በመሸሻ ወልዴ
የኢትዮጵያ እግር ኳስን በክለብ ደረጃ
ከወጣትነት ዕድሜውና ከወጣት ቡድን
ተጨዋችነት ዘመኑ አንስቶ ለ18 ዓመታት
ተጫውቶ አሳልፏል፤ በተጫወተባቸው
የተለያዩ ክለቦች ውስጥም በመሀል ሜዳ
ላይ ድንቅ ብቃቱን ለተመልካቾች በማሳየት
በብዙዎቹ ዘንድ ሊደነቅም ችላል፤ ይህ
ተጨዋች መሀሪ አላምረው ሲሆን የእግር
ኳስን ካቆመ በኋላም የአሁን ሰዓት ላይ
በሹፍርና ሙያ ተሰማርቶ ሕይወቱን
እየመራ ይገኛል፤ የመሀል ሜዳ ላይ ባለው
ጥሩ የሆነ ብቃት በተለይ ደግሞ ለአጥቂ
ስፍራ ተጨዋቾች ኳስን መግቦ በመስጠትና
ራሱም የተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾችን
አልፎም ግብ በማስቆጠርና በአንድ ሁለት
ቅብብልም ከአጋር ጓደኞቹ ጋር ጥሩ
ይንቀሳቀስ የነበረውን ይህ የቀድሞ እግር
ኳስ ተጨዋች በዛሬው የቀድሞ እግር ኳስ
ተጨዋቾችን በምናስታውስበት የOldes
But Goodies አምዳችን ላይ እንግዳ
አድርገን ያቀረብነው ሲሆን እሱም ስለራሱ
ሕይወት፣ ስለተጨዋችነት ዘመኑና
ሌሎችንም ጉዳዮች አስመልክቶ ምላሹን
ሰጥቶናል፤ ተከታተሉት፡፡
ስለውልደቱ ኳስ አጀማመሩና ኳስን የት
ጀምሮ የት እንደጨረሰ፡-‘‘የእኔ ውልደትና
እድገቴ የአማኑኤል ቶታል አካባቢ ነው፤
እዚያም ነው ከልጅነቴእድሜ ጀምሮ
የማፈቅረውን እግር ኳስ ተጫውቼ እስከትልቅ
ደረጃ ላይለመድረስ የቻልኩት፤ የእግር ኳስን
በቅድሚያ መጫወት የጀመርኩት ለኢትኮባ
የእግር ኳስ ክለብ በወጣት ቡድን ደረጃ ነው፤
ከዚያም በ4 ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ዋናው ቡድን
አድጌ ልጫወት ቻልኩ፤ቀጥዬም በሌሎች
የተለያዩ ክለቦች ውስጥም ገብቼ ከተጫወትኩ
በኋላ ነው በመጨረሻም የኢትዮጵያ ንግድ
ባንክ ክለብ ውስጥ የእግር ኳስን ተጫውቼ
ለማቆም የቻልኩት”፡፡
–የትውልድ ሰፈሩና አካባቢው
ስላፈራቸውና ያደንቃቸው ስለነበሩት
ተጨዋቾች፡-‘‘በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ
ከአካባቢያችን በኳስ ጥበባቸውና በድንቅ
ችሎታቸው አደንቃቸው የነበሩ ብዙ
ተጨዋቾች ነበሩ፤ እኔ ከማስታውሳቸውና
ልዩ ቦታ ከምሰጣቸው ተጨዋቾች ውስጥ
እነ ምንቱ ካሳ፣ መቻል ካሳ፣ ኑረዲን
አብደላና ዓለሙ ሰብስቤ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፤
እዚያው አቅራቢያችንም እነ ወልዴ ባልቻ፣
ተካ ገለቱ፣ ጌቱ መልካ፣ መላኩና ሌሎችም
አካባቢያችን ያፈራቸው ምርጥ ተጨዋቾችም
ነበሩ፤ ያኔ በተለይ የእኛ የአማኑኤል ቶታል
አካባቢምበወቅቱ ምርጥ ታለንት ያላቸው
ልጆችንም ያፈራ ስለነበር የእግር ኳስ ፋብሪካ
የሚል ስያሜም ለሰፈራችን ወጥቶለት የነበረ
ሲሆን እንደውም እንዲህ በሚል ይዜምልንም
ነበር ‘‘ልብሳቸው ጥቋቁር እንደሀዘንተኛ
13ቶች መጡ የጨዋታው ዳኛ ተብለን
እንጠራም ነበር፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ አሰልጣኝ፡- ለእኔ
ከወርቁ ደልገባ በላይ ማን ሊሆን ይችላል!
