማገናዘቤ እራሴን ለማጥፋት የሞከርኩበት
በመጥፎ የማነሰው አጋጣሚ ነው፡፡
–በጨዋታ ዘመኑ ከማን ጋር መጫወት
ይቀለዋል ?ማን ይመቸዋል?፦ከመድኑ
ሐሰን በሽር ጋር…! ብዙዎች ከሐሰን ባህሪና
ዝምተኛነት አንፃር ምርጫዬ ሊገርማቸው
ይችላል ከሐሰን ጋር ስጫወት ግን እግር ኳስ
ይቀለኛል፡፡
–አብሮት ባለመጫወቱ በጣም
የሚቆጨው፦ሰለሞን (ልምጭ)…! ብዙ
ያልተዘመረለት በጣም ጨዋና ትልቅ አቅም
ያለው ተጨዋች ስለነበር የቅጣት ምት
ኤክስፐርት ከሆነው ሰለሞን (ልምጭ) ጋር
አንድ ቀን አብሬው ባለመጫወቴ በጣም
እቆጫለሁ፡፡ አምላክ የጨዋታ ዘመኔን
ምኞት አይቶ ነው መሰል አሁን በስተርጅና
በሾላ የጤና ስፖርት ክለብ ውስጥ አብረን
የመጫወት እድል በማግኘቴ ምኞቴን
በመጨረሻ ሰአትም ቢሆን አሳክቻለሁ፡፡
–በጨዋታ ዘመኑ አላንቀሳቅስ፣
አላፈናፍን ብሎ ሲያስቸግረው ስለነበረው
ተጨዋች፦አንዋር ሲራጅ (ትንሹ)…!አንዋር
ሲራጅ አትታለል፣ አትሸውድ፣ አልፈሃት
አትሄድ በቃ የሆነች
የማትለቅ በዚህ ስትላት
በዚያ የምትመጣ በጣም
ስታስቸግረኝ የኖረች
ተጨዋች ናት፡፡ አንዋር
ካለች የማደርገው ሁሉ
ይጠፋብኝ ነበር፤ በጣም
ምርጥና ብልጥ ተከላካይ
መሆንዋ የፈለኩትን
እንዳላደርግ ታስቸግረኝ
ነበር፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ
ምርጥ ግብ፦መድን እያለሁ
ከኢትዮዽያ ቡና ጋር
ስንጫወት የግብ ጠባቂው
አሊ ረዲን መውጣት አይቼ
ከርቀት መትቼ ያገባኋት
ለእኔ ምርጥ ግብ ናት፤
በዚህች ጎል ማሸነፋችን
ብቻ ሳይሆን የቡደናችን
አሰልጣኝ የነበረው
መንግስቱ ወርቁ ወደ ላይ
አንስቶ በማቀፍ ያደነቀኝ
ግብ ናት፤ መንግስቱ
ወርቁን በሚያክል ትልቅ
አሰልጣኝ በዚህ ደረጃ
መሞገስን አስበኸዋል?
–የጨዋታ ዘመኔ
ምርጥ አሰልጣኝ
ብሎ ቅድሚያ
የሚሰጠው፦ የሚ ገርም ህ
በጨዋታ ዘመኔ በትንሹ
ከ14 በላይ አሰልጣኞች
አ ሰ ል ጥ ነ ው ኛ ል ፤
የውጪ ዜጋ ነው ብለህ
ካልተቀየምከኝ የእኔ
የምንጊዜም ምርጡ
አሰልጣኝ ጋርዚያቶ ነው፤
ዜጋ እንዳልሆነ አውቃለሁ፤
ለእኔ ግን በስልጠናው
በሰራው ሰራ ከዜጋ
በላይ ነውና ጋርዚያቶን
ምርጡ አሰልጣኝ ብዬ
አስቀድማለሁ፡፡ በእግር
ኳስ የምናውቀው ጌታሁን
መንግስቱን የነገን ገምቶ
ከሰፈር ጨዋታ ላይ መርጦ ለዛሬ ማንነቴ
ያበቃኝ የአባቴ ያሀል የማየው ካሳሁን
ተካ ሌላው በእግር ኳስ ህይወቴ ምርጡ
አሰልጣኝና ትልቅ ቦታ የምሰጠው ሰው ነው፡
፡ ካሳሁን በልጅነቴ እኔን መመልመል ብቻ
ሳይሆን “ይሄንን ልጅ ያዙልኝ ትልቅ ቦታ
አደርሰዋለሁ፤ ለአገር የሚጠቅም ልጅም
አደርገዋለሁ” ብሎ እርግጠኝነት በተሞላበት
ስሜት የተናገረው ካሳሁን ካምፕ ገብቶ
ምግብ ይመገብ ትምህርቱንም ይማር ሲል
ኮሚቴዎች የበጀት ችግር አለ ሲሉት እንኳን
በእኔ ከመተማመኑ የተነሳ “ከደሞዜም ቢሆን
ቁረጡ፤ ይሄ ልጅ ግን ይያዝልኝ ትልቅ ቦታ
አደርሰዋለሁ” ብሎ የተማመነብኝ ሌላው
የጨዋታ ዘመኔ ምርጡ አሰልጣኝ ነው፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ተጨዋች ብሎ
ቅድሚያ የሚሰጠው፦አሸናፊ ግርማን…! ከአሹ
ጋር አብሬ ተጫውቻለሁ፤አብሬው ልምምድ
ስለሰራሁ አቅሙን በቅርበት አውቀዋለሁ፡፡
ከዘህ አንፃር የምርጥ ተጨዋችነት ምርጫዬን
ከእሱ ውጪ ለማንም አልሰጥም፡፡
–በችሎታው እያደነቀው ስላደገው
ተጨዋች፦አሰግድ ተስፋዬ…! “አሴ… ጎል…
ጎል” እየተባለ ደጋፊውን የማያሳፍር ጎል
የሚያገባ ተጨዋች አጋጥሞህ ያውቃል? ለእኔ
ከአሰግድ ውጪ አጋጥሞኝ አያውቅም፤አምላክ
ነፍሱን በገነት ያኑረው አሴን በጣም እያደነቅኩ
ነው ያደግኩት፡፡
ከአገር ውጪ የሚደግፈው ቡድን፦ማንቸስተር
ዩናይትድ
በአሰለጣጠኑና በውጤታማነቱ ቀልቡን
በመሳቡ የሚያደንቀው አሰልጣኝ፦ጆሴ
ሞውሪንሆ…! አሁን በማን.ዩናይትድ ያለው
ሳይሆን በቼልሲ የነበረው ውጤታማውና ጥሩ
ቡድን የገነባው ሞውሪንሆ
–ከውጪ የሚያደንቀውና የሚደግፈው ብሄራዊ
ቡድን፦የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን
–ከባህር ማዶ በአጨዋወቱ ቀልቡን የማረከው፤
የሚያደንቀው ምርጡ ተጨዋች፦ቲዮሪ ኦንሪ!
