በሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች እጅግ ድንቅ እና ውብ ዝማሬ የተጀመረው እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የመጀመሪያው ግብ ጠባቂ አቶ ታደሰ ጌጤ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ በ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ጨዋታው ከተጀመረ 7ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለ ከተማው ተከላካይ አንተነህ ገ/ክርስቶስ ከቅጣት ምት የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ወደውጭ ወጥቶበታል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ብልጫ መውሰድ ችለው የነበሩት ቅ/ጊዮርጊሶች ተደጋጋሚ ግብ የማግባት ማድረግ ቢችሉም ወደግብ መቀየር ባለመቻላቸው አቻ ለመውጣት ተገደዋል።
10ኛው ደቂቃ ላይ አሉላ ግርማ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጭ የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ ሲወጣ ከ 4ደቂቃዎች በኋላ ተመሳሳይ ኳስ መቶ
የመቐለ ከተማው ግብ ጠባቂ በቀላሉ ይዞታል። 18ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም መሀመድ ሳይታሰብ ከ40 ሜትር ርቀት የመታውን ኳስ የመቐለ ከተማው ግብ ጠባቂ ፍዳን አሸኖ በድንቅ ሁኔታ አውጥቶታል። በተደጋጋሚ ወደ መቐለ ከተማ የግብ ክልል ጥረት ያደረጉት ቅ/ጊዮርጊሶች 25ኛው ደቂቃ ላይ አሉላ ግርማ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ መቶት በመጀመሪያው አጋማሽ ድንቅ የነበረው የመቐለ ከተማው ግብ ጠባቂ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 3ደቂቃዎች ሲቀሩት የቅ/ጊዮርጊሱ ተከላካይ ሳላዲን በርጌቾ ተከላካዮችን አታሎ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው አውጥቶታል።
በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ያለቻሉት መቐለ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ ብልጫውን መውሰድ ችለው ነበር።
ኳስ ተቆጣጥረው በድንቅ ቅብብል ወደ ቅ/ጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመድረስ የሞከሩት መቐለ ከተማዎች 61ኛው ደቂቃ ላይ በ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከሳጥን ውጪ በመታው ኳስ ሙከራ ቢያደርጉም ኳሱ ወደውጭ ወጥቷል። 66ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊስ ተከላካይ ምንተስኖት አዳነ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት የመቐለ ከተማው አማኑኤል ገ/ሚካኤል በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር።
ከግቡ መቆጠርም በኋላ ጫና ለመፍጠር የሞከሩት መቐለ ከተማዎች 72ኛው ደቂቃ ላይ አቻምቦንግ አምቤ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጭ የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥቶበታል። ተስፋዬ በቀለ ተቀይሮ ከገባ በኋላ ወደ ጨዋታው ሪትም ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ቅ/ጊዮርጊሶች 88ኛው ደቂቃ ላይ በአሜ መሀመድ ጥሩ ሙከራ ቢያደርጉም ኳስና መረብን ማገናኘት አልቻሉም። የጨዋታው መገባደጃ(90ኛው) ደቂቃ ላይ አበባው ቡጣቆ ከማእዘን ምት መምቻ አካባቢ ከቅጣት ምት ያሻገረለትን ኳስ ምንተስኖት አዳነ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብነት ቀይሮት ቡድኑን ከሽንፈት ታድጎታል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የቅ/ጊዮርጊስ ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ “ከአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታችን ነው፤ ጨዋታውን ማሸነፍ ፈልገን ነበር ግን የሜዳው ሶስተኛ ክፍል ላይ ጥሩ አልነበርንም እሱን አሻሽለን እንመጣለን። የመጀመሪያ ጨዋታ ከባድ እንደሚሆን ጠብቀን ነበር። ለማሸነፍ ነበር የመጣነው ግን ሜዳ ላይ ብዙ ስህተቶች ነበሩ እነሱን አሻሽለን መቅረብ ይጠበቅብናል።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
- ማሰታውቂያ -
የመቐለ ከተማው አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በበኩላቸው “ተጫዋቾቼ ሜዳ ላይ ባሳዩት ነገር በጣም ደስተኛ ነኝ። ያለባቸውን ተፅዕኖ ተቋቁመው ያሳዩትን ብቃት ማድነቅ አለብን። ገና 3ኛ ጨዋታ ነው 27 ጨዋታዎች ስላሉ እስካሁን ማሸነፍ ባለመቻላችን ብዙም ስጋት ውስጥ አንገባም።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።