አሰልጣኝ ወርቁ ደልገባ የእውነት በሙያው
ያልተዘመረለት ጀግና ነው፡፡ እሱን ላደንቀው
የቻልኩትም የማሰልጠን ብቃቱ ልዩ በመሆኑ
ነው፤ ወርቁ በሙያው ቆይታ የአንድን የእግር
ኳስ ተጨዋች ብቃት የመረዳትና የማንበብ
ችሎታው ይገርመኛል፤አንድ ተጨዋች
በምን መልኩ መጫወት እንዳለበትና ምን
አይነት ብቃትም እንዳለው ከችሎታው
ተነስቶ በሚገባ ያውቃልና እሱ ነው የእኔ
ተቀዳሚና የመጀመሪያው ምርጡ አሰልጣኝ፤
ከወርቁ የማሰልጠን ችሎታው በተጨማሪ
በስልጠናው ወቅትም ከእኛ ጋር ሆኖ የእግር
ኳስን ሲጫወትም ያለው ብቃት የሚገርም
ነው፤ ያንን ሳይ ምናለ ድሮ ደርሼ ሲጫወት
ባየው ወይም ደግሞ የተቀዳ ፊልም ኖሮ
ብመለከተው ብዬም ተመኝቻለሁ፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ተጨዋች፡
-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ
ከተመለከትኳቸው ተጨዋቾች መካከል
በችሎታው የእኔ የመጀመሪያው ተመራጭና
የማደንቀው ተጨዋች የኢትዮጵያ ቡና
አጥቂ የነበረውን ሚሊዮን በጋሻውን ነው፤
በመቀጠል የማደንቀው ሌላ ተጨዋች
ለመድን፣ ለኢትዮጵያ ቡና፣ ለኤሌክትሪክና
ለመሳሰሉት ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈውን
ስምዖን አባይን ነው፤ ሁለቱን ተጨዋቾች
የጨዋታ ዘመኔ ምርጥ ልላቸው የቻልኩትም
እንደ አጥቂ ስፍራ ተጨዋችነታቸው ለእኔ
የአማካይ ስፍራ እንቅስቃሴዬ በቦታ አያያዝና
አጠባበቃቸው በጣም ምቹ ስለሆኑልኝና
ምርጥ ብቃትም ስላላቸው ነው፤ ሁለቱም
ተጨዋቾች ኳስን በምይዝበት ሰዓት ለደብል
ፓስ አጨዋወትም ኳስን ሰንጥቄ ልሰጥ ስልም
ያላቸው አቋቋም ስለሚመቸኝ አድናቂያቸው
ነበርኩኝ፤በአንድ ወቅት ላይ አንድ የቡና
ደጋፊ እንደውም የእኔንና የሚሊዮንን በኳስ
ላይ ያለንን መግባባት ተመልክቶም ምን
አለመሰለህ መሀሪና ሚሊዮን የእግር ኳሱን
ሲጫወቱት በጣም ከመግባባታቸው የተነሳ
ኳስን ከአንድ የግቢ አጥር ውስጥ ጀምረው
በደብል ፓስ በመቀባበል ሳሎኑን፣ መኝታ
ቤቱን አልፈው እስከ ማድቤት /ኩሽና/ ቤት
ድረስ በጋራ እየተቀባበሉ ይዘውት ይሄዳሉም
ብሎም ነበርና በተጨዋችነት ዘመኔ ለሁለቱም
ተጨዋቾች ልዩ አድናቆት ነው ያለኝ፡፡
–የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋችነት
ቆይታው ላይ አብሮት ተጣምሮት ሲጫወት
ስለሚመቸውና ስለሚደሰትበት ተጨዋች፡
-የኢትዮጵያእግር ኳስ ውስጥ አብሬያቸው
ከተጫወትኳቸው ተጨዋቾች መካከል
ከእኔአጠገብ ሆኖ ሲጫወት በጣም ይመቸኝና
ያስደስተኝ የነበረው ተጨዋች ጥላሁን መንገሻ
ነው፤ከጥላሁን መንገሻ ጋር ከሰፈር አንስቶ