ለእሱ በጣም የተለየ ቦታ አለኝ፡፡
–እድሉን ባገኝና ለአንድ ደቂቃም ቢሆን
ባገኘውና ባወራው ብሎ የሚመኘው ታዋቂ
ተጨዋች፦ከተጨዋቾች ቲዮሪ ኦንሪ ፤
ከአሰልጣኞች ደግሞ ሰር አሌክስ ፈርጉሰንን
አግኝቼ የስኬታማነታቸውን ምስጢር
ባወራቸው ደስ ይለኝ ነበር፡፡
–በጨዋታ ዘመኑ በጣም ስለተደሰተበት
አጋጣሚ፦የተለያዩ ደስታዎችን በተለያየ ጊዜ
አጣጥሜያለሁ፤ የበለጠ ቦታና የተለየ ክብደት
የምሰጣቸው ግን ወደ ሶስት ለሚጠጉት ነው፡
፡ አንደኛው በባዶ እግሬ ስጫወት ከሰፈር
ጨዋታ ላይ በኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ
ተመርጬ ለመጀመሪያ ጊዜ የመድንን ማሊያ
ለብሼ ከእረፍት በኋላ እንድጫወት በአሰልጣኝ
ብርሃኔ ገ/እግዚአብሄር እድል ተሰጥቶኝ
በመብራት ሃይል 2ለ0 ሲመራ የነበረው
መድን እኔ ከእረፍት በኋላ ባስቆጠርኳቸው
3 ግቦች 3ለ2 አሸንፈን የወጣንበትና ሀትሪክ
የሰራሁበት የመጀመሪያው ጨዋታዬ ሲሆን
ሁለተኛው በዚህ ጨዋታ በአሰልጣኝ ሰውነት
ቢሻው ለታዳጊ ቡድን ተመርጬ ለጨዋታ
ወደ ውጪ የሄድኩበት ሌላውና ትልቁ ደስታ
ያጣጣምኩበት ደግሞ ዛሬም ድረስ እንደ ትልቅ
ታሪክና ስኬት የሚነሳው የአርጀንቲናው
የአለም ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ አገርን
እስከመወከል መድረሴ በወቅቱ ከተያዙት 14
እና 15 አጥቂዎች ውሰጥ ከተመረጡት ሶስት
አጥቂዎች አንዱ ሆኜ የዚህ ትልቅ ታሪክ
አካል መሆኔ በጨዋታ ዘመኔ ካገኘኋቸው
የማይዘነጉ ደስታዎች ውሰጥ የሚጠቀሱ
ናቸው፡፡
–በእግር ኳስ ህይወቱ በሐዘን ልቡ
የተሰበረበትና በጣም ስላዘነበት አጋጣሚ፦በዚህ
በኩል ሁሌም እንደ ሐዘን የማነሳው ከመድን
ወደ ኢትዮጵያ ቡና ስሄድ የተፈጠረው
አጋጣሚ ነው፤ መድኖች ኮሚቴው፣
ተጨዋቾች ብቻ ሳይሆን ሰራተኛው
ሳይቀር ከቢሮ ወጥቶ “እባክህ ክለቡን ለቀህ
አትሂድብን” እያሉ ለምነውኝ ልመናቸውን
ረግጬ ስኬትንና ድልን አገኛለሁ ብዬ ወደ
ኢት.ቡና ሄጄ የኢት.ቡና ቆይታዬ እንዳሰብኩት
ሳይሆን ቀርቶ በተለያዩ ችግሮች ተተብትቦ በ7
ወራት ብቻ መገደቡ ሁሌም በሐዘንና በመጥፎ
አጋጣሚነት የማነሳው ገጠመኝ ነው”
–በኢትዮጰያ እግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያ
ሆኖ ስለተመዘገበው የአርጀንቲናዊ የአለም
ወጣቶች ሻምፒዮና፦የአርጀንቲናው የአለም
ወጣቶች ሻምፒዮና በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ
የተሳተፍንበት አጋጣሚ በቀላሉ የማይዘነጋ
ዛሬም ድረስ እንደ አዲስ የሚወራ በወርቅ
ቀለም የተፃፈ ደማቅ ታሪካችን ነው፤ እንኳን
በእኛ በተጫዋቾች በሁሉም ኢትዮዽያዊያን