እኔ በእድሜ የማንስ ቢሆንም አብረን ነው
ተጫውተን ያደግነው፤ ከእሱ ጋር አብሬው
መጫወቴ በጣም ያስደስተኛል፤ከእሱ ጋር
በተያያዘም አንድ ትንሽ ቅር የሚለኝ
ነገርም በተደጋጋሚ ብዙጊዜ አብረን
ያለመጫወታችንም ነው፡፡
–በእግር ኳሱ አብሮት ባለመጫወቱ
የሚቆጨውና አንድ ቀን አብሬው ብጫወት
ብሎ የሚመርጠው ተጨዋች፡-የኤሌክትሪክ
የቀድሞው ድንቅ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች
ሸዋንግዛው ተመስገን ያለው የኳስ ብቃትና
ክህሎት በጊዜው ምርጥና ኳስን ይዞና
ተቆጣጥሮም ይጫወት ስለነበር፤ እንደዚሁም
በአጨዋወቱም የተረጋጋ አይነት ተጨዋች
ስለነበር ከእሱ ጋር አብሬው አለመጫወቴ
በጣም ይቆጨኛል፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ግብ ብሎ
የሚጠራት፡-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ
ለበርካታ አመታቶች ስጫወት ካስቆጠርኳቸው
ግቦች መካከል በአድናቆት ደረጃ የምጠቅሳቸው
ብዙ ቢሆኑም የመጀመሪያ ደረጃ ሰጥቼ
የምወዳት ግብ ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ተጨዋች እያለሁ ከብርሃንና ሰላም ጋር
ስንጫወት በግብ ጠባቂው ገዛኸኝ ባንክስራ
ላይ ያስቆጠርኳትን ነው፤ እሱ ላይ ያገባሁት
ግብም አልፌው ነበር፤ ብዙ ጊዜም እኔ ግቦችን
የማስቆጥረው በረኞችን አልፌም ነበርና ያቺን
ግብ ሁሌም አደንቃታለሁ፡፡ እሷ ግቤም የባንክ
ሰርቪስ ላይም በወቅቱ ፎቶው ተለጥፎም
ነበርና ያኔ በተደጋጋሚም እመለከታትም
ነበር፡፡
–የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ
ለተለያዩክለቦች ሲጫወት ስለነበረው ቆይታና
ስላሳለፈው ትዝታ፡- በኢትዮጵያ እግር
ኳስ ውስጥ በክለብደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ
የተጫወትኩት ለኢትኮባ ወጣት ቡድን ነበር፤
እዚያም ልገባ የቻልኩት የሰፈራችን ልጆች ጋር
ለኤሌክትሪክ የወጣት ቡድን ለመመረጥ ወደ
ስፍራው ካመራን በኋላ ምርጫው በመቅረቱ
ያን እለት ሌላ ምርጫ ያደርግ ወደ ነበረው
የኢትኮባ ክለብ ምርጫ ሄጄ ነው በስኳዱ
ልያዝ የቻልኩት፡፡ እዚያም በነበረኝ ቆይታዬ
ለአራት ወር ያህል ልምምዴን ከሰራውና
ከተጫወትኩኝ በኋላ የኢትኮባ ዋናውቡድን
ሲዳከም በአሰልጣኝ ካሳሁን ተካ የወጣት
ቡድኑ ላይ ታይቼ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ
በፈጣን ሁኔታ ያሳደገኝ ሁኔታ የማይረሳኝ
ነው፤ ያኔ የኢትኮባ ክለብ ውስጥም ከ1979-
82 ዓ.ም ተጫወትኩኝ፤ ቀጥሎ ያመራሁት
ደግሞ በአሰልጣኝ ወርቁ ደልገባ አማካኝነት
ተመልምዬ ወደ ባንክ ክለብ ነው፡፡ እዚያም
ለ1 አመት ተጫወትኩኝ፤ በእዚህ ቡድን
የመጀመሪያ ዓመት ቆይታዬም ጥሩ ጊዜን
ላሳልፍ ችያለው፤በቡድኑ በተለይ የአሰልጣኝ
ወርቁ ደልገባ የማሰልጠን ችሎታ መቼም
ቢሆን የማይረሳኝ ነው ያም ሆኖ ግን በዓመቱ
የአሰልጣኝ ለውጥ ተደርጎ ታም ሩሙልጌታ
ወደ ቡድናችን ሲመጣ ከአጨዋወት ዘይቤ
ጋር በተያያዘ ክለቡ ውስጥ ለብዙዎቻችን
ተጨዋቾች ማለትም ለእኔ ለተከላካያችን
ደጀኔ ምቹ ነገር ሊፈጠርልንስላልተቻለ
ክለቡን ልለቅ ቻልኩ፤ደጀኔ እንደውም ጥሩ
የሚያገናዝብ ተጨዋቻችን ሆኖ ያልሆነ
ነገር ሲሉት ነውበእዚያውም ኳስመ ጫወት
ያቆመው፤ በጊዜው እሱ ለእኔም ሆነ ልጆች
ለነበርነው ተጨዋቾች ጥሩ ነገር ያደርግልንበር፤ ስናጠፋ ይገስፀን ነበር ጥሩ ስንሰራ
ያበረታታን ነበር፤ በተለይ ለእኔ ባንክ
ውስጥ እንደዛ ስሆንና ልወጣ ስል አይዞህ
የትምሄደህት ጫወታልህም ይለኝ ነበር፤
ከባንክ ከወጣው በኋላም አሰልጣኝ ስዩም
አባተ ለመድን እንድጫወት ጥሪ አድርጎልኝ
ወደ ክለቡ ብሄድም የባንክ ክለብ አመራሮች
እኔን ለመድንም ሆነ ሌላ በተመሳሳይ ሊግ ላይ
ለሚገኝ ማንኛውም ክለብ እነዚህ ተጨዋቾች
በባንክ ቆይታቸው ተገቢ ያልሆነ ነገር
አድርገው ስለወጡ መጫወት እንደማልችል
ለፌዴሬሽንም ስላሳወቁ ክለቦቹ ቅርርብም
ስላላቸው በታችኛው ሊግ ለሚጫወተው
የምድር ባቡር ክለብ ፈረምኩኝ፣ የምድር
ባቡር ላይ በነበረኝ ቆይታም ክለቡን
ለሻምፒዮንነት ለማብቃት ስንችል ይህ ድል
መቼም የማይረሳኝነው፤ በመቀጠል የገባሁበት
ክለብ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ነው፤ የቡና
ተጨዋች እያለሁ በክለቡ የቆየሁት በ1985
እና በ1986 የውድድር ዓመት ላይ ሲሆን
ይህ ቆይታዬ መቼም የማይረሳና ሁሌም
የምወደውነው፤ ቡድኑ ውስጥ እያለው
በተለይ ከሚልዮን በጋሻው፣ ጥላሁን መንገሻ፣
ገ/ኪዳን ነጋሽ ጋምብሬ እና በጣም ይመክረኝ
ከነበረውና ለእኔም ልዩ ቦታ ይሰጠኝ ከነበረው
አስራት አዱኛ ጋር አብሬ ስለተጫወትኩም
ለእሱ ልዩ ክብርም ነው ያለኝ በቡና ተጫውቼ
በማለፌም ሁሌም ስደሰትም እኖራለው፡
፡ የቡና ክለብን ከለቀቅኩኝ በኋላ በድጋሚ
የተጫወትኩበት ቡድን ደግሞ የባንክ ክለብ
ነው በእዚህ ቡድን ከ1987 አንስቶ እስከ
1997 ዓ.ም ድረስም ቆይቼ ተጫውቻለው
በኋላ ላይ ግን የባንክ ክለብ ውስጥ የነበረው
የአሰራር መዋቅር ክለቡን የሚጎዳ ሆኖ
ስለተመለከትኩና በእዚያ ዙሪያም በወቅቱ
ከነበረው የክለቡ ፕሬዝዳንት ጋርም አንድ
አንድ ነገሮችን ስንነጋገር ከተግባር ይልቅ