አእምሮ ታትሞ የእግር ኳሳችን ትልቁ ታሪክ
ነው።
ስለነበረው ቡድናችን ጋዜጦች ብዙ ፅፈዋል፣
አሰልጣኞች ብለዋል፣ ህዝቡም በግልፅ አድናቆቱን
ሰጥቷል፡፡ የዚህ ምክንያቱ አንደኛው ቀልቡን
የሚገዛው የቡድኑ አጨዋወት ሲሆን ሁለተኛው
ደግሞ መልካችንም አጨዋወታችንም ወደ
ብራዚል በመጠጋቱና ኢትዮጵያ የምትባለውን
አገር በእግር ኳስ በዚህ ደረጃ አለመጠበቃቸው
ይመስለኛል፡፡ ብዙዎች ኢትዮጵያ የምትባለዋን
አገር በእነ ሃይሌ፣ደራርቱ ቱሉ በሩጫ እንጂ
በእግር ኳስ አያውቋትም ይሄ ግርምት
የፈጠረባቸው ይመስለኛል፡፡ በወቅቱ የሆላንድ
ብሄራዊ ቡድን የቀድምው የማንቸስተር ዩናይት
ድአሰልጣኝ የሆኑት ቫን ሃል በቡድናችን
አጨዋወት ከመገረም አልፈው የተወሰኑ
ተጨዋቾችን ለመውሰድ እስከማነጋገር የደረሱበት
ሁኔታ ሁሉ ነበር፡፡ በአጭሩ ቡድናችን በቡድንም
በግልም ባሳየው አጨዋወት የአድናቆት መአት
ነበር የወረደበት፡፡
–የኢትዮጰያ ብሄራዊ ቡድን የተደነቀው
ከልጆቹ ጋር ተጫውቶ ነው ፂም እየላጩ
እድሜ አጭበርብረው ነው ስለመባሉ፦እድሜ
ማጭበርበር የሚባለው ነገር አይነካካንም ብዬ
አልዋሽህም፡፡ ያንስ ይሆን ወይም ይበዛ እንደሆነ
እንጂ የትኛውም ብሄራዊ ቡድን ጋር ብትሄድ
ከእድሜ ማጭበርበር የፀዳ ቡድን አታገኝም፡
፡ የሆላንድ፣የኢኳዶርና የኮስታሪካ ቡድኖችን
ብትወስድ የእድሜ ማጭበርበር መጠኑ ይነስ
እንጂ አለ፡፡ ወደ እኛ ስትመጣም ተመሳሳይ
ነገር ነው ያለው፤ ሁለት ሶስት ሰው ይኖራል
ይሄን መካድ አልፈልግም፡፡ ሁሉም የቡድኑን
አባላት ግን በዚህ ደረጃ መፈረጅ ግን ስህተት
ነው። ለምሶሌ እኔን ብትወስድ እድሜዬን ጠብቄ
ነው የመጣሁት፤ ፂም መላጨት ላልከውም
የላጩ አይጠፉም (እየሳቀ)፤ አንዴ እንደውም
ምን ተፈጠረ መሰለህ አንዱ ስሙን የማልነግርህ
ተጨዋች ፂሙ ወዲያው ወዲያው እያደገ
ሽማግሌ እንዳስመሰለው አሰልጣኝ ሰውነት
ቢሻው ያይና “እስቲ ከተለወጥክ ሂድና ፂምህን
ተላጭተህ ና” ይለዋል፡፡ ተጨዋቹም ሄዶ
ተላጭቶ ሲመጣ ሰውነት ያየውና “የባሰ ተፎገርክ
ባትላጨው ይሻልህ ነበር” ያለውና የሳቅነው ሳቅ
አይረሳኝም ፤እኔን ባይመለከተኝም ፂም እየላጩ
የሚገቡ ተጨዋቾች አልነበሩም ብዬ አልዋሽም፡፡
–የሆላንዶቹ ቫንፐርሲና ሮበን ዛሬም ድረስ
በትልቅ ሊግና ትልቅ ቡድን ውስጥ እየተጫወቱ
የእኛዎቹ ከዛሬ አምስት አመት በፊት ጫማ
መስቀላቸውና በሌላ ሙያ ውስጥ መገኘተቸው
የእድሜ ልዩነቱ በጣም ሰፊ ስለመሆኑ አያሳይም
በሚል ስለተነሳለት ጥያቄ፦አዎን አኛ ካቆምን
ዘርፍ ከቀየርን ቆይተናል፤ እነ ቫንፐርሲ፣
ሮበን ሳቪዬላና አሌከሳንደር በትልቅ ክለብ
ውስጥ በቋሚነት እየተጫወቱ ነው ይሄ ሊገርም
አይገባም፡፡ ቫንፔርሲ ወይም ሮበን ማነው?
ጌታሁን፣ዮርዳኖስና አሸናፊስ እነማን ናቸው?