ወሬ ላይ ብቻ ያተኩር ስለነበርም መስማማት
ላይ ስላልቻልን ሁኔታዎች ሁሉ ጥሩ ሆነው
ስላላገኘኋቸው ራሴን ከቡድኑ አገለልኩና
በእዚያው ኳስን አቆምኩ፤ ያን ወቅት ላይ
ሞባይል የለም ነበር እኔን ለመመለስም ጥረት
ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ከማንም ጋር ልገናኝ
ስላልቻልኩ በእዚሁ ከኳሱ ራሴን አገለልኩ፡፡
–በእግር ኳስ በጣም ስለተደሰተበትና
ልዩ ቀን ብሎ ስለሚያነሳው፡-የእግር ኳስን
ተጫውቼ ሳሳልፍ በጣም ተደስቼ ያለፍኩበት
ቀን ቢኖር የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች ሳለው
የ1986 ዓ.ም ላይ ቅዱስጊዮርጊስን 5-3
ስናሸንፍ ነው፤ ያ ጨዋታ ለእኛ በጣም ምርጥና
እነሱን በልጠን ያሸነፍንበትም ነበር፤ በጊዜው
ከጨዋታው በኋላ የቡና ደጋፊዎችሳሪስ
ወደሚገኘው ካምፓችን ልናመራ ስንል
በውጤቱ ተደስተው እየጨፈሩ ስለነበር ወደ
ጎተራና ሳሪስ የሚወስደንን የመሽዋለኪያ
መንገድን ዘግተውብን በቦሌ ወሎ ሰፈር
አድርገን የሄድንበት ጊዜ አልረሳውም፡፡ ያኔ
በእዚህ ግጥሚያም ጎል ማስቆጠሬም ልዩ
የደስታ ስሜትም ፈጥሮብኝ አልፏል፡፡
–በእግር ኳስ ተጨዋችነትዘመኑ
በሃዘን ልቡ የደማበትና የተሰበረበት ቀን፡-
የመጀመሪያው ከባድ ሃዘኔ ልክ የዛሬ 10
አመት በጣም የምወደውን ወላጅ አባቴን
በሞት ያጣሁበት ቀን ሲሆን፤ ሌላው ሀዘኔ
ደግሞ የ1987 ዓ.ም ላይ የኢትዮጵያ ንግድ
ባንክ ክለብ ተጨዋች እያለው ከቅዱስ
ጊዮርጊስ ጋር ለዋንጫ ስንጫወት እኔ
ለበላቸው ይታየው ትንሼ ጥሩ ኳስ ሰጥቼው
ቀድመን ግብ አስቆጥረን ሻምፒዮና የመሆን
እድላችንንም ወደሶስት አስፍተን በቅዱስ
ጊዮርጊስ 3-1 ተሸንፈን ዋንጫ ያጣንበትን
ቀን መቼም የማልረሳውና ሁሌም የማዝንበት
ቀን ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ለእኔ እናት ክለብ
የሆነውና ከክለቡ ስለቅም የወርቅ ሽልማት
ሰጥቶኝ የነበረው የባንክ ክለብ መፍረስ ሁሌም
ይቆጨኛል፡፡
-መሃሪ ራሱን በ3 የተመረጡ ቃላቶች
ግለፅ ቢባል እንዴት ይገልፃል፡-ለሃይማኖቱ
ከፍተኛ ቦታ ስላለው ፈጣሪን ይፈራል፣ ሰውን
ያከብራል፣ እንደዚሁም ነገሮችን ሳይሸፋፍን
ፊት ለፊትና ቀጥታ ይናገራልና ይሄ ነው
ባህሪው፡፡
–ለመጀመሪያ ጊዜ በእግር ኳስ
ተጨዋችነት ያገኘው ትልቁደመወዝና ምን
ላይ እንዳዋለው፡-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ
ለመጀመሪያ ጊዜ ስጫወት ያገኘሁት ትልቁ
ደመወዝ የኢትኮባ ክለብ ውስጥ እያለሁ
150 ብር ነው፤ ያኔም 50 ብሩን ለራሴ
ኪስ በማስቀረት 100 ብሩን ለእናቴ ነበር
የሰጠኋትና ያን መቼም የማልረሳው ነው፡፡
–ዛሬ የአንድ ተጨዋች ወርሃዊ ደምወዝ
200 ሺህ ብር ገብቷል፤ ይህንን ክፍያ ከእናንተ
ዘመን ጋር ስታነፃፅረው ምን ይሰማሃል፤
ምነው በዚህ ዘመን በኖርኩ ብለህ ትመኛለህ፡
–አዎን፤ በአጭር አመታት ውስጥ ጥሩ ኑሮን
ለመኖርና ቤተሰብንም በሚገባ ከማስተዳደር
አኳያ ሳየው ከነበረኝ ጥሩ የኳስ ችሎታዬ
በመነሳት ምነው በዚህ ዘመን ብፈጠር
ብዬ የተመኘሁበት ጊዜ አለ፤ የእኛ ጊዜ ላይ
የምናገኘውገንዘብ በወቅቱ ዋጋ ነበረው፡፡ ያም
ሆኖ ግን ተጨዋቾች አሁን የሚያገኙት
ገንዘብ ከጊዜውና ከወቅቱ ጋር የሚሄድ ስለሆነ
ማግኘታቸው ብዙም አይገርምም ሆኖም ግን
ተጨዋቾቹ እንደሚያገኙት ክፍያ ራሳቸውን
በመጠበቅ ለእግር ኳሱም ዋጋ ሰጥተው
ጥሩ ሊጫወቱና ተመልካቹንም ሊያስደስቱት
ለእዚያም ጠንክረው ሊሰሩም ይገባል ነው
የምለው፡፡
—ከውጪ አገር ብሄራዊ ቡድኖች የማን
ደጋፊ ነህ፡-የብራዚል
-ከውጭ አገር ክለቦችስ፡-አሁን ላይ የእለት
እለት ጨዋታን በማየት ነው ጥሩ ለሚጫወት
ክለብ አድናቆቴን የምሰጠው እንጂ መደገፍ
አልወድም፤ የቀድሞው ጊዜ ላይ ግን በእነካንቶና ዘመን የማንቸስተር ዩናይትድን ቡድን
እደግፍ ነበር፡፡
–ከውጪ አሰልጣኞች በችሎታቸው
የምታደንቀው፡-ጋርድዮላን
ከኳስ ተጨዋቾችስ፡- ሀዛርድን
-መሃሪ እግር ኳስ ተጨዋች ባይሆን ኖሮ
በምን ሙያ ላይ ይገኝ ነበር፡- በትምህርቱ ጥሩ
ደረጃ ላይ ደርሶበአንድ ሙያ ላይ ይሰማራ
ነበር፤ ይህንን ለማለት የቻልኩትም ገና ልጅ
እያለሁ ጀምሮ በትምህርቴ ጥሩ ስለነበርኩ
ነው፡፡ የባንክ ክለብ ውስጥ ተጨዋች እያለሁም
የባንክና ፋይናንስ ትምህርትን እየተማርኩ
ነው ለዝግጅት ወደደብረዘይት ባመራንበት
ጊዜ በኳሱ ምክንያት አንድ ኮርስን ሳልወስድ
ቀርቼ ሳልመረቅ የቀረሁበትም ጊዜ
ነበርና የእግር ኳስ ተጨዋች ባልሆን ኖሮ
በትምህርት ጥሩ ቦታ እደርስ ነበር፡፡
–የእግር ኳስ ተጨዋች ሆኖ በማለፉ
ስለሚሰማው ስሜት፡-የኢትዮጵያ እግር ኳስ
ላይ ኳስ ተጨዋች ሆኜ በማሳለፌ ጥሩና ደስ
የሚል ስሜት ነው አሁንም ድረስ የሚሰማኝ፤
ለኳስ ልዩ ፍቅር ነው ያለኝ፤ በቅርቡ ራሱ
መኪናዬን ጋራዥ እያሰራሁ በነበረበት ወቅት
ህፃናቶች ኳስ ሲጫወቱ ሳይ አብሬያቸው
የተጫወትኩበት ሁኔታ ነበርና እነሱም ካዩኝ
በኋላ አሰልጥነን ያሉኝና በሌላ አጋጣሚ ደግሞ
መኪና እየነዳሁ ስሄድም አሁንም ህፃናቶች
እየተጫወቱ ሳይ ከሌላ መኪና ጋር ልጋጭ
የተቃረብኩበትም ወቅት ነበርና ያኔ ለኳስ ካለኝ
ፍቅር የተነሳ ከመኪናው በመውረድ ከእነሱ
ጋር ወርጄ ልጫወት ያልኩበት ሁኔታም አለና
ተጨዋች ሆኜ ማለፌ ያስደስተኛል፡፡
–የእግር ኳስን ተጫውቶ ካለፈ በኋላ
ጫማውን ስለሰቀለበት ምክንያት፡-የእግር ኳስ
ተጨዋቾች ብዙ ጊዜ ኳስን የሚያቆሙት
በጉዳት ወይም ደግሞ ከአሰልጣኝ ጋር
ባለመስማማትና ተስፋ በመቁረጥ እና ወይም
ደግሞ እድሜ ገድቧቸው በቃኝ በማለት
እንደሆነ ቢታወቅም እኔ ግን ከወጣትነት
እድሜዬ አንስቶ ኳስን ለ18 አመታት ያህል
ከተጫወትኩ በኋላ በቀጣይነት ለ4 እና ለ5
አመታት መጫወት እየቻልኩኝ ነው የባንክ
ክለብ ውስጥ የነበረው አሰራር የማይጥመኝ
ስለነበር ራሴን ከኳሱ ለማግለል የቻልኩት፡፡
–ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እየተመረጠ
ብዙም ቆይታ አለማድረጉናያለመጫወቱ
ምክንያት፡-የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ላይ
በአገር ውስጥም በውጪ አገር አሰልጣኞችም
በተደጋጋሚ ተመርጩ የምጠራበት ወቅት
ቢኖርም የመጫወት እድሉን እና በቡድኑ
የመቆየት እድሉን ግን ብዙም ላገኝ
አልቻልኩም የእዚህ ምክንያትንም ላቀው
አልቻልኩም፡፡
–በተቃራኒነት ስትጫወት አንተን
ያስቸግርህ የነበረው ተጨዋች፡- ብዙም ገጥሞኝ
አያውቅም፤ አንድ ጨዋታ ላይ ግን የባንኮች
ክለብ ውስጥ እያለሁ በአሰልጣኝ ሰውነት
ቢሻው በሚመራው የኒያላ ክለብ ውስጥ
የሚጫወተው ጅቡቲ የሚባል ተጨዋች ነበር፡፡
ይሄ ልጅ ያኔ ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታቶች
ለሐዋሳ ዱቄት ቡድን ተጫውቶም አሳልፏል፡
፡ ለኒያላ ያኔ ክለቡ የመውረድ አደጋ ከፊቱ
ተደቅኖበት ነበርና ከኛ ጋር ሲጫወቱ አሰልጣኝ
ሰውነት ቢሻው መሃሪን ማርክ አድርገው
ተከተለውም ብለውት ነበርና 45ቱን ደቂቃ
እኔን በመያዝ ብዙም እንዳልጫወት አደረገኝ
እኔም ተናደድኩ ያን ጊዜ ወደመልበሻ ክፍል
እያመራን ሳለ አሁንም ከሜዳ ውጪም እዚም
ያዘኝ አልኩት ያኔ እሱ ተናደደ የእኛ ልጆችም
አጨዋወቱ አላስደሰታቸውም፤ የሁለተኛው
አጋማሽ ላይ ግን እኔ አስቀድሜ በተናገርኩት
ነገር ተፀፅቶ ሳይሆን አይቀርም ምንላድረግ
አሰልጣኙ አዞኝ ነው አለ፤ በኋላ ወደእኔ
ይመጣና ይሸሸኛል ያኔ አሰልጣኝ ሰውነት
ማርክ አድርግ እንዳትለቀው ያልኩክን አድርግ
ሲለው ይመታና ማርክ ለማድረግ ጣረና
ወዲያው ስሸሸው ቀንድቤ አካባቢ መትቶም
ተረተረኝ እዛ ጨዋታ ላይ እኔ ብመታም
አንድ ኳስ ማስቆጠሬና አንድ ኳስን ደግሞ
ለአለማየሁ ሰጥቼው እኛ 2-1 ያሸነፍንበትን
ጨዋታ አልረሳውም፡፡
–የእግር ኳስን ሲጫወት ስላጋጠመው
ከፍተኛ ጉዳት፡-በኢትዮጵያ ውስጥ የእግር
ኳስን ስጫወት ከፍተኛ የሚባል ጉዳትን
ያስተናገድኩት አሁን ከላይ በጠቀስኩትም
የኒያላ ክለብ ጋር ስንጫወት ያጋጠመኝ ነው፤
እኔን የመታኝም የእነሱ ተጨዋች ጁቡቲ