እንዴት ነው ኳስ ተጨዋች የሆኑት? ከየትና
እንዴት ነው የመጡት? ብለህ ስትጠይቅ
መልሱን ታገኛለህ፡፡ እነ ቫንፔርሲ ትክከለኛውን
የእግር ኳስ ስርአት ጠብቀው በአካዳሚ ውስጥ
በብዙ ባለሙያዎች ተለፍቶባቸው ነው የመጡት፡
፡ እኛ ግን በድንገት በቅለን በድንገት ኳስ
ተጨዋቾች ነው የሆነው፡፡ አካዳሚ የሚባለውን
ስሙን እንኳን መስማት የጀመርነው ገና አሁን
ነው፤ ምስጋና ለሰውነት ቢሻውና ለአሰግድ
አካዳሚ የሚባል ነገር የት እናውቃለን? እነሱ
ግን በእድሜያቸው በትክክለኛው መንገድ
ከመምጣታቸው ውጪ ራሳቸውን ጠብቀው
በባለሙያ ተከበውና ታግዘው ነው የሚጫወቱት፤
የእድሜ ልዩነት እንዳለ ባልክድም የሚመጡበት
መንገድ በራሱ ብዙ አመት በብቃት እንዲጫወቱ
ያደርጋቸዋል፡፡ እኔን ብትወስድ ካሳሁን ከሰፈር
አወጣኝ መድን ገባሁ፤ በዚያው በአንድ ጨዋታ
ለታዳጊ ተመረጥኩ ቀጥሎ ለወጣት እያልኩ
ነው እድገቴን ጠብቄ ያደግኩት፡፡ ሁሉም ግን
በዚህ መንገድ መጥቷል? ጥያቄ ያስነሳል፤
ለሲ በ22፣ለቢ ደግሞ በ25 ወደ ዋናው ቡድን
ሲያድጉ እድሜያቸውን ታች ጨርሰው በ30 ነው
የሚገቡት፡፡ ይሄ ትልቅ ልዩነት ያመጣል፤ እኛን
ከእነሱ ጋር ማነፃፀርም ከባድ ነው። አርጀንቲና
እያለን አካዳሚዎችን የማየት እድል አግኝቻለሁ፤
ከ600 ሺህ በላይ ታዳጊዎች ናቸው በየአካዳሚው
የሚሰለጥኑት፡፡ ከዚህ ውስጥ የሚወጡ ናቸው
በየእድሜ ካታጎሪ ያለውን ብሄራዊ ቡድን
የሚያገለግሉት፡፡
–የአርጀንቲና ነገር ሲነሳ አርጀንቲናዊያን
ቆነጃጅት በኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች ፍቅር
ስለመውደቃቸው፦እውነት ለመናገር ከጨዋታው
ውጪ አርጀንቲናን በፍቅር እንድናነሳት
ብቻ ሳይሆን በፍቅር እንድንወዳት ያደረጉ
አርጀንቲናዊያን ቆነጃጅት መሆናቸው አይካድም፡
፡ ምክንያቱን በትክክል ባለውቅም አርጀንቲናዊያን
ሴቶች በጣም ይወዱን በፍቅር ያብዱልን ነበር፡፡
ምን አልባት በሰአቱ የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድኑ
ቶፕ ደረጃ ላይ የደረሰበት ወቅት በመሆኑና
ይሄንን ተከትሎም ተጨዋቾቹ እንደ እንቁ ይታዩ
ሰለነበር እኛንም በዚያ ደረጃ አይተውን ይሁን
አሊያ መልካችን ከብራዚላዊያን ጋር ተመሰሳይ
ስለሆነ በዚያ አይን አይተውን ይሁን አላውቅም
በጣም ወደውን አላስቆም አላስቀምጥ ብለውን
ነበር፡፡ ለማጋነን ወይም ለጉራ ሳይሆን በተለይ እኔ
መከራዬን ነበር ሳይ የነበረው፤ አርጀንቲናዊያን
ቆነጃጅት አላስቆም አላስቀምጥ ብለውኝ ነበር፡
፡ በተለይ አንደኛዋ አንድ ቀን ሆቶል ድረስ
መጥታ አስጠርታኝ መኪና ውስጥ ግባ ካለችኝ
በኃላ መኪናውን ቆላልፋ ይዛኝ እስከከመጥፋት
የደረሰችበትን፤ ለምን አግብተኸኝ እዚሁ ቀርተህ
ከእኔ ጋር አትኖርም ብላ ያስጨነቀችን ጊዜ
አልረሳውም፡፡
–ጌታሁን ከአርጀንቲናዊ ፍቅረኛው አንድ
ልጅ አለው ተብሎ ስለተወራውና እስከዛሬ
ስለተደበቀው ምስጢር፦ከየት አመጣኸው…?
ከተጨዋቾቹ ጋር እኮ ይሄ ምስጢር እንዳይወጣ
ተማምለን ነበር፤ (በጣም እየሳቀ) የሚገርም
ነው፡፡ እንግዲህ ከደረስክበት የተደበቀ ምስጢሬን
አሁን ላውጣ፤ መውጪያ መግቢያ አይደለም
መተንፈሻ ካሳጣችኝ አርጀንቲናዊት ቆንጆ
የ11 አመት ልጅ ወልጃለሁ፤ እዛ ለጨዋታ
በሄድንበት ጊዜ በመጀመሪያው የጦፈ የፍቅር
ግንኙነት አርግዛብኝ አንድ ጎረምሳ አፍርተናል፡፡
አርጀንቲናን ለቅቄ ስመጣ በጣም ብዙ ችግር ነበር
የገጠመኝ፤ “አትሄድም… ከእኔም… ከልጃችን ጋር
አብረን እዚሁ በፍቅር እንኑር” ብላ ጨቅጭቃኝ
በስንት ጦርነት ነበር የመጣሁት፡፡ እዚህ