ነበር፤ጎን ፊቴን በክርን መቶኝ ሊተረትረኝ
ችሏል፤ ያኔም አፍሪካ ከፍተኛ ክሊኒክ ሄጄ
ነው የታከምኩት ልሰፋ ስልም ዶክተሩ
በማደንዘዣ ነው ያለማደንዘዣ ሲለኝ እንዴ
ስፖርተኛ ነኝ ያለማደንዘዣ ብዬ ነበር
የተሰፋሁት ያኔም ስሰፋ ምንም ሳያመኝ ሲቀር ዶክተሩ የእውነትም ስፖርተኛ ያለኝን
መቼም ብሆን አልረሳውም፡፡
–ስለትዳር ህይወቱና ባለቤቱን ሲገልፃት፡
– ከባለቤቴ ቻይና ጋር ትዳርን መስርቻለሁ፡፡
ከእሷም ጋር ባለኝ የእስካሁን ያማረ የትዳር
ቆይታዬም 4 ልጆችን ማለትም ሁለት
ወንድ ሁለት ሴት ወደዩኒቨርሲቲ የገባውን
የ19 አመቱን ናትናኤል የ13 አመቷን ሊያ
የ13 አመቷን ናኒ እና አሁን 2ኛ አመቱን
የያዘውን ዮሃንስን /ጆኒን/ እንደዚሁም ከቀድሞ
ባለቤቴም አሁን ዩንቨርስቲ እየተማረች
ያለች የ22 ዐመቷ ሀናን ላፈራም ችያለው፡
፡ ባለቤቴን በተመለከተ ለእኔ በጣም ጥሩ
የሆነች ሴት ናት፤ እሷ ከእኔ ጋር ለመኖር
ስትልም ነው ብዙ የውጭ እድሎችን ትታም
አብራኝ እየኖረች ያለችውና በእዚህ አጋጣሚ
በጣሙን እንደምወዳት እንደማከብራትና
እንደማመሰግናትም ለመናገርም የምፈልገው፡፡
–የአሁን ሰአት ላይ ስለሚገኝበት ሁኔታ፡
–የእግር ኳስ ተጨዋችነትን ካቆምኩ በኋላ
አሁን የምገኝበት ሁኔታ የራሴን ታክሲ
በመግዛት በሹፍርና ሙያ ላይና እንደዚሁም
ደግሞ የአካባቢያችንም ላይ የተቋቋመን ክለብ
ኮርስም ወስጄ ስለነበር እነሱን ሳሰለጥን ቆይቼ
ነበር፡፡ ሆኖም ግን ክለቡ በፋይናንስ እጥረት
ደርጃ ብዙም ሊዘልቅ ባለመቻሉ ማሰልጠኑን
በማቆም የአሁን ሰአት ላይ ቤተሰቤን
ለማስተዳደር ስል በሹፍርናው ሙያ ላይ ብቻ
ተሰማርቼ ስራዬን እየሰራሁ ነው፡፡
–ወደአሰልጣኝነት በቀጣይ ጊዜ ይመጣ
ስለመሆኑ፡- በአሰልጣኝነት ሙያ ላይ
ተሰማርቼ የአገሬን እግር ኳስ የተሻለ ቦታ
ላይ እንዳደርስ ከእኔ በሚጠበቀው መልኩ
አንድ ነገርን ለመስራት የሁልጊዜም ምኞቴ
ነው፤ የእግር ኳስን ሳስብ ሁሌም ሰፈር
ውስጥ የሚቀሩ ታዳጊ ወጣቶች በጣም
ያሳዝኑኛል እነሱን እንደዚሁም ደግሞ በክለብ
ደረጃም ወጣቶችን ላሰለጥን ብዬም አስባለው፤
ስለዚህም ወደፊት የእግዚአብሄር ፈቃድ
ታክሎበት ወደዚህ ሙያ ላይ መምጣቴ
የማይቀር ነው፡፡
በመጨረሻ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት
ዘመኔ ላይ እኔ ጥሩ ደረጃ ላይ እንድደረስ ብዙ
ሰዎች ከጎኔ ሆነው አግዘውኛል፤ በቅድሚያ
ቤተሰቦቼ ከእዚያ ውጪ የሰፈሬ የአማኑኤል
አካባቢ ልጆችና ጓደኞቼ እንደዚሁም ደግሞ
ታምሩ ሀይለ ማሪያም፣ ላስታ፣ ኑረዲን
አብደላ፣ ሃይሉ ሀብቴ፣ ፍቃዱ ጅሩና ከእኔ
ጎን የነበሩትን የስፖርት ቤተሰቦች ሁሉ
ለማመስገን እፈልጋለው፡፡