ከመጣሁ በኋለም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በተለያየ
መንገድ ታገኘኝ ነበር፡፡ ስለልጄም ታወራኝ ነበር፡
፡ ያው እህል ውሃና ባህል አለያይቶናል እንጂ
የ14 አመት አርጀንቲናዊ ጎረምሳ አግኝቻለሁ፡
፡ በጣም የሚገርምህ ፈረንጆች ቁም ነገረኞች፣
የፍቅር ሰዎች መሆናቸውን የምታውቀው ዛሬም
ድረስ “አንድ ቀን መገናኘታችን አይቀርም” ብላ
ተስፋ አለመቁረጥዋ ነው፡፡ “ልጁ አንድ ቀን
አባቱን ፍለጋ ወደ አገርህ ይመጣል እናገኝሃለን”
ትለኛለች፡፡
–ወደ ኢትዮጵያ ውሰደኝ ስትለው “ወደ አገሬ
የምወስዳት ሸንኮራ አገዳ ላበላት ነው ወይስ
ምን ላበላት ነው ስለ ማለቱ፦“በአርጀንቲና እኔ
ያየሁትን ፈተና ማንም አላየውም፤ አሁን ልጅ
የወለደችልኝ አርጀንቲናዊ “አብረን እንኑር” ብላኝ
ሞክራ ሞክራ እንቢ ስላት “በቃ እሺ አብሬህ
ወደ ኢትዮጵያ ልሂድ፤ ከአንተ ጋር አብሬ ልኑር”
ስትለኝ ለጓደኞቼ ይህችን ሴትዮ ወደ አገሬ
የምወስዳት ወንጂ ወስጄ ሸንኮራ አገዳ ላበላት
ነው? ወይስ ምን ላበላት ነው? ብዬ ከችግሬ
የተነሳ ተናግሬያለሁ፡፡ የሚገርምህ እኔ ራሴ
እዛው ለመቀረትና አብሬያት ለመኖር አሰብኩና
በኋላ ውጣልኝ ብትለኝና በሰው አገር መንገድ ላይ
ብትወረውረኝስ ብዬ ነው ሃሳቤን የቀየርኩት እንጂ
እኔም በፍቅርዋ ከንፌ ልቀር ብዬ ነበር፤ እዚህ
ጥቁር እንኳን የሌለበት አገር ብዬ ግን ፈራሁ፡፡
ተጨዋቾችንም ያነሳሳሁት እኔ ነበርኩ፤እንደውም
ሃሳቤን ስቀየር “ምነው እንቅርና እዚሁ አግብተን
እንኑር ብለኸን” ብለው በጣም የወቀሱኝ ነበሩ፤
ግን የሚገርምህ በኋላ ላይ የእኛ ልጆች ላይ
የደረሰውን ስታይ ውሳኔዬ ልክ ነበር፤ ወደ አገር
ቤት ይዣት እንዳልመጣ ምን ላበላት? በምን
ላኖራት ነው? ብዬ ፈራሁ፡፡ ሸንኮራ አገዳ ላበላት
ነው? ያልኩት በዚህ የተነሳ ነው፡፡
–ስለ አሰልጣኝ ጋርዚያቶና ሰለ ስልጠናው፦
ጋርዚያቶ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በታሪክ
መዝገብ ስሙ እንዲሰፍር ያደረገ ትልቅ
ባለውለተኛ አሰልጣኝ ነው፤ ጋርዚያቶ ትውልዱ
ሌላ ደሙና ፍቅሩ ግን ከኢትዮጵያዊያን
የማይተናነስ ነው፡፡ ጋርዚያቶ ትልቅ አሰልጣኝ
ነው፤ ነገር ግን እዚህ አገር ያሉ አንዳንድ
አሰልጣኞችና የስፖርት ቤተሰቦች “አይችልም”
ይሉታል፡፡ ጋርዚያቶ ግን ይችላል፤ አይችልም
የሚሉትንም “ኑ ና እንማማር” ይላቸው እንደነበር
አስታውሳለሁ፡፡ በተለይ ስልጠናውን በተመለከተ
ብዙ የሚያወሩበትና የሚያጣጥሉበት ነበሩ፤ በእኛ
አገር ስላልተለመደ በእርግጥ ስልጠናው በጣም
ከባድ ነበር፡፡ ትጌይኒንግ ሰርቶ የማያስመልሰው፤
ተዝለፍልፎ የማይወድቅ ተጨዋች አልነበረም፡
፡ ያም ቢሆንም ግን ጥሩ ትንፋሽና ጉልበት
እንዲኖረን ጠንካራው ስልጠናው ጠቅሞናል፡፡
አይተህ ከሆነ አንድ 90 ደቂቃ አይደለም ሁለት
90 ደቂቃ መጫወት የሚያስችል ትንፋሽና
ጉልበት ነው የፈጠረልን በጠንካራው ልምምዱ፡፡
–የየመን የፕሮፌሽናልነት ቆይታውና
የኮከብ ተጨዋችነት ስኬቱ፦በጣም የሚገርምህ
በየመን በጣም ትንሽ የማይባል የጨዋታ
ጊዜን አሳልፌያለሁ ለሰባት አመታት በየመን
ሊግ ውስጥ ዋዳ ሰነዓ እና ሻማኩላ ክለቦች
ተጫውቻለሁ ብልህ ታምናለህ? ግን አድር
ጌዋለሁ፤ በየመን የሰባት አመት ቆይታዬ
ኢትዮጵያ ውሰጥ ሁለት ጊዜ በዮርዳኖስ አባይ
በአንድ ጎል ተበልጬ ያጣሁትን የኮከብ ግብ
አግቢነት ክብር አግኝቻለሁ፤ ሁለት ጊዜ የየመን
ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን የራሴንም
የአገሬንም ስም አስጠርቻለሁ፡፡
ብዙዎች ትናንት ጀግናችን ብለው
እንዳላወደሱኝ ፍቅራቸውን ያለስስት እንዳልሰጡኝ
ጎዳና ላይ በነበርኩበት ሰአት ሁሉም ሊባል
በሚችል መልኩ ፊታቸውን አዙረውብኛል፡፡ ይሄ
ነገር ከረሃቡም ከእርዛቱም በላይ ህመም ሆኖብኝ
ነው የቆየው፤ የስፖርት ዞን አዘጋጆች ሰይድና
መኳንንት በርሔ ጎዳና ላይ መውደቄን ይፋ
ካደረጉ በኋላ ከስፖርት ቤተሰቡ ትልቅ ምላሽ
ጠብቄ ነበር፡፡ እኔን ከዚህ ፈተናም ጎትተው
ያወጡኛል የሚል እምነቱም ነበረኝ፤ በሰይፉ
ፋንታሁን ሾው ላይ በድፍረት ያለሁበትን
ሁኔታ ከገለፅኩ በኋላም የነበረኝ ስሜት
ተመሳሳይ ነበር፡፡
ተጨዋች በአንድ ሙያ ውስጥ
ስላለን ዝምታን ይመርጣሉ ብዬ አላሰብኩም
በተለይ ተጨዋቾቹን፡፡ ከአንዋር ሲራጅ ትንሹ
ውጪ ድምፁን ያሰማ ተጨዋች አላጋጠመኝ፤
በዚህም ሞራሌ ተነክቷል፡፡ እኔ እንደእነሱ
የተከበርኩ የሚጨበጨልኝ ተጨዋች
ነበርኩ፤ዛሬ በወር ከ1000ሺ ብር በላይ የሚያገኙ
ተጨዋቾችና “የሙያ አጋራችን ነው፤ እኛ እነሱ
በዘረጉት መንገድ ነው እዚህ የደረሰነው” ብለው
አይዞህ ለማለት እንኳን አልሞከሩም፡፡ ይህ በጣም
አሳምሞኛል፡፡
–ስለትዳር ህይወቱና ለፈተና ስላደረገው
ጉዳይ፦እንደማንኛው ሰው የትዳር ህይወት
ነበረኝ፤ወልጄ ከብጄ ጥሩ ቤተሰብ የመመስረት
ጉጉቱ ስለነበረኝ ከፍቅረኛዬ ጋር በጋብቻ ተሳስረን
መኖር ጀምረን ነበር፡፡ የተሻለ ነገንለመፍጠርና
ጥሩ ትዳር እንዲኖረን በማሰብ ከባለቤቴ ጋር
በመመካከር እኔ ኳስ እየተጫወትኩ ከማገኘው
ገንዘብ እያጠራቀምን ባለቤቴ የተለያዩ ስራዎችን
እንድትሰራ በማሰብ ለፀጉር ስራ የሚረዱ
መሳሪያዎችን በመግዛት ፀጉር ቤት ከፈትን፤ እኔ
የመን እያለሁ በወር አንድ ሺህ ዶላር ይከፈለኛል፤
ሰባት አመት ሙሉ በወር የማገኘውን አንድ ሺህ
ዶላር በእሷ ሰም በተከፈተው አካውንት እየላኩ
እኔ በአበል፣ በኢንሴንቲቭና ጎል ሳገባ በማገኘው
ገንዘብ እያብቃቃሁ ነበር የምኖረው፡፡ ይሄን ሁሉ
ሳደርግ አንድ ነገር ይፈጠራል የሚል ጥርጣሬው
አልነበረኝም፤ በዚህ ሁኔታ ውሰጥ እያለን
አንድ ወያኔ ቶዮታ መኪና ነበረችኝ አንድ ቀን
በድንገት “መኪናው መሸጥ አለበት” አለችኝ እኔ
ደግሞ መኪናዋ ትጠቅመናለች ለምን ትሸጣለች?ስላት “ከቆርቆሮና ከእኔ ምረጥ” አለችኝ
እኔም ከአንቺማ ቆርቆሮ አይበልጥም ብያት
ፍላጎቷን ለማሟላት መኪናዋ ተሸጠች፡፡ ይሄ
ከሆነ በኃላ ሰው እንደሚጋጨው በመሃከላችን
ችግር ተፈጠረና ተጋጨን፡፡ እኔ መተሃራ
እህቶች ስላሉኝ በመሃል ወደዚያ ሄድኩ እዚያ
ደርሼ ስመለስ ያልገመትኩት ነገር ተከስቶ
አየሁ፤ ፀጉር ቤታችንም ሆነ ቤታችን ባዶ
ሆኖ አገኘሁት፡፡ ምን ተፈጥሮ ነው? ብዬ
ስጠይቅ መልስ የሚሰጠኝ አጣሁ፡፡ እሷስ የት
ሄደች? ብዬ ስጠይቅ አየኋት የሚል ጠፋ፤
በእቃው ብደነግጥም የእሷ መጥፋት ደግሞ
ምን ሆና ይሆን? በሚል በጣም አሳሰበኝ
መጨረሻ ላይ አገር ለቃ ወደ ጀርመን
መሄዷን ሲያረዱኝ ሰው የሞተበት ያህል
በቁሜ ክው ብዬ ቀረሁ፤በጣምም ደነገጥኩ፡፡
ድካሜ ልፋቴ ሁሉ መና ሲቀር ትዳሬ ሲበተን
በማየቴ በጣም ተበሳጨሁ፡፡ የሆነውን ሁሉ
አምኜ መቀበልና መቋቋም አቃተኝ፤ ተስፋ
መቁረጥና ብቸኝነት ወረረኝ፤ ከዚህ አጋጣሚ
በኋላ በተሻለ መስመር ላይ የነበረው ሀይወቴ
ምስቅልቅሉ ወጣ፤ ከመኖር ወደ አለመኖር
ተሸጋገርኩ”
–ለሰባት ወር የሞቀ ቤቱን ትቶ የጎዳና
ህይወት ስለመግፋቱ፦ከላይ እንዳልኩህ
ህይወቴ ተመሰቃቀለ፤ መኖር ሁሉ አሰጠላኝ፤
ሀብት ንብረቴን የምወደውን ትዳሬን ቤቴን
ሁሉ አጣሁ፤ የት ልውደቅ? ወና ቤት ውሰጥ
መኖርም አስፈራኝ፤ ወደ ቤተሰቦቼ ጋር
እንዳልሄድ በነበረኝ ጥሩ በሆንኩበት ሰአት
ዞር ብዬ ያላየኋቸው ቤተሰቦቼ ጋር እንዴት
ባዶ እጄን ችግሬን ይዤ ልሄድ? አዕምሮዬ
ይሄንን ማድረግና መቀበል አቃተው፤ መራራ
ቢሆንም የከፋ እንደሆነ ብረዳም ሰው ላይ
ሄጄ ከመውደቅ ጎዳና ላይ ብወድቅ ይሻላል
ብዬ ስቴድየም ጀርባ የሚገኝ ጎዳና ላይ ወድቄ
አስከፊ ህይወት መምራት ጀመርኩ፡፡ እንኳን
ለእኔ ለባለጉዳዩ ወሬውን ለሚሰማ ሰው እንኳን
የጎዳና ህይወት በጣም ከበድ ነው፤ እኔ ግን
ብርድና ፀሐይ እየተፈራረቀብኝ የለበስኩት
ልብስ መልኩን ቀይሮ በፌስታል የመጣ
ምግብ(ቡሌ) ከጎዳና ልጆች ጋር እየተሻማሁ
የሰባት አመት ያህል ከባድ የሆነውን ሰባት
ወር ካርቶን ላይ እየተኛሁ ገፋሁት፤ የመከራን
ገፈት መቅመስ ጀመርኩ፡፡ ለእንደ እኔ አይነቱ
በተሻለ ህይወት ውስጥ ለነበረ ሰው የጎዳና
ህይወት የሚቻል አልነበረም፤ እኔ ትናንት
በስፕሪንግ አልጋ ላይ ነበር ስተኛ የነበረው፤
ዛሬ ግን ካርቶን ላይ ነው የወደቅኩት፡፡
ሶስትና አራት ዲሽ ምግብ ደረጃቸውን በጠበቁ
ሆቴሎች እያማረጥኩ ነበር የምበላው፤ በ7
ወር የጎዳና ህይወቴ ግን በፌስታል የመጣ
ምግብ (ቡሌ) ነበር እየተሻማሁ ስበላ የነበረው፤
የጎዳና ህይወት ለጠላትህም አይስጠው፡፡ዛሬ
ግን እግዚአብሄር ይመስገን ከጎዳና ህይወት
ወጥቼ ደጋግ ሰዎችን እያስቸገርኩ በሆቴል
(አልቤርጎ)ውስጥ እየኖርኩ ነው።
–ከጎዳና ህይወት እንዲወጣ ስለተደረገው
ጥረት፦በጣም በሚያሳዝንህ ሁኔታ በ7 ወር
የጎዳና ህይወቴ ከገጠመኝ ረሃብና እርዛት
በላይ ሲርበኝ የነበረው የሰው ፍቅር ነው፤
እኔ ለአገሬ ትንሽም ነገር ትሁን የአቅሜን
ያበረከትኩ እግር ኳሱ እዚህ እንዲደርስ
የበኩሌን የተወጣሁ ሰው ነኝ ብዬ አስባለሁ፤
በዚህ ፈተናና አስቸጋሪ ህይወት ወቅት
ግን ከረሃቡ በላይ የጎዳኝ የሰው ፊት ነው፡
፡ የሰው ልጅ እያብላህ እያጠጣህ ለምን
የማይከፈልበትን ፈገግታውን ይነፍግሃል?
–ሰይፋ ፋንታሁን ሾው ላይ ከቀረበ
በኃላ ህይወቱ ተለውጧል ስለመባሉ፦ብዙ
ሰው እንዲህ እያለ እንደሚያወራ እኔም
እሰማለሁ፤ዕውነት ለመናገር ምንም ያገኘሁት
ነገር የለም፤ በእርግጥ በፕሮግራሙ ላይ
በዚህ በኩል ምንም ያገኘሁት ነገር የለም፡
፡ በርግጥ በፕሮግራሙ ላይ እንደታየው
ብዙ ነገር ቃል ተገብቶልኛል፡፡ ምናልባት
ቃል የገቡልኝ ሰዎች ስላልተመቻቸው ይሁን
በሌላ ምክንያት እስካሁን የተፈፀመልኝ ነገር
የለም፡፡ ያም ቢሆን ግን ሰዎች በመልካምነት
ተነሳስተው በሚዲያ በሰው ፊት የገቡት ቃል
በመሆኑ ቃላቸውን ሳያጥፋ ይፈፅሙልኛል ብዬ
ተሰፋ አደርጋለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች ይሃንን ሰምተው
እንደተለወጥኩ ገንዘቡን እንደማጠፋ ሁሉ
እንደሚወራ ይነግሩኛል፤ ሲያገኙኝ የሚያዩትና
የሚወራው ግራ ያጋባቸዋል፡፡ እኔ አሁንም
ህይወትን በሆቴል (አልቤርጎ) ውሰጥ እየገፋሁ
ነው፡፡
–ነገን በተስፋ እንዲኖር ከእግዚአብሄር
መልዕክተኛ ሆነው የመጡ ናቸው ስለሚላቸው
የሻላ ስፖርት ክለብ አባላት፦መቼም አንዳንድ
ጨካኝ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ በጣም አዛኝ ለሰው
ችግር በመድረሰ የሚረኩ ሰዎችም አሉ፤በዚህ
በኩል ደግሞ የጨለመው ህይወቴ ብርሃን
እንዲያገኝ ከእግዚአብሄር የተላኩ መልዕክተኞች
ሆነውልኝ የመጡት የሻላ ስፖርት ክለብ አባላት
ናቸው፤ እውነት ለመናገር ሻላዎች ከተሰፋ
መቁረጥ ውስጥ መንጭቀው በማውጣት ነገን
በተስፋ እንድኖር ነው ያደረጉኝ፤ ብዙ ሺህ ብር
ተከፍሎ የሚገባበት የስፖርት ማህበራቸው
ውስጥ “አንተማ የአገር ባለውለተኛ ነህ መውደቅ
የለብህም፤ አይዞህ ህይወት እንደዚህ ናት” ብለው
ሞራሌን ገንብተው በነፃ የቡድናቸው አባል
ከማድረጋቸው በተጨማሪ በሆቴል ውስጥ ሰዎችን
እያስቸገርኩ በመኖሬ በጣም አዝነው “አንተማ
ሆቴል አልቤሪጎ ውስጥ መኖር የለብህም፤
በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤት ተከራይተንልህ ሙሉ
እቃ አሟልተንልህ ትወጣለህ” የሚል ትልቅ
ተስፋ ሰጥተውኝ ቤት እያፈላለጉልኝ ነው፤
ከምንም በላይ በችግሬ ምክንያት ከሰው ሸሽቼ
ርቄ ከነበርኩበት ሰው መሃል ቀላቅለውኛል፡
፡ ከ10 አመት በኋላ ቁምጣ ለብሼ በመጫወት
ሌላ ህይወት እንድጀምርም አድርገውኛል፡፡
ውስጤ የነበረው ሃሳብና ጭንቀት ተስፋ መቁረጥ
በእነዚህ መልካም ሰዎች ተበትኗል፤ እኔ የሻለ
ስፖርት ክለብን ከተቀላቀልኩ በኂላ ላስበው
ስለማልፈልገው ነገ ማሰብ ጀምሬያለሁ፡፡ ልቤ
ከመነካቱ የተነሳ ሻለ ስፖርት ክለብን “ሻላ ውስጤ
ነው” እስከ ማለትም ደርሻለሁ፡፡ ድሮ ክለብ
ስጫወት ያላገኘሁትን ክብር፣ ፍቅር እንክብካቤ
ሻላዎች በመሰጠታቸው በጨለማ የተከበበ
የሚመስለው ህይወቴን ብርሃን አልብሰውታል፤
እነሱን በአንባቢ ስም ላመሰግናቸው
እወዳለሁ፤በጣም የሚገርምህ ሻላዎች በስፖርት
ክለቡ ውሰጥ ታቅፌ ከመጫወት በዘለለ ማህበራዊ
ህይወት ላይም በመሳተፍ የወገን ደራሽነትና
የደግነት ማሳያዎችም ናቸው፤ በርካታ ህፃናትን
ይደግፋሉ፤ ትምህርት ቤት የሚያሰሩ ደጋግና
መልካም ሰዎች የተሰበሰቡበት ነውና እነሱ ነገን
በተሰፋ አሻግሬ እንድመለከት ስላደረጉኝ እከሌ
ከእከሌ ሳልል ሁሉንም ከልብ አመሰግናቸዋለሁ፡፡
–በችግሩ ወቅት ስለታዘበው፦ የሰው ልጅ
ተነስቶ ከመውደቅ ይጠብቀው፤ አግኝቶም
አይጣ፤ እኔ ጎዳና ላይ በወደኩበት የሚላስ
የሚቀምስ ባጣሁበት ወቅት እስትንፋሴን
ለማቆየት የብዙዎችን በር አንኳኩቻለሁ፤
ያገኘሁት ምላሽ ግን ልብን የሚሰብር ነው።
በጣም ደጋግ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ጨካኝ ልብ
ያላቸውም አጋጥመውኛል፤ ሰው እኮ ሰው
የሚባለው በፈተና በችግር ወቅት ለሰው ሲደርስ
ነው። ትናንት ጀግና ሲለኝ የነበሩት ሰዎች ጎዳና
ላይ መውደቄን መቸገሬን አይተው ሸሽተውኛል፤
ፊት ነስተውኛል፡፡ እኔ ይሄንን የምለው ለወቀሳ
ሳይሆን ሰው ውሰጥ በምላሻቸው ልቤን የሰበሩት
ለባንክ ስጫወት ልጁ ሲለኝ የነበረው የብሄራዊ
ቡድኑ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለና አብሮኝ
የተጫወተው ታፈሰ ተስፋዬ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን
ሰዎች ስማቸውን አታንሳ እያልኩኝ ያነሳሁት
እንዲወቀሱ ሳይሆን እንዲማሩበትም ነው፡
፡ አሰልጣኝ አሸናፊ ተቸግሬያለሁ ብዬ ነግሬው
ልጄ ነህ ሲለኝ የነበረው ሰው አይኔን ማየት
ተጠይፎ በዘበኛ ነው 100 ብር የላከልኝ እኔ
ገንዘቡ አይዞህ ቢለኝ ቢያበረታታኝ ይበልጥብኝ
ነበር በዘበኛ ተጠይፎ ከሚልክልኝ፡፡ አብሬው
የተጫወትኩት ታፈሰ ተስፋዬም ገና ለገና
ወድቋል ብሎ ያሳየኝ ነገር መግለፅ ይቸግረኛል፡
፡ እኔ ለዚህ ለደረጃ የበቃሁት ተመኝቼ ወይም
ከሱቅ ገዝቼው አይደለም ወይም በመጠጥ ሱስና
በቁማር አይደለም የወደኩት፡፡ በትዳር ህይወቴ
ባጋጠመኝ ችግር ነው፡፡ ነገ ሁላችንም ምን
እንደሚገጥመን አናውቅም ግን የሚያዝን ደግ
ልብ ቢኖረን መልካም ነው፡፡ እኔ የሰው ልጅ
መቼም ቢሆን የሰው ፊት ከማየት እንዲያድነው
ነው የምመኘው፡